‹‹ፈለሰት ማርያም እምዘይበሊ ኀበኢይበሊ›› ቅዱስ ያሬድ

 እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ዓለም ፷፬ ዓመታትን በሕይወተ ሥጋ ከቆየች በኋላ ሥጋዋ በምድር እንዲቆይ የአምላክ ፈቃድ አልበነረም፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእናቱን ተድላ ነፍሷን እንጂ ተድላ ሥጋዋን አይወድምና ከጌቴሴማኒ ሥጋዋ ተነጥቆ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር እስከ ነሐሴ ዐሥራ ስድስት ቀን ለሁለት መቶ አምስት ቀናት እንድትቆይ ፈቃዱ አደረገ፡፡ እርሱ ሞትን በሥልጣኑ እንዳሸነፈ ሁሉ በልጇ መለኮታዊ ኃይል ሞትን አሸንፋ ተነስታለች፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ስለፍልሰተ ሥጋዋ «ፈለሰት ማርያም እምዘይበሊ ኀበኢይበሊ፤ ድንግል ማርያም ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ተሻገረች» በማለት ተናግሯል፡፡

ታሪኩ በነገረ ማርያም እንደተመዘገበውም በዚያን ጊዜ ሐዋርያት እመቤታችንን በአጎበር አድርገው ወደጌቴሴማኒ መካነ መቃብር ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ በምቀኝነት ተነሱባት፡፡ «እርሷም እንደ ልጇ ተነሣች፤ ዐረገች እያሉ ሊያውኩን ነውና ኑ የማርያምን ሥጋ በእሳት እናቃጥለው» ተባባሉ፡፡ ከመካከላቸው አንድ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ከሐዋርያት እጅ ለመንጠቅ ዘሎ በመሄድ የአልጋውን ሸንኮር ሲይዝ የታዘዘ መልአክ በረቂቅ ሰይፉ እጆቹን ቆረጠው፡፡ እጆቹም በአልጋው ሸንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ የምሕረት እናት የሆነችው ድንግል ማርያም ቅዱስ ጴጥሮስ ጸልዮ እጆቹን እንዲመልስለት ነግራው እንደነበረ አድርጎለታል፡፡

ከዚያም የእመቤታችን ሥጋዋን መላእክት ከዮሐንስ ወንጌላዊ ጋር በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር ወስደው አስቀመጡት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም ሥጋዋ ያለበትን አይቶ እነርሱ አላዩትም ነበርና እመቤታችን ባረፈች በ፮ኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን እስከ ፲፬ ቀን ድረስ ከጾሙ በኋላ በ፲፬ኛው ቀን ሥጋዋን እንደገና ከጌታ ተቀብለው በጌቴሴማኒ ባለው መቃብር ቀበሩት፡፡

በ፫ኛው ቀንም እመቤታችን ድንግል ማርያም እንደ ልጇ ተነሥታ መላእክት እየዘመሩላት ወደሰማያት ባረገች ጊዜ ሐዋርያው ቶማስ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሰ ዕርገቷን በማየቱ መላእክት «እመቤትህ እርሷ ናት፤ ስገድላት» አሉት፤ እርሱም «ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ ይላል፤ ከደመናው ሊወድቅ ወደደ» ይህም ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ የእርሷን ትንሣኤ ለማየት ብሎ ነው፡፡ እመቤታችንም «ትንሣኤየን ያየህ አንተ ነህ፤ ሌሎቹ አላዩም» ብላ ሐዋርያት ገንዘው የቀበሩበትን የሐር ግምጃ ሰጥታ አጽናንታ ሰደደችው፡፡

ቅዱስ ቶማስ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የእመቤታችን ነገር እንዴት እንደሆነ ጠየቃቸው፤ እነርሱም አግኝተው እንደቀበሯት ነገሩት፤ እርሱም ያየውን ምሥጢር በልቡ ይዞ «ሞት በጥር፤ በነሐሴ መቃብር፤ ለሰሚውም አያምር፤ ይህ እንዴት ይሆናል?» ቢላቸው ቅዱስ ጴጥሮስ መልሶ «ድሮም አንተ ተጠራጣሪ ነህ፤ ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ እንዲሉ፤ ገንዘን የቀበረን እኛ እያለን እንዴት ትጠራጠራለህ» ብለው ወደ መቃብሯ ሄደው መቃብሯን ቢከፍቱት ባዶ ሆኖ አገኙት፡፡ በዚህ ተደናግጠውም ተያዩ፤ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ «አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችን ተነሣች፤ ዐረገች፤ ይኸው ምልክቱ» ብሎ ገንዘው የቀበሩበትን ሰበን አሳያቸው፤ እነርሱም አምነው ሰበኗን ለበረከት ተካፈሉት፡፡

በዓመቱ ነሐሴ ፩ ቀን ሐዋርያት በመንፈሰዊ ቅናት ተነሳስተው «ቶማስ ትንሣኤዋን አይቶ እኛ ሳናይ እንዴት ይቀርብናል» በማለት ነሐሴ ፩ ቀን ሱባኤ ጀምረው በ፲፮ኛው ቀን የሐዋርያትን ሱባኤ ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር ጴጥሮስን ተራዳኢ፣ ካህን እስጢፋኖስን ሠራዔ ዲያቆን አድርጉ ቀድሶ አቅርቧቸዋል፡፡

ቅዱስ ዳዊት ትንሣኤዋን ሲያስረዳ ታቦት የጽላቱ ማደሪያ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ በታቦቱ ውስጥ የሚያድረው በእግዚአብሔር ጣቶች የተጻፈው ሕግ ነው፡፡ እውነተኛዋ የታቦት ማደሪያ ደግሞ እናታችን ድንግል ማርያም ናት፡፡ ሙሴ በተቀበለው ታቦት ውስጥ ያለው ጽላት በውስጡ የያዘው ሕጉን ነው፤ በድንግል ማርያም ላይ ያደረው ግን የሕጉ ባለቤት ነውና፡፡ ከፍጡራን ከፍ ከፍ የማለቷ ድንቅ ምሥጢርም ይህ ነው፡፡ የእመቤታችን ትምክህቷም፣ ትውክልቷም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ወንጌላውያኑ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው መስክረውላታል፡፡ እርሷም ‹‹ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬ፣ በመድኃኒቴ ሐሤትን ታደርጋለች›› በማለት ተናግራለች (ሉቃ.፩፥፵፯)፡፡

ለአምላካችን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና ድንግል ማርያም ከሙታን መካከል ተለይታ ተነሥታለች፡፡ መንፈስ ቅዱስ በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷን በትንቢት እንዳናገረ ትንሣኤዋንም በትንቢት ሲያናግር ኖሯልና ይህ ታላቅ ምሥጢር በቅዱስ ዳዊት አንደበት ‹‹ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦትም›› ተብሎ ተገልጿል፡፡ (መዝ.፻፴፩፥፰)

ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ያሉት ቀናትም ሐዋርያት ሱባኤ ይዘው የጾሙት ጾመ ፍልሰታ በመሆኑ መላው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ይጾሙት ዘንድ ይገባል፤ አምላካችን እግዚአብሔር የጾሙና የትንሣኤዋ በረከት ተካፋይ ያድረገን፤ አሜን