ጰራቅሊጦስ ከሣቴ ምሥጢር

ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በመምህር ማዕበል ፈጠነ

ጰራቅሊጦስ ማለት ከሣቴ ምሥጢር ማለት ነው፡፡ ይኸውም በግብሩ ታውቋል፡፡ በበዓለ ጰራቅሊጦስ አበው ሐዋርያት ብዙ ምሥጢር በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው ብሉይና ሐዲስን ተርጕመዋል፡፡

ማለትም ወደ ኋላ ተመልሰው *እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በመጨረሻው ቀን ሥጋ በለበሰ ኹሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፡፡ ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤* ተብሎ የተነገረውን ትንቢት ጠቅሰው፣ በመብረቅ መጽሔት ተሞልተው ወደ ፊት የሰው ልጅ በሃይማኖትና በምግባር የሚወርሳትን የመንግሥተ ሰማይን ተስፋ አብሥረዋል /ሐዋ.፪፥፲፯፤ ኢዩ.፪፥፲፰/፡፡

ከቀደመው ቋንቋቸው ሌላ ፸፩ ቋንቋ ተገልጾላቸው በ፸፪ ቋንቋ አስተምረዋል፡፡ ይህ ሲባል ግን በዘመኑ የነበረው ሕዝብ እርስበርስ ይግባባቸው የነበሩት ቋንቋዎች ፸፪ ስለ ነበሩ ነው እንጂ መንፈስ ቅዱስ ከዚህም በላይ ቋንቋዎችንና ጥበብን መግለጽ እንደሚቻለው ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ጥንተ ነገሩስ እንደምን ነው ቢሉ ጌታችን በዚህ ዓለም ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌለ መንግሥትን አስተምሮ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ፣ በሲኦል የነበሩ ነፍሳተ ሙታንን ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ አውጥቶ የሲኦልን በር ዘግቷል፡፡

በዚህ ዓለም ደግሞ ብርሃነ መለኮቱን ገልጾ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ፵ ቀን ለአበው ሐዋርያት በመጽሐፈ ኪዳን የተገለጹ ረቂቅ ምሥጢራትን አስተምሮ መንፈስ ቅዱስ ትርጕሙን እንደሚነግራቸው፤ በሰዓቱ ግን መሸከም እንደማይችሉ ነግሯቸው ባረገ በ፲ኛው ቀን ለ፲፪ቱ ሐዋርያት፣ ለ፸፪ቱ አርድእትና ለ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት በአጠቃላይ ለ፻፳ው ቤተሰብ መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ በአዲስ ልሳን መናገር ጀምረዋል፡፡

አዲስ ልሳን ሲባልም በዓለም የሌለ ሌላ ባዕድ ቋንቋ ማለት አይደለም፡፡ የዓለም ቋንቋዎች ኹሉ በመንፈስ ቅዱስ እሳትነት በሐዋርያት አንደበት ተዋሐዱ፤ በልቦናቸው አደሩ፤ ሐዋርያት በዕውቀት ታነፁ ማለት ነው እንጂ፡፡ እንደሚታውቀው የሰው ልጅ የዓለማትን ቋንቋ በሙሉ ተምሮ ለማወቅ አይቻለዉም፡፡ አበው ሐዋርያት ግን ከሥጋዊ፣ ከደማዊ መምህር በመማር፤ መልክአ ፊደል በማጥናት ሳይኾን፣ መንፈስ ቅዱስ ገልጾላቸው አንደበታቸው ሰይፍ፣ ልሳናቸው ርቱዕ፣ ኾኖ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች መናገር ችለዋል፡፡

ነገር ግን ሐዋርያት ባዕድ ቋንቋ አላመጡም፡፡ ጌታም የገለጸላቸው የዚህ ዓለም ብርሃን እንደመኾናቸው በዓለም የሚነገሩ ቋንቋዎችን ነው፡፡ ሰው የማይሰማውን ቋንቋ ቢናገሩ ኖሮ ከነፋስ ጋር እንደመናገር ይቈጠር ነበር /፩ኛቆሮ.፲፬፥፱/፡፡ ይህንንም ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ *ወአኀዙ ይንብቡ ዘዘዚአሆሙ በነገረ ኵሉ በሐውርት በከመ ወሀቦሙ መንፈስ ቅዱስ፤ ኹሉም መንፈስ ቅዱስን ተሞሉ፡፡ ይናገሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንዳደላቸው መጠንም እየራሳቸው በአገሩ ኹሉ ቋንቋ ይናገሩ ጀመሩ፤* በማለት ገልጾታል /ሐዋ.፪፥፬/፡፡

በዚህ ጊዜ ቤተ አይሁድ በከፊል አንጎራጎሩ፤ አሕዛብ ተደመሙ፡፡ ሐዋርያትን በገዛ ቋንቋቸው ሲናገሩ ሰምተው *እኛ የጳርቴ፣ የሜድ፣ የኢላሜጤም ሰዎች ስንኾን፣ በእኛ ቋንቋ እነሆ የእግዚአብሔርን ጌትነት ሲናገሩ እንሰማዋቸዋልን* ሲሉ አደነቁ፤ ከእግራቸው ሥርም ወደቁ፡፡ በቅፅበትም ሦስት ሺህ ነፍሳት አምነው ተጠመቁ፡፡

በዚህ ዘመን በግላቸው ቤተ እምነት መሥርተው የሚኖሩ ባዕዳን *መንፈስ ቅዱስ ወረደልን፤ አዲስ ልሳን ተገለጠልን፤ እልል በሉ፤* እያሉ ዐይናቸውን ይጨፍናሉ፤ አእምሯቸውን ይስታሉ፡፡ በአንደበታቸውም እነርሱ የማያውቁትን፤ ሌላ ሰውም ሊሰማው የማይችለዉን ትርጕም የሌለዉን ጩኸት፣ እነርሱ ልሳን የሚሉትን ድምፅ ያነበንባሉ፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ዓላማ ሰዎች እርስበርስ እንዲግባቡ ትርጕም ያለዉን ቋንቋ መግለጽ እና ኹሉም በየቋንቋው የእግዚአብሔርን የምሥራች ቃል እንዲማር፣ እንዲያውቅና እንዲረዳ ማድረግ ነው፡፡ ልሳን ማለትም ሰው ሊረዳውና ሊግባባት የሚችል ቋንቋ ማለት እንጂ ድምፅ በማውጣት ብቻ የሚገለጽ ጩኸት አይደለም፡፡ መናፍቃኑ ልሳን የሚሉት ግን ይህንኑ ዓይነት ባዶ ጩኸት ነው፡፡ ይህም ከሰይጣን እንጂ ከመንፈስ ቅዱስ እንዳልኾነ ያጠይቃል፡፡

የመንፈስ ቅዱስ የሆነው አዲስ ልሳን ግን ትናንት በአበው ሐዋርያት ዘመን የነበረ፤ ዛሬም በእኛ ዘመን ያለ፤ ለመጭው ትውልድም የሚተላለፍ ሕያው ልሳን ነው፡፡ ለምን ቢሉ ከሣቴ ምሥጢሩ (ምሥጢር ገላጩ) መንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡

እንግዲህ በነቢያት የተነገረው፣ በሐዋርያት ልቡና በእሳት አምሳል የተገለጠው ምሥጢረ መንፈስ ቅዱስ ይህ ነው፡፡ ይህ ምሥጢር ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላልፎ በሐዋርያት ልቡና ቀርቷል፤ ከሐዋርያት ልቡና ያልደረሰው ደግሞ በልበ መንፈስ ቅዱስ ቀርቷል፡፡ ዓውደ ትምህርቱ ይህ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡