filseta.gif

ጾመ ፍልሰታን እንዴት እናክብር?

 በሕይወተ ሥጋ ሳለን ካልጾምንና ካልጸለይን ነፍሳችን ልትለመልም አትችልም፡፡ በጾም በጸሎት ዲያብሎስን፣ ዓለምንና ፍትወታት እኩያትን ድል መንሣት ይቻላል፡፡ እንደዚሁም በጾም አማካኝነት መንፈሳዊ ሕይወትን ማሳደግ ይቻላል፡፡

filseta.gif

ውድ አንባቢያን ለመግቢያ ያህል ስለጾም ይህን ያህል አልን እንጂ ጾም በራሱ ምንድን ነው? ለምንስ ይጾማል? ምንስ ጥቅም ያስገኛል? ባንጾምስ ምን ጉዳት አለው? የሚሉትን በአጭር በአጭሩ ከገለጽን በኋላ በዋናነት ስለተነሣንበት ዐቢይ ርእስ ስለ ፍልሰታ ጾም በስፋት ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

 

የፍልሰታ ጾም ከሰባቱ አጽዋማት አንዷ ነች፡፡ በደመቀና በተለየ ሁኔታ የምትጾምበት ምክንያት ምን እንደሆነና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች በማንሳት የቤተ ክርስቲያንን ሊቃውንት መልስ ጭምር ይዘን ቀርበናል መልካም ንባብ፡፡

«ጾም» ማለት «ጾመ»  ተወ፣ ታቀበ፣ ታረመ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲሆን የቃሉ ትርጉም ደግሞ ምግብ መተው፣ መከልከልና መጠበቅ ማለት ነው ሲሉ ዲያቆን ቃኘው ወልዴ በ1995 ዓ.ም «ጾምና ምጽዋት» በሚለው መጽሐፋቸው በገጽ 8  ላይ ገልጸውታል፡፡ የኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላትም የሚያመለክተው ይህንኑ ነው፡፡

ጾም ጥሉላት መባልዕትን ፈጽሞ መተው፤ ሰውነትን ከመብልና ከመጠጥ እንዲሁም ከሌላውም ክፉ ነገር ሁሉ መጠበቅ፣ መግዛት፣ መቆጣጠር፣ በንስሐ ታጥቦ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መቅረብና እርሱንም ደጅ መጥናት ነው፡፡ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር ደጉ ዓለም ካሣ እና ቀሲስ ስንታየሁ አባተም የሚገልጹት ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡

«መላው ሕዋሳታችን ካልጾሙ የምግብና መጠጥ ጾም ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ መጽሐፉም የሚለው «ወደ አፍ የሚገባ ሰውን አያረክስም፤ ከአፍ የሚወጣ እንጂ፡፡» ስለዚህ ዐይን፣ ጆሮ፣ እግርና እጅ የመሳሰሉት የስሜት ሕዋሳታችን መጾም አለባቸው፡፡ ከምግብና መጠጥ ይልቅ የሚበልጡት እነዚህ ናቸው፡፡ ከምግብና መጠጥ የምንቆጠበው በራሱ ኃጢአት ስለሆነ ሳይሆን ምግብና መጠጥ ሥጋን አጥግቦ በገደል ስለሚጥል ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ስለሚጎትት እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡ በዋናነት ስንጾም ከሐሜት፣ ከአሉባልታ፣ ከዝሙትና በሐሰት ከመመስከር ወዘተ መቆጠብ አለብን» ሲሉ መምህር ደጉ አመልክተዋል፡፡

የጾም መሠረቱ ሃይማኖት ነው፡፡ በሃይማኖት የተነሣ ለተወሰኑ ጊዜያት ከምግብና ከመጠጥ የምንከለከልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ጾም ይህ ብቻ አይደለም፤ ሁለት ዓይነት መስመር አለው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአጽዋማት ወቅት ከምግበ ሥጋና ከኃጢአት ትከለክላለች፡፡ ከኃጢአት ሁልጊዜ እንከላከላለን፡፡ ከምግብ የምንከለከለው ምግብ ኃጢአት ስለሆነ ሳይሆን ከሃይማኖት የተነሣ ነው፡፡ ምግብ በልተን ፍቃደ ሥጋችንን ከምናደልብ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ሥጋችንን ጎስመን ከሞት በኋላ ከሰማይ የሚኖረን ሕይወት ያለምግብና መጠጥ በምስጋና እያመሰገንን የምንኖርበትን ሕይወት የምናስብብት ነው ያሉት ደግሞ ቀሲስ ስንታየሁ አባተ ናቸው፡፡

«ኃጢአትን ደግሞ ስንጠመቅ ለኃጢአት ሞተን፣ ለጽድቅ የተነሣን ስለሆንን ሁልጊዜ ኃጢአትን ትተን በንጽሕና፣ በቅድስና የምንኖርበት ሁኔታ ነው፡፡ ነገር ግን ከዕውቀት ጉድለት የተነሣ ሥጋዊን ምግብ ብቻ አንዳንድ ሰዎች ሊተውት ይችላሉ፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት አይደለም፡፡ ዋጋ እንዲኖረን /እንድናገኝ/ ኃጢአቱን፣ ቂም በቀሉን፣ ክፋቱን፣ ማንኛውንም በእኛ ላይ እንዲደረግብን የማንፈልገውን ነገር ሌሎች ላይ ማድረግን ትተን ምግብን ለተወሰነ ሰዓት እንጾማለን» በማለት ቀሲስ ስንታየሁ አክለው ተናግረዋል፡፡

ጾም የግልና የዐዋጅ /የሕግ/ ጾም በመባል ይከፈላል፡፡ የግል ጾም የንስሐና የፈቃድ ጾም ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ የዐዋጅ /የሕግ/ ጾም በሰባት የሚከፈል ሲሆን እነዚህም ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት /የሰኔ ጾም/፣ ጾመ ነቢያት /የገና ጾም/፣ ጾመ ገሃድ፣ ጾመ ነነዌ፣ ጾመ ረቡዕና ዓርብ እና ጾመ ፍልሰታ ናቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ መነሻም ከሰባቱ አንዱ በሆነችው ጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የፍልሰታ ጾም ስለሆነ ነው፡፡

ፍልሰታን ከሌሎቹ አጽዋማት ሁሉ ልዩ የሚያደርጋት ምን እንደሆነ እናያለን፡፡ የፍልሰታን ጾም ሕፃን አዋቂው ሳይቀር በልዩ ሥነ ሥርዓትና በደመቀ ሁኔታ ይከናወናል፡፡ አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኞችና በግል የሥራ መስክ የተሰማሩ ሁሉ የዕረፍት ጊዜ በመውሰድ በገዳማትና በየአብያተ ክርስቲያናት ሱባኤ በመግባት ከነሐሴ አንድ ጀምሮ እስከ አሥራ ስድስት ቀን ድረስ ጾም ጸሎት በማድረግ ይቆያሉ፡፡ ጾም ጸሎት ሲያደርጉ ደግሞ በድሎት ሳይሆን በየዋሻው፣ በየመቃብር ቤቱና አብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ እንጨት ረብርበውና ሳር ጎዝጉዘው ጥሬ እየበሉ ነው፡፡

ፍልሰታ ምን ማለት ነው? በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር ደጉ ዓለም መልስ አላቸው፡፡ «ፍልሰታ ማለት ፈለሰ፣ ተሰደደ ከሚለው ግስ የወጣ ነው፡፡ ፈለሰ ማለት ደግሞ የተለያየ ትርጉም ቢሰጠውም ፍልሰታ ለማርያም ብሎ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሚያልፈው ወደ ማያልፈው ዓለም ከመቃብር የወጣችበት /የተነሣችበት/ ቀን ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ከሥጋዊው ዓለም ወደ መንፈሳዊው ዓለም የተሸጋገረችበት ነው፡፡»

በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርት ክፍል ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙት ቀሲስ ስንታየሁ አባተ በበኩላቸው «ፍልሰታ ለማርያም የሚለው የግእዝ ቃል ሲሆን ፍልሰታ ማለት ደግሞ ፈለሰ ከሚል ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ፈለሰ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሔድን /መፍለስን/ ያመለክታል፡፡ ይኸውም እመቤታችን በሐዋርያት ዘመን ካረፈች በኋላ የሥጋዋን መፍለስ አስመልክቶ ሐዋርያት የእመቤታችን ሥጋ የት እንደተቀበረ አላወቁም ነበርና እግዚአብሔር ያንን እንዲገልጥላቸው ስለ እመቤታችን ዕረፍት አስመልክቶ የጾሙት ጾም ነው፡፡ ሐዋርያት ሁለት ሱባኤ ጾመው የእመቤታችንን ሥጋዋን ሰጥቷቸው ትንሣኤዋን፣ ዕርገቷን ያዩበት ሁኔታ ስለነበርና በረከት ያገኙበት ጾም ነው፡፡ ስለሆነም ምእመናን ፍልሰታ ለማርያምን ከልጅ እስከ አዋቂው በጾም በጸሎትና በመቁረብ በጋራ በፍቅር፣ በሰላም ያሳልፉታል፡፡»

መምህር ደጉ ዓለም ካሣ እንዳብራሩት ከሆነ ቅዱስ ዮሐንስ እመቤታችንን እንዲጠብቃት ከተደረገ በኋላ ሐዋርያት የእመቤታችን ነገር እንዴት ነው? ብለው በጠየቁት ጊዜ «እመቤታችንማ በገነት በዕጸ ሕይወት ሥር ናት» ሎ ነገራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሐዋርያት እመቤታችን ከመቃብር መነሣቷንና ማረጓን ማየት አለብን፤ እንዴት ዮሐንስ ዐይቶ እኛ ሳናይ እንቀራለን ብለው በመንፈሳዊ ቅናት በመነሳሳት ነሐሴ አንድ ቀን በዕለተ ሰኞ ሁለት ሰባት ሱባኤ ያዙ፡፡ በ14ኛው ቀን ጌታችን የእመቤታችንን ሥጋ አንሥቶ ሰጣቸውና በጌቴ ሴማኒ ቀበሯት፡፡ እመቤታችን በ64 ዓመቷ ጥር 21 ቀን ዐርፋ ነሐሴ 14 ቀን ልትቀበር ችላለች፡፡

ይሁንና ሐዋርያት ቢቀብሯትም መነሣቷ ዕርገቷን አላዩም ነበር፡፡ መነሣቷን ዕርገት ያየው ነገር ግን ሲቀብሯት ያላየው ትውልዱ ከሰዶቃዊ የሆነ ቶማስ ነው፡፡ ቶማስ እንዲያስተምር ሕንድ ሀገር ዕጣ ደርሶት አስተምሮ በደመና ሲመለስ ነሐሴ 16 ቀን እመቤታችን ስታርግ በሕዋ ላይ ተገናኙ በማለት መ/ር ደጉ አስረድተዋል፡፡ እንደ መምህር ደጉ ገለጻ የፍልሰታ ጾም የሚጾመው ልክ ሐዋርያት ሁለት ሰባት ሱባኤ ይዘው ለ14 ቀን የሚጾም ቢሆንም አባቶቻችን ግን እመቤታችን የተነሣችበትንና ያረገችበትንም በማሰብ እስከ 16 ቀን እንዲጾም ተደርጎ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ምእመናንም ይህንኑ መሠረት በማድረግ በየዓመቱ ሕፃን አዋቂው ሳይቀር የእመቤታችን ፍቅር አድሮባቸው ይጾማሉ፣ ያስቀድሳሉ፤ ይቆርባሉ፡፡

የፍልሰታን ጾም ሕፃን አዋቂው ይጾመዋል ከሌሎቹ አጽዋማት ሁሉ የተለየ የሚያደርገው ምስጢሩ ምን ይሆን? የሚል ነበርና ለዚህም መምህር ደጉ ዓለም ካሣ መልስ አላቸው፡፡ «ኢትዮጵያ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የአሥራት ሀገር በመሆኗና ለእመቤታችን ልዩ ፍቅር ስላላቸው ምእመናን መሬት ላይ እየተኙና ጥሬ እየበሉ በሰላም በፍቅር ይጾሙታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ፍልሰታን ሳይጨምር ትልቅ ጾም የሚባሉት ዐቢይ ጾም፣ ነነዌ፣ ገሃድ/ጋድ/፣ ረቡዕና ዓርብ እና አጽዋማት ናቸው፡፡ ምእመናን ግን ፍልሰታን ከእነዚህ አስበልጠው መሬት ላይ እየተኙ ይጾሙታል፡፡ ይህ ደግሞ የእመቤታችን ፍቅር ስቧቸውና ኢትዮጵያም በእመቤታችን ፍቅር የተነደፈ ክርስቲያን ያለባት ሀገር በመሆኗ ነው፡፡»

ቀሲስ ስንታየሁ አባተ እንደዚሁ የተናገሩት ይህንኑ አባባል የሚያጠናክርና የሚያጎላ ነው፡፡ እንደሳቸው አባባል «በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የፍልሰታ ጾም ልዩ ስፍራ አለው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለእመቤታችን ያላቸው ፍቅር የተለየ ነው፡፡ ይህም ከእመቤታችን ጋር ያለን ትስስር ሲሆን ኢትዮጵያ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የአሥራት ሀገር ናት፡፡ እመቤታችን በስደቷ ጊዜ ልጇ ወዳጇን መድኃኔዓለምን ይዛ በተሰደደችበት ሰዓት ያረፈችው በግብፅ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ምድርም መጥታ ዐርፋለች፡፡ በዚህ ጊዜ አራቱንም የሀገሪቱን መዓዘን ባርካለች፡፡

በዚህም ሊቃውንቱ እንደሚያስተምሩ ነቢዩ እንባቆም «የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ» ብሎ ተናግሮ የነበረው ትንቢት እመቤታችን ልጇን ይዛ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችበት ዘመን እንደተፈጸመ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ሥርዓት አድርገን ፍልሰታን በልዩ ሁኔታ እንጾማለን» ነበር ያሉት፡፡

ድርሳነ ዑራኤል የሚለው መጽሐፍ በመግለጫው ላይ የተሰጠውን ሐሳብ ያጠናክራል፡፡ «እመቤታችን ድንግል ማርያም በስደቷ ወራት ልጇን ሕፃኑ ኢየሱስን ይዛ ከምድረ እስራኤል ወደ ምድረ ግብ ከዚያም ወደ ብሔረ ኢትዮጵያ መጥታ በቅዱስ ዑራኤል መሪነት በደብረ ዳሞ በትግራይ፣ በጎንደር፣ በአክሱም፣ በደብረ ዐባይ፣ በጎጃምና በጣና በአደረገችው የስደት ጉዞ ሕፃኑ ኢየሱስ ለድንግል እናቱ ኢትዮጵያን ዓሥራት አድርጌ ሰጥቼሻለሁ» በማለት በሸዋና በወሎ፣ በሐረርጌና በአርሲ፣ በሲዳማና በባሌ፣ በከፋና በኢሉባቦር፣ በወለጋና በሌሎችም በኢትዮጵያ ክፍላተ አኅጉር በብሩህ ደመና ተጭነው በአየር እየተዘዋወሩ ተራራውንና ወንዙን /አፍላጋቱን/ እንዳስጎበኛት ይኸው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅቱ የፍልሰታ ጾም የሚጀምርበት በመሆኑ ምእመናን ምን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው? ከገቡስ በኋላ ምን ነገር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል? የሚለው ከጥያቄዎቻችን መካከል አንዱ ነበር፡፡ መምህር ደጉ ዓለም እንዲህ በማለት አመልክተዋል፡፡ “ምእመናን ጾም /ሱባኤ/ ከመግባታቸው በፊት የሥጋን ኮተት ሁሉ አስወግደው መግባት አለባቸው፡፡ ሐሳባቸው ሁሉ ወደተለያየ አቅጣጫ ሳይከፋፈል ልቡናቸውን ሰብስበው ለአንድ እምነት መቆም፣ ከሱባኤ የሚያቋርጣቸውን አስቀድሞ ማጠናቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ከገቡም በኋላ ሥጋቸውን ማድከም፣ በጾም በጸሎት መጠመድ አለባቸው፡፡

ከዚህም ባሻገር እንደተሰጣቸው ጸጋ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ተገቢ ነው፡፡ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ገንዘብ ያለው ደካሞችን በመርዳት፣ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ፣ አቅሙ የደከመና መርዳት የማይችል ደግሞ በምክርና ሐሳብ በማበርከት የበኩሉን ድርሻ ይወጣ፡፡ ብዙ ከመብላት ጥቂትን፣ ብዙ የሚያሰክር ጠጥቶ ከመንገዳገድ ውኃን ብቻ በመጎንጨት ለቁመተ ሥጋ የሚያበቃቸውን እያደረጉ ፈጣሪያቸውን ይጠይቁ፡፡ አለባበስን በተመለከተ ደግሞ አግባብና ወግ ያለው አለባበስ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከሌላው የተለየና የሌሎችን ቀልብ የሚስብ  ልብስ መሆን የለበትም፡፡”

ቀሲስ ስንታየሁ አባተ የተናገሩትም ከመምህር ደጉ የተለየ አይደለም፤ የእሳቸውን ሐሳብ የሚጋራ እንጂ፡፡ «እኛ የምንጾመው የወገኖቻችንን፣ በአጠቃላይ የሰውን ልጅ ጥፋት አታሳየን ብሎ ቦታና ጊዜ ወስኖ ሱባኤ የምንይዝበት ነው፡፡ ጾም ማለት ለእግዚአብሔር ማመልከቻ ማስገባት ማለት ነው፡፡ የነነዌ ሰዎች ሦስት ቀን ጾሙ፣ በሦስት ቀናት ውስጥ ሀገራቸው ከመከራ ዳነች፡፡ እኛ በገዳማት ውስጥ ከ250 ቀናት በላይ እንጾማለን፡፡ ነገር ግን ስንጾም ማየት የሚገቡን ነገር አለ፡፡ «ፍቅር እንደሸማ ያላብስህ» እንደሚባለው ስንጾም ፍቅር ሊኖረን ይገባል፡፡ ጾም ያለ ፍቅር፤ ፍቅር ያለ ጾም ዋጋ የለውም፡፡ ቁም ነገሩ እኛ በጾም ደርቆ መዋል ሳይሆን ፍቅርና ሰላም መታከል አለበት፡፡ የተጣላ መታረቅ አለበት፣ በቅዳሴ ሰዓት ቦታ ላጡ ቦታ መስጠት፣ አቅመ ደካሞችን መርዳት፣ በተለይ አረጋውያንንና ሕፃናትን መደገፍ የወጣቶች ድርሻ ነው፡፡ በቅዳሴ ሰዓት የበረታው ለደከመው ቦታ መልቀቅ ይኖርበታል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሐሜትና ሁካታ ቂም በቀል ቦታ ሊኖረው አይገባም” በማለት ተናግረዋል፡፡

እንደ ቀሲስ ስንታየሁ ገለጻ ጾም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ከሆነ ለምንድን ነው በጾማችን፣ በጸሎታችን ኅብረተሰባችን ከጉስቁልና ያልወጣው? ብለን ብንጠይቅ ሳይጾም ሳይጸለይ ቀርቶ ሳይሆን ፍቅር ስለሌለ ነው፤ እንጂ እግዚአብሔር ሳይሰማ ቀርቶ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ፊትም አሁንም ሆነ ወደፊት ይሰማል፡፡

በመጨረሻ ለመምህር ደጉ ዓለምና ለቀሲስ ስንታየሁ አባተ ያነሳንላቸው ጥያቄ አንዳንድ ሰዎች ታመው ከሕመማቸው እንዲፈወሱ፣ ስለ ማኅበራዊ ጉዳይ ሱባኤ በመግባት ራእይ ማየት አለብኝ ይላሉ፡፡ ራእይ ያላዩ ተስፋ እንዳይቆርጡ ምን ትመክራላችሁ? የሚል ነበር፡፡ መምህር ደጉ «ምንም እንኳን ወሩ ከሌላው በተለየ የሱባኤና የራእይ ወቅት ሆኖ ቢገለጽም በፍልሰታ ጾም ራእይ ማየት አለማየት የሚለው የብቃት መለኪያ /ማረጋገጫ/ መሆን የለበትም፡፡ ቦታ ቀይረውና ከሰው ተለይተው በጾም በጸሎት መጠየቅ ታዝዟል፡፡ ኢትዮጵያን ምእመናን ወደ ውሳኔ ከመድረሳቸው በፊት ፈቃደ እግዚአብሔርን እንጠይቅ ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ካልተሳካላቸው በተለያየ ጊዜ በሱባኤው ይቀጥላሉ እንጂ ተስፋ መቁረጥ የለባቸው» ሲሉ መክረዋል፡፡

ቀሲስ ስንታየሁ በበኩላቸው «አንድ ሰው የሚጾመው ራዕይ ልይ ብሎ አይደለም፡፡ ይህ እግዚአብሔር በፈቀ የሚታይ ነገር ነው፡፡ አባቶቻችን ሲጾሙ ሲጸልዩ ኃጢአታቸው እንዲገለጽላቸው እንጂ እግዚአብሔር እንዲገልጽላቸው አይደለም፡፡ አንተ ኃጢያትህ ከተገለጸልህና ንስሐ ከገባህ እግዚአብሔርን ታየዋለህ፡፡ አንድ ሰው በኃጢአት ተሞልቶ እግዚአብሔርን ልይ ቢል ሊሆን አይችልም፡፡ እኛንና እግዚአብሔርን የሚለያየን ኃጢአትና በደል ነው፡፡ ስለዚህ የሚያራርቀንን ነገር ለማስወገድ መጾም አለብን፡፡ ምእመናን በሕይወታቸው ውስጥ ስላለው ችግር፣ ለሰው ልጅና ለሀገር የሚበጅ ነገር አምጣልን ብለው ሱባኤ በመያዝ መጾም መጸለይ የሚገባ ነው» በማለት መንፈሳዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ጽሑፋችንን ለማጠቃለል ያህል ምእመናን በሚጾሙበት ወቅት የተራቡትንና የታረዙትን በማሰብ ካላቸው ላይ ከፍለው ማብላትና ማልበስ ተገቢ ነው፡፡ ምእመናን ይህን የሚያደርጉት በፍልሰታ ወይም በሌሎችም አጽዋማት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሌላም ጊዜ እንደሆነ ያነጋገርናቸው እንግዶች አስረግጠው የተናገሩት፡፡ መርዳት መረዳዳት የኢትዮጵያዊነት ባህል ብቻ ሳይሆን የሃይማኖታችን መንፈሳዊ ግዴታችን ነው እያልን ጾሙን በሰላም በፍቅር አስጀምሮ እስከሚያስፈጽመን ድረስ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን አሜን፡፡  

                                                              ወስብሐት ለእግዚአብሔር