ጾመ ማርያም ለቤተ ክርስቲያን ሰላም

በዝግጅት ክፍሉ

ነሐሴ ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ነቢያት የተነበዩትን ትንቢት፣ የቈጠሩትን ሱባዔ መሠረት በማድረግ ቅድስት ድንግል ማርያም በኪደተ እግሯ ኢትዮጵያን መባረኳን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ድኳኖች ሲጨነቁ አየሁ፤» (ዕንባ. ፫፥፯) በማለት ነቢዩ ዕንባቆም የተናገረው ቃለ ትንቢት እመቤታችን የኢትዮጵያን አውራጃዎች ለመባረኳ ማስረጃ መኾኑንም ሊቃውንቱ ያስረዳሉ፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን ለእናቱ ዐሥራት አድርጐ በመስጠቱ፣ ከዅሉም በላይ ክርስቶስ ከእርሷ በለበሰው ሥጋ አማካይነት የመዳናችን ምሥጢር በመከናወኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልዩ ፍቅር አለን፡፡

የአብነት ተማሪዎች በትምህርት ዓለም ከአንዱ ወደ ሌላ አገር እየተዘዋወሩ የአብነት ትምህርት ሲማሩ ‹‹በእንተ ስማ ለማርያም›› (ስለ ማርያም ስም) እያሉ ነው፡፡ ተማሪዎቹ የእመቤታችን ስም ስንቅ ምግብ ኾኗቸው ይጠቀሙበታል፡፡ የልጇ ግማደ መስቀል ወደ ከተመበት ግሼን ደብረ ከርቤ አምባ የሚጓዙ ምእመናንም ‹‹አንድ እፍኝ ሽምብራ አልያዝኩም ከቤቴ ስሟ ስንቅ ነው የእመቤቴ›› እያሉ በፍቅሯ ተማርከው ግብር ሰፍረው ዕጣን ቋጥረው ሱባዔ እየገቡ ይማጸኗታል፡፡ እርሷም ከልጇ ዘንድ ባገኘችው የአማላጅነት ጸጋ ምልጃቸውን በመቀበል ጸሎታችውን በማሳረግ የእናትነት ሥራዋን ስትፈጽምላቸው ኖራለች፡፡ ዛሬም እየሠራች ነው፤ ወደፊትም አማላጅነቷ አይቋጥም፡፡ እመቤታችን ከልጇ ያገኘችውን (የተቀበለችውን) ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ በአራቱ ማዕዘን ‹‹ሰአሊ ለነ ቅድስት፤ ቅድስት ሆይ ለምኝልን›› የማይላት ክርስቲያን የለም፡፡

በፍቅሯ ተደስተው በአማላጅነቷ ተማምነው ‹‹የእመቤቴ ፍቅሯ እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ምድር አሸዋ በዝቶልኝ፣ እንደ ልብስ ለብሼው፣ እንደ ምግብ ተመግቤው›› እያሉ ተማጽነው ልመናቸው ሠምሮ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊው፣ ቅዱስ ያሬድ ዘኢትዮጵያና አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ አባ ጽጌ ድንግል ያዘጋጁላትን፤ የደረሱላትን የምስጋና መጻሕፍት በመድገም እመቤታችንን ዘወትር መማጸን የቀደምቱም ኾነ የዛሬዎቹ ገዳማውያንና ምእመናን ዕለታዊ ተግባር ነው፡፡ ጌታችን ለቀደሙት ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችን አማላጅ እና እናት እንድትኾናቸው በገቢርም በነቢብም ከአደራ ቃል ጋር እናቱን አስረክቧቸዋል፡፡ በገቢር በቃና ዘገሊላ የሰውን ችግር ፈጥና የምትረዳ ርኅርኅት እናት አማላጅ መኾኗን አሳይቷል፡፡ ለዚሁም ‹‹የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል›› ብላ ያቀረበችው ቃለ ምልጃ ማስረጃ ነው፡፡ ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ከእግረ መስቀሉ ሥር የነበረውን ቅዱስ ዮሐንስን ጠርቶ ‹‹እነኋት እናትህ፤›› ድንግል ማርያምን ደግሞ ‹‹እነሆ ልጅሽ፤›› በማለት ለቅዱሳን ሐዋርያትም ለእኛ ለምእመናንም እመቤታችንን በእናትነት ሰጥቶናል (ዮሐ. ፲፱፥፳፮)፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችንን በእናትነት ከተረከቧት ጊዜ ጀምረው ልጇ በዕርገት በአካለ ሥጋ ሲለይ በቤታቸው አኑረው እንደ ልጅ አገልግለዋታል፡፡ እርሷም የእናትነት ሥራዋን ሠርታላቸዋለች፡፡ በምድር የነበራት ቆይታ ሲፈጸምም ልጇ በአዳምና በልጆቹ ኃጢአት ምክንያት የፈረደውን፣ ለራሱም ያላስቀረውን ሥጋዊ ሞት እናቱ እንድትቀምስ አደረገ፡፡ በእናትነት የተረከቧት ቅዱሳን ሐዋርያትም መካነ ዕረፍት ለይተው በንጹሕ በፍታ ከፍነው በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡ የእመቤታችን ሥጋዊ ዕረፍቷና የትንሣኤዋ ምሥጢር ከመ ትንሣኤ ወልዳ (እንደ ልጇ ትንሣኤ) ነውና ሙስና መቃብር ሳያገኛት ከሦስት ቀናት ሥጋዊ ዕረፍት በኋላ ከሞት ተነሥታ ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ስታርግ በዕለተ ቀብሯ ያልተገኘው ቅዱስ  ቶማስ ደመና ጠቅሶ በደመና ሠረገላ ሲመጣ ዕርገቷን ይረዳል፡፡ ለማስረጃነትም የተከፈነችበትን በፍታ (ጨርቅ) ይቀበላታል፡፡ ለቅዱስ ቶማስ የተገለጠው የዕረፍቷ ምሥጢር ለእነርሱም እንዲገለጥላቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ቢማጸኑ እመቤታችን ዳግም ተገልጻላቸው ትንሣኤዋን ለማየት በቅተዋል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችንን በሁለት ሱባዔ ማግኘታቸውን መሠረት በማድረግ በየዓመቱ ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን የፍልሰታን ጾም እንድንጾም በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ተወስኗል፡፡ ይህ እመቤታችንን የምንማጸንበት ጾመ ፍልሰታ ቤተ ክርስቲያናችን መፍትሔ የምትፈልግባቸውን ጉዳዮች ለእመቤታችን የምታቀርብበት የጸሎት ወቅት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለሚገጥማት ችግር መፍትሔው ከእመቤታችን እጅ ላይ አለ ብለን እናምናለን፡፡ አባቶች ሱባዔ ገብተው እመቤታችንን እንደሚያገኟ ዅሉ፣ እርሷ የፍቅር እናት ናትና ፍቅርን አንድነትን እንድትሰጠን፤ የዶኪማስን ጓዳ እንደሞላች የጐደለውን ሕይወታችንን እንድትሞላልን ውዳሴዋን እየደገምን ድንግል ማርያምን መማጸን ያስፈልጋል፡፡

በውዳሴ ማርያም፣ በጸሎተ ማርያም የሚመካ በጕልበቱ አይመካም፡፡ ጊዜ ረዳኝ ብሎ በወገኖቹ ላይ ግፍን አይፈጽምም፡፡ ስለዚህ በእነዚህ የጾም ሳምንታት የእመቤታችን አማላጅቷ እና ጸጋዋ በአገራችን፣ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እንዲያድር በሱባዔ እንማጸናት፡፡ የሁለቱ ሳምንታት ሱባዔ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር እየተገኘን ምሕላ የምናደርስበት፣ የተጣላነውን ይቅር ለእግዚአብሔር የምንልበት፣ የበደልነውን የምንክስበት፣ ሥጋውንና ደሙን የምንቀበልበት ወቅት መኾን አለበት፡፡ ነገር ግን ቀናቱን እየቈጠርን እስከተወሰነው ሰዓት ብቻ መጾም ብቻ በሕይወታችን መሠረታዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ ከዚህ ላይ ማስተዋል የሚገባን ሌላው ቁም ነገር በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ሱባዔ ገብተን ውዳሴ ማርያም በደገምንበት አፋችን ሰው የምናማ፣ በሰው ሕይወት ገብተን የምንፈተፍት ከኾነ እመቤታችንን አናውቃትም፤ እርሷም አታውቀንም፡፡ እናም ‹‹መክፈልት ሲሹ መቅሠፍት›› እንደሚባለው በረከት ማግኘት ሲገባን መቅሠፍት እንዳይደርስብን ዅሉንም በሥርዓቱና በአግባቡ ልናከናውን ያስፈልጋል፡፡

በጾመ ፍልሰታም ኾነ በሌላ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን የሚደረሰው ውዳሴ ማርያሙ፣ ሰዓታቱ፣ ቅዳሴው ከጠላት ሰይጣን ተንኮል የሚያድን፣ ከጥፋት የሚጠብቅ መንፈሳዊ የሰላም መሣርያ ነውና በጸሎቱ እንጠቀምበት፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚተጉ አባቶች እና ምእመናን በዚህ የእመቤታችንን ጾም ወቅት ለተሰደዱ፣ ለተራቡ፣ በፈተና ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ይጸልያሉ፤ ይማጸናሉ፡፡ እኛም ለእነርሱና ለሌችም ነዳያን ጸበል ጸሪቅ በማቅመስ ከበረከታቸው እንካፈል፡፡ በአጠቃላይ መንፈሳዊነት፣ እውነት፣ ቅድስና፣ ሕጋዊ አሠራር በቤተ ክርስቲያን እንዲሰፍን ዅላችንም በዚህ በጾመ ፍልሰታ ሱባዔ ተግተን ልንጸልይ ይገባል፡፡

                                                             ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡