‹‹ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ›› (ፊልጵ.፬፥፬)
ዲያቆን ያሬድ ጋሻው
ታኅሣሥ ፲፭ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሳታቋርጡ ጸልዩ በሁሉ አመስግኑ!›› ብሎ እንዳስተማረን የእግዚአብሔር ቸርነት ዘወትር በመዓልትና በሌሊት፣ በክረምትና በበጋ፣ በደስታና በሐዘን፣… አይፈራረቅምና ምስጋናውም አይታጎልም፤ ስለዚህም ሁል ጊዜ እናመሰግነዋለን። (፩ኛተሰ.፭፥፲፯)
ከመከራው በላይ የእግዚአብሔርን ቸርነት እያሰበ የሚያመሰግን ሰው፥ ዘወትር ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ደስተኛ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እስር ቤት ሁኖ በደቀ መዝሙሩ በአፍሮዲጡ አማካኝነት በወንጌል ለተከላቸው ተክሎች ምእመናን በላከላቸው መልእክት እንዲህ ይላቸዋል፦ ‹‹ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፥ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ!›› (ፊልጵ.፬፥፬)
ልጆች እያለን በሜዳ ላይ ሮጠን እና ድብብቆሽ ተጫውተን በሁለት ብር ብስኩት፣ በኀምሳ ሳንቲም ሸንኮራ፣ በመቶ ብር ጫማ… ደስታ ማግኘት ቀላል ነበር። አሁን ግን በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ፣ ብዙ ጓደኞች፣ በዓለም የናኘ ዝና… ደስታ የሚያሰጡን አልሆኑም። በአጠቃላይ ሕይወታችን ከምድራዊ ጉዳዮች ጋር ያለመጠን ለተሳሰርን ለእኛ፥ ደስታን እንደጨረቃ ተንጠራርተን የማንነካው ሆኖብናል። ከግል ሕይወታችንም ባለፈ በዙሪያችን የምንሰማው የዘረኝነት፣ የጦርነት፣ የስደት፣ የረኃብ… ወዘተ ወሬ፥ ሐዘንን እንጂ ደስታን የሚያሰሙ አይደሉም። መንኖ ጥሪትን፣ ከገዳም መግባትን፣ ከሰው መለየትን ገንዘብ ካደረጉ ቅዱሳን በቀር በእነዚህና በመሳሰሉት ምድራዊ ጉዳዮች የማይታወክ ሰው ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ኀዘኑ ከመጠን ሲያልፍ ደግሞ እግዚአብሔርን መበደል ይሆናል።
ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ የነገረን ወቅትና ሁኔታ የማይቀያይረው አንድ ደስታ አለን። ይህም በጌታ የሆነ ደስታ ነው። ‹‹ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ።›› ከላይ ካየነው ደስታ ይህን ደስታ የሚለየው፥ በዓይን አይተን፣ በጆሮ ሰምተን፣ በእጅ ዳሰን፣ በአፍንጫ አሽትተን… በአጠቃላይ በስሜት ሕዋሳቶቻችን ተረድተን፥ በከንፈሮቻችን መከፈትና በጥርሶቻችን መታየት የሚገለጥ ሳይሆን በልቡናችን የምናውቀውና በተስፋችን የምንገልጠው በመሆኑ ነው። ይህ ደስታ፥ በመራብም በመጠማትም፥ በመጥገብም በመርካትም ውስጥ አለ። በሰዎች ዘንድ ክብርን ማግኘት አይገነባውም፤ እንደ ጉድፍ መታየትም አይነደውም። ‹በጌታ› የሆነው ደስታ፥ የሰማዩን ፍጹም ደስታ ተስፋ የሚያስደርግ ነውና በክርስቲያኖች ዘንድ ሁሌም አለ።
በሁኔታዎች መለዋወጥ አብሮ የሚለዋወጠው ደስታ ሁሌም ሊያገኘን አይችልም። በምድር እንደመኖራችን ሰዎች ተምረው ሲመረቁ፣ ትዳር ሲመሠርቱ፣ ልጆች ሲወለዱ ደስ ይለናል፤ ሰዎች ሲሞቱ ግን እናዝናለን። ሀገር ሰላም ሲሆን ደስ ይለናል። በአንጻሩ ሰላም ሲደፈርስና ሕዝብ ሲራብ እናዝናለን።
በጌታ የሆነ ደስታ ኀዘንን አይሽርም (አይቃወምም)። ‹‹የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ መጽናናትን ያገኛሉና!›› እንዲል፤ ሞተ ወልደ እግዚአብሔርንና በሰማዕታት ላይ የተፈጸመውን ግፍ እያሰቡ ማዘን ማልቀስ የተወደደና መዓዛው ያማረ ድንቅ መሥዋዕት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ (ወልደ ነጎድጓድ) ፸ ዓመታት ፊቱን ቋጥሮ የኖረው በጌታ ደስ ስለማይለው አይደለም። ይልቁንም ጌታን ከመውደዱ የተነሣ የዕለተ ዓርብ መከራውን እያሰበ ያዝን ስለነበር ነው እንጂ። (ማቴ.፭፥፬)
ቤተ ክርስቲያን የትንሣኤውን ደስታ ብቻ ሳይሆን የስቅለቱንም ኀዘን ልጆቿን ሰብስባ ታውጃለች። ‹‹ብክይዎ ወላሕውዎ እለ ታፈቅርዎ፤ የምትወዱት ሰዎች ፈጽሞ አልቅሱለት!›› ብላ በቅዳሴዋ ታውጃለች። በደላችንም ሊያሳዝነን እንደሚገባ፥ ከምናኔ በፊት በነበረው ሕይወት ስለፈጸመው ኀጢአት ዕድሜ ዘመኑን ዕንባውን ሲያፈስ እንደኖረው ቅዱስ አርሳንዮስ ያሉ አባቶች ሕይወት ለእኛ ኃጢአት ‹‹የባሕርይ ግብራችን›› እስኪመስል ድረስ ዕለት ዕለት ለምንበድል ጎስቋሎች ታላቅ ትምህርት ነው።
በዚህ ውስጥ ግን የእግዚአብሔርን ቸርነት ማድነቅና ማመስገን ሁል ጊዜም ይኖራል።‹‹እግዚአብሔርን አመስግኑ ቸር ነውና፥ ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና።›› (መዝ.፻፴፭፥፩)
በፍቅሩ ስቦ በረድኤቱ አቅርቦ ለዚህች ሰዓት ያደረሰን የአባቶቻችን አምላክ የእኛም አምላክ ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። ፍቅሯን በልቡናችን ጣዕሟን በአንደበታችን ያሳድርብንና፥ ባለማወቅ ለምንመላለስ ለእኛ ምርኩዛችን የሆነች እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስሟ የተመሰገነ ይሁን፤ አሜን፡፡