ጾመ ፍልሰታ ለማርያም

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሐምሌ ፳፰፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት ናችሁ? የክረምቱን ወቅት ምን ቁም ነገር እየሠራችሁበት ነው? ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርት እየተማራችሁ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን፤ ከዚሁ ጋር በተጓዳኝ ለቀጣዩ ትምህርት ዘመን ለምትገቡበት ክፍል ከእናንተ ቀደም ያሉትንም በመጠየቅ ከወዲሁ ዝግጅት ልታደርጉ ያስፈልጋል! ትምህርቱን እንዲገልጥላችሁ የማስተዋል ጥበብን እንዲሰጣቸሁ ደግሞ እግዚአብሔርን በጸሎት ልትጠይቁ ይገባል፤ መልካም!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ የምንማረው ስለ ፍልሰታ ጾም ነው፤ አባቶቻችን በሠሩልን ሥርዓት መሠረት ከሰባት ዓመት በላይ የሆኑ ክርስቲያኖች ሁሉ እንዲጾማቸው የታወጁ ሰባት አጽዋማት አሉ፤ ከእነዚህ መካከል ደግሞ አንዱ ሕፃን፣ ወጣቱ፣ አዋቂው ሁሉ በኅብረት የሚጾማት ጾመ ፍልሰታ አንዷ ናት፤ ልጆች! ይህን ጾም ጾመው እንድንጾም ሥርዓቱን የሠሩልን ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ስድሳ አራት ዓመት ከኖረች በኋላ ዐረፈች፤ ከዚያም ቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ይዘው ከጌቴሴማኒ በክብር ለማሳረፍ ሲሄዱ አይሁድ በተንኮል ተነሣስተው መንግድ ላይ በመጠበቅ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለመውሰድ ፈለጉ፤ ከመካከላቸው አንደኛው ታውፋንያ የተባለ የእመቤታችን ክቡር ሥጋ ያለበትን የአልጋውን ሸንኮር (ብረት) በእጁ ያዘ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ እጁን በሰይፍ ቆረጠው፤ በቦታው የነበሩ ሁሉ በሁኔታው ደነገጡ፤ ቅዱሳን መላእክትም የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ እና ወንጌላዊ ዮሐንስን ከዚያ ቦታ ወስደው በኤደን ገነት አሳረፉት፤ ያ በድፍረቱና በንቀቱ የተነሣ እጁ የተቆረጠበት ሰው አዘነ፤ አለቀሰ፤ ተጸጸተ፤ ይቅር ትለውም ዘንድ እመቤታችንን ለመናት፤ ቅዱስ ጴጥሮስም ጸለየለትና ይቅርታን እመቤታችን አደረገችለት፤ የተቆረጠችው እጁ ዳነለት፡፡

ከዚያም ልጆች! ቅዱስ ዮሐንስ ሲመጣ ቅዱሳን ሐዋርያት ስለ ሁኔታው ጠየቁት፤ የእመቤታችን ክቡር ሥጋ ያለበትንም ነገራቸው፤ እነርሱም ነሐሴ አንድ ቀን በጾም በጸሎት ሱባኤ ያዙ፤ በዐሥራ አራተኛው ቀንም ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ሰጣቸውና በክብር በጌቴ ሰማኒ አሳረፉት (ቀበሩ)፤ እመቤታችንም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጇ ሞትን ድል አድርጋ ተነሣች፤ ቅዱሳን መላእክት እያመሰገኑ (እየዘመሩ) ወደ ሰማይ በደመና ስታርግ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ከሕንድ ሀገር ስብከቱ ሲመለስ ተመለከተ፤ እመቤታችንም ቅዱሳን ሐዋርያት የገነዙበትን ሰበን (መቀነት የሚመስል) ለቅዱስ ቶማስ ሰጠችው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ ቶማስም ይህንን ለቅዱሳን ሐዋርያት ነገራቸው፤ የሰጠችውንም ሰበን አሳየቸው፤ እነርሱም ዕርገቷን ማየት ፈልገው እንደገና በዓመቱ ነሐሴ አንድ ቀን ሱባኤ በጾም፣ በጸሎት ያዙ (ገቡ) ከዚያም በዐሥራ ስድስተኛው ቀን ጌታችን ቅዱሳን መላእክትን አስከትሎ ከእመቤታችን ጋር መጣ፤ ስታርግም አሳያቸው፤ በዚህም መሠረት እኛም እመቤታችንን እንድትባርከን፣ ማስተዋል፣ ጥበቡን እንድትገልጥልን፣ የምንፈልገውን መልካም ነገር ሁሉ እንድትፈጽምልን እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ከነሐሴ አንድ ጀምረን እስከ ነሐሴ አሥራ ስድስት ድረስ እንጾማለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በዚህ በፍልሰታ ጾም ጳጳሳት፣ ሊቃውንት አባቶች ካህናት፣ ዲያቆናት ምእመናን ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን በማደር አባታችን አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የደረሰውን ሰዓታት የተባለውን ጸሎት (እግዚአብሔርን እመቤታችንን፣ ቅዱሳንን የሚያወድስ) በመጸለይ ያድራሉ፤ ቀን ደግሞ አባታችን ቅዱስ ኤፍሬም የደረሰውን ውዳሴ ማርያም ትርጉም ይነገራል፤ ከዚያም ቅዳሴ ይቀደሳል፤ በዚህ ወቅት የሚቀደሰው ቅዳሴ አባ ሕርያቆስ የደረሰው ቅዳሴ ማርያም ነው፡፡ ጊዜው ያመቻቸው በሁሉም መንፈሳዊ አገልግሎት በመሳተፍ ይህን የሱባኤ ወቅት ያሳልፋሉ፤ ብዙ ምእመናን ቤታቸው ማደር ትተው ወደ ገዳማት በመሄድ አልያም አቅራቢያቸው ከሚገኝ ቤተ ክርስቲያን በማደር በጾም በጸሎት ይሰነብታሉ፤ እመቤታችንን ይማጸናሉ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ እኛም ከእመቤታችን በረከት ለማግኘት በመጾም በመጸለይ ቤተ ክርስቲያን ሄደን በማስቀደስ በመቁረብ የጾሙን ወቅት ማሳለፍ አለብን፤ ታዲያ ልጆች! ቤተ እግዚአብሔር ስንሄድ በሥርዓት መሆን አለበት፤ በቅዳሴ ጊዜ መረበሽና መጫወት የለብንም፤ በሥርዓት ሆነን ማስቀደስ ይገባናል፤ ቤተ ክርስቲያን ስንሄድም ሆነ ስንመጣም ከታላላቆቻችን ጋር ሆነን፣ የመኪና መንገድ ስንሻገር ተጠንቅቀን በማስተዋል ይሁን!

እንግዲህ ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! መልካም የሱባኤ ጊዜ ይሁንላችሁ! እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከቷንና ረድኤቷን ታድለን አሜን! ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ጥር ፳፩ እና ነሐሴ ፲፮፣ ተአምረ ማርያም (በእንተ ዕርገተ ሥጋሃ፤ ሰባተኛ ተአምር)