‹‹ፈኑ እዴከ እምአርያም፤ ወአድኅነኒ፤ እጅህን ከአርያም ላክ፤ አድነኝም›› (መዝ. ፻፵፫፥፯)
ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ኅዳር ፲፫፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም
ከነቢያት አንዱ፣ እግዚአብሔር የሚወደው፣ እንደ ልቤም ብሎ የተናገረለት ታላቁ ንጉሥ፣ ነቢይ እና የቃል ኪዳን አባት የሆነው ቅዱስ ዳዊት ይህንን ኃይለ ቃል ተናግሯል፡፡
ሊቃውንት ይህንን ቃል በዚህ ወቅት አብዝተው ይሰብኩታል፡፡ ነቢዩ ዳዊትና ሌሎች ነቢያት ‹‹ውረድ፤ ተወለድ፤ አድነን›› እያሉ የተናገሩት ትንቢት፣ የጸለዩት ጸሎት፣ የቆጠሩት ሱባኤ ያስተማሩት ትምህርት፣ የሰጡት ተስፋ አብዝቶ የሚነገርበትና የሚሰበክበት ዘመነ ነቢያት ጾመ ነቢያት ስለሆነ ነው፡፡
ነቢያቱ አንድም በትምህርት አንድም በትንቢት፣ አንድም በጸሎት፣ አንድም በጾም ተወስነውና ጸንተው ሕዝቡን ሲያጸኑ፣ ሲያጽናኑ ነገረ ምጽአቱን እያዘከሩ ይተጉ የነበረበት ወቅት የሚታሰብበት ዘመን በመሆኑም ነው፡፡
ቅዱስ ዳዊት ‹‹እጅህን ከአርያም ላክ›› ያለው እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን እግዚአብሔር ወልድን ከሰማየ ሰማያት ከአርያም ዙፋኑ ወደዚህ ዓለም ይልከው ዘንድ ልጁ ክርስቶስም በአባቱ ፈቃድ በራሱም ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ያድነው ዘንድ አንድም ስለ ራሱ አንድም በአዳም ተገብቶ የአዳምን ጩኸት የአዳምንና የዘሩን ሁሉ ጥያቄና ልመና ያቀረበበት ቃል ነው፡፡ (መዝ. ፻፵፫፥፯)
ነቢዩ በጊዜው ይህንን ቃል የተናገረው እንደ ሳኦል ካሉ በሥጋ ከሚጣሉት ጠላቶቹ እንዲያድነው አንድም ከብዙ መከራ ከብዙ ጦር፣ አንድም ከፍትወታት እኩያት ከኃጣውእ ከፍዳ ከመከራ ሁሉ ፈጽሞ ያድነው ዘንድ የጸለየው ጸሎት ሲሆን በዚሁ ምዕራፍ ‹‹ገስሶሙ ለአድባር ወይጠይሱ..፤ነገሥታቱን በእደ መዓትህ ዳስሳቸው፤ ይጠፋሉም›› በማለት አብዝቶ በሥጋ በነፍስ ለሚታመንበት አምላኩ ከጠላቶቹ ያድነው፣ ይታደገው፣ ያጠፋቸውም ዘንድ ሲለምን እናገኛለን፡፡(መዝ.፻፵፫፥፭)
ነገር ግን ይህ ምሳሌውና ጊዜያዊ ትርጉሙ ነው፡፡ ምሥጢሩ ግን ከዚያ ያለፈ ነው፡፡ ነቢይ ነውና የሕዝቡን ጩኸት ልመናና ጸሎት ነው የተናገረው፡፡ በአዳም አባታችን ምክንያት ወደዚህ ዓለም የገባ ሞት ዓለሙን ሁሉ ገዝቶ ነበርና፡፡
ሥጋዊ ፍጥረትም ሁሉ ምግባሩና ትሩፋቱ፣ ጽድቁና እምነቱ ሁሉ ግምት ውስጥ ሳይገባ በሥጋ ወደ መቃብር፣ በነፍስ ወደ ሲኦል የሚወርድበት፣ እኩያን ፍትዋታት፣ እኩያን አጋንንት በሰው ልጅ ላይ ሁሉ የሠለጠኑበት፣ የመከራ ዘመን የኀዘንና የልቅሶ ዘመን ዘመነ ፍዳ ዘመነ መከራ ዘመነ ኩነኔ ነበርና፡፡
ስለዚህ ለአዳም የተገባው ቃል ኪዳን ይፈጸም ዘንድ እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን ይልክ ዘንድ፣ እግዚአብሔር ወልድም በአባቱ ፈቃድ ይወርድ፣ ይወለድ ዘንድ የሰጠውንም የተስፋ ቃሉን ፈጽሞ ከጠላት ዲያብሎስና ከክፉዎች አጋንንንት ይታደጋቸው ዘንድ በትጋት ይጸልያል፡፡
የተስፋ ቃሉ ምን ነበር? ከተባለ ‹‹እምድኅረ ሐሙስ መዋዕል ወመንፈቀ መዓልት እምሕረከ ወእሠሃለከ በብዝሐ ሣህልየ ወምሕረትየ ወእወርድ ውስተ ቤትከ ወአኀድር ውስተ ከርሥከ በእንቲአከ…፤ከአምስት ተኩል በኋላ እምርሃለሁ፤ ይቅርታም አደርግልሃለሁ፡፡በይቅርታዬ ብዛትና በምሕረቴ ብዛትም ወደ አንተ ቤት እወርዳለሁ፤ በወገንህም ከርሥ አድራለሁ፤ ይህ ሁሉ ስለአንተ ድኅነት ይሆናል›› የሚል ነው፡፡ (ቀሌምንጦስ ምዕ.፫ቁ. ፲፱)
ለዚህ ነው ጠላት ዲያብሎስ እና ሠራዊቱ ከመጀመሪያው ሰው ከአባታችን አዳም ጀምሮ ትውልዱን ሁሉ በነፍስ በሥጋ፣ በሕይወት፣ በሞት አገዛዝ አጽንተውባቸው፣ በመከራ ቀንበር አስጨንቀዋቸው ነበርና ቅዱስ ዳዊትና ሌሎች ነቢያት ሁሉ በየዘመናቸው ‹‹እግዚኦ አጽንን ሰማያቲከ ወረድ፤ አብርቅ መባርቅቲከ ወዝርኦሙ…፤አቤቱ በመላእክት አድረህ ርዳኝ፡፡በኃያላኑም በኩርንዐ መዓትህ ውረድባቸው፡፡ አንድም ባሕርየ መላእክትን ሳይሆን ባሕርየ አዳምን ባሕርይ አድርገህ አድነኝ፤ አድነን፡፡ መባርቅተ መዓትን አብዝተህ አምጣባቸው፤ በትናቸውም›› እያሉ የተማጸኑት፡፡ (መዝ.፻፵፫፥፭)
ጸሎቱ ‹‹ውረድ፤ ተወለድ፤ አድነን፤ ወደ ክብራችን መልሰን፤ ያጣናትን ገነት አውርሰን፤ የተገፈፈውን ጸጋችንነወ አልብሰን፤ ጠላት በእኛ ላይ ኃይልና ሥልጣን አያግኝ›› የሚል ነው፡፡ ይህ ሁሉ ጸሎት ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም እንዲመጣ፣ የሲኦል አበጋዞችን አጋንንትን ሁሉ ድል እንዲነሣቸው፣ ሥልጣናቸውን እንዲሽር፣ ከዙፋናቸው እንዲያዋርዳቸው፣ ከክብር እንዲያሳንሳቸው፣ እንዲበትናቸውም፣ ነፍሳትን ነጻ እንዲያወጣ፣ የሰው ልጅ ሁሉ ወደ ቀደመ ሰላሙ እንዲመለስና የመከራ ዘመን እንዲያበቃ የሚሳስብ ነበር፡፡
ስለዚህ ነገር ነቢዩ ኢሳይያስም እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ሰማዮችን ቀደህ ምነው ብትወርድ፥ ተራራዎቹም ምነው ቢናወጡ፥ እሳት ጭራሮውን እንደሚያቃጥል ውኃውንም እንደሚያፈላ ስምህ ለጠላቶችህ ይገለጥ ዘንድ…፡፡›› (ኢሳ.፷፬፥፩)
ነቢዩ ዳዊት፣ ነቢዩ ኢሳይያስም ሆነ ሌሎች ነቢያት ሁሉ ነቢያት ናቸው፤ እረኞች ናቸው፤የሕዝቡ ባለ አደራ ናቸው፤ ስለ ራሳቸው ብቻ ሳይሆን ስለ ሕዝቡ፣ ስለ መንጋው ይጨነቃሉና፤ ያዝናሉና፤ ዘወትር ‹‹እግዚአብሔር አብን እጅህን ላክልን፤ ክንድህን፤ ላክልን›› ይሉታል፡፡እግዚአብሔር ወልድን ና ‹‹ውረድ፤ ተወለድ፤ አድነን፤ ሰማዮችን ቀድደህ ውረድ፤ ተራራ የተባሉ ክፋታቸው፣ ተንኮላቸው፣ እንደ ተራራ የሆነ ኩራታቸው፣ ትዕቢታቸው ከተራራ የገዘፉ አጋንንት ይናወጡ ዘንድ፤ ስምህም ለጠላቶችህ ይገለጥ›› እያሉ ያለ ዕረፍት አሳስበዋል፡፡
እነዚህ አባቶች የራሳቸው ሕይወት ብቻ ሳይሆን የተሾሙለት የተላኩለት ሕዝብ ያሳስባቸዋልና፡፡ ሕዝቡ ተስፋ እንዳይቆርጡ ‹‹እግዚአብሔር ትቶናል፤ አይወርድም፤ አይወለድም፤ አያድነንም፤ ከሲኦል እሳትና ከዲያብሎስ ግዛትም ልንወጣ አንችልም፤ በመቃብር ፈርሰን፣ በሲኦል በስብሰን መቅረታችን ነው›› ብለው ተስፋ እንዳይቆርጡ አብዝተው ይጨነቃሉና፡፡
ቅዱስ ዳዊት ‹‹እጅህን ከአርያም ላክ፤ አድነን›› እያለ ስለ ራሱም ስለ ሕዝቡም አብዝቶ መጸለይ፣ መለመን፣ መማጸን ይገባው ነበርና ይህንን አደረገ፡፡ ምክንያቱም በሕዝቡ ላይ የተሾመ ነቢይ፣ መምህር፣ ንጉሥና አጽናኝ አባትም በመሆኑ ነው፡፡ በራሱም በሕዝቡም ላይ በሥጋ በነፍስ ከሚያስጨንቅ ጠላት ሊያድናቸው የታመነ አምላክ ነውና አብዝቶ ለመነ፡፡
ዛሬም በሕዝቡ ላይ (በመንጋው ላይ) እረኛ፣ አባትና መምህር ሆነው የተሾሙ እረኞችና ጠባቂዎች ሁሉ (ጳጳሳት፣ ካህናት) ዘወትር ስለ ራሳቸውና ስለ መንጋው ‹‹ፈኑ እዴከ እምአርያም ወአድኅነነ፤ እጅህን ከአርያም ላክ፤ አድነን›› በማለት ለጸሎት የሚተጉበት ሰዓት ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹በከንቱ የሚጠሉኝ ከራሴ ጠጉር ይልቅ በዙ፤ በዐመጽ የሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ በረቱ፤ በዚያን ጊዜ ያልቀማሁትን መለስሁ›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ እንደ ራስ ፀጉር የበዙ፣ ለጥላቻቸው ምክንያት የሌላቸው፣ በከንቱ ጥላቻ ሰክረው የተነሡ፣ ያልበላውን፣ ያልቀማውን የሚያስመልሱ፣ የሚያስከፍሉት ብዙዎች ለነፍስም ለሥጋም አደጋ የደቀኑበትና መከራ ያበዙበት ወቅት ስለሆነ ነው፡፡ (መዝ.፷፰፥፬)
አሁንም የእግዚአብሔርን መንጋ ሊያጠፉ፣ በሥጋ ወደ መቃብር፣ በነፍስ ወደ ሲኦል ሊያወርዱ በአስጨናቂነት በሕዝቡ ላይ የተነሡ ብዙዎች በመሆናቸው ‹‹እጅህን ከአርያም ላክ፤ አድነንም፤ እሳት ጭራሮውን እንደሚያቃጥል፣ ውኃውንም እንደሚያፈላው አሸናፊው ስምህ ለጠላቶችህ ይገለጥ›› ብሎ የሚጸልይ አባት የሚያስፈልግበት ወቅትና ዘመን ነው፡፡
ይህ ሱባኤ፣ ዘመነ ነቢያት፣ ወርኃ ጾመ ነቢያት ከመቼውም በላይ አስጨናቂዎቻችን፣ በሥጋ በነፍስ የሚዋጉን፣ አጋንንት ውሉደ አጋንንት፣ ረቂቃኑ አጋንንት፣ ልቡሰ ሥጋ አጋንንት፣ ሁሉ እንደ ጤዛ ረግፈው፣ እንደ ትቢያ ተበትነው፣ ከሕዝበ ክርስቲያንና ከቤተ ክርስቲያን ይርቁ ዘንድ፣ የክርስቶስም መንጋ በሰላም በበረቱ ያድር ዘንድ፣ ‹‹እጅህን ከአርያም ላክ፤ አድነንም›› የምንልበት ጊዜ ነው፡፡
እጁን ይልክልን፣ ያድነንም ዘንድ ፈቃዱ ይሁን አሜን!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!