‹‹ጥልንም በመስቀሉ ገደለ›› ኤፌ.፪፥፲፮

በለሜሳ ጉተታ

የዓለም ሰላም የተሰበከውና የተረጋገጠው በመስቀል ላይ በተደረገው የክርስቶስ ቤዛነት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ‹‹ጥልን በመስቀሉ ገድሎ ርቃችሁ ለነበራችሁ ሰላምና የምሥራችን ሰበከ›› ያለው፤ ብፁዕ አባ ያሬድ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራአስኪያጅ እና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የመስቀል በዓል ላይ የተናገሩት ንግግር ነበር፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ በግልጽ እንደሚነግረን ዓለም እንደተፈጠረ ብዙም ሳይቆይ የጥል ግንብ እንደተገነባ ነው፤ የጠቡ መነሻ የሆነው ችግር ድግሞ ለእግዚብሔር አለመታዘዝ፣ታማኝ ሆኖ አለመገኘት፤ ሕግን መጣስ ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ የዲያብሎስን ምክር መቀበልና መስማት  ነው፡፡ (ዘፍ.፪፥፲፮-፲፯፤ ዘፍ. ፫፥፩-፰) ይህ አድራጎት የተፈጸመው በአባታችን አዳምና በእናታችን ሔዋን ሲሆን ድርጊቱ በፈጣሪና በፍጡራን እንዲሁም በፍጡራንና በፍጡራን መካከል ጽኑ የሆነ ጥል ፈጠረ፤ ከባድ የሆነ መርገምና መለያየትም አስከተለ፤ (ዘፍ.፫፥፲-፳፬)፡፡

አዳም ባለመታዘዙ ምክንያት ብዙ ጸጋዎችን አጥቷል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በፍቅር ይኖር የነበረው ሰው ሰላሙን አጥቷል፡፡ ፍርሐትና ጭንቀትም ተጋብቶታል፡፡ ፍጥረታት ይታዘዙለት የነበረው ሰው ይህንን ክብርና ጸጋውንም አጥቷል፡፡ አለመታተዝ ሰላምን ይነሳል፤ ጸጋንም ያሣጣል፡፡ ፍቅርን ይነሳል፡፡ ክብርንም ያሣጣል፡፡ በአገልግሎትና በመንፈሳዊ ሕይወት ላይም ዝለትን ያመጣል፡፡ አባታችን አዳም ባለመታዘዙ ምክንያት ክብርና ጸጋውን አጥቷል፡፡ ሕይወቱንም በፍርሃትና በጭንቀት ለመምራት ተገዱዋል፡፡ መታዘዝ ለበረከት እንደሚያበቃ ሁሉ አለመታዘዝ ደግሞ ለመቅሠፍት ያጋልጣል፡፡ ዛሬም የእኛ ሕይወትም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ባለመታዘዛችን ብዙ ነገሮችን አጥናልና ወደ ልባችን ልንመለስ ይገባል፡፡ መጽሐፍ አለመታዘዝን እንዲህ ብሎ ይገልጻል ‹‹ይህን እወቁ፤ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኵስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም። ከዚህ የተነሣ በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ይመጣልና ማንም በከንቱ ንግግር አያታላችሁ›› (ኤፌ.፭፥፮)።

ባለመታዘዙ ምክንያት አዳም ከፈጣሪው እግዚአብሔር ጋር፤ ከራሱ እና ከሌሎችም ፍጥረታት ጋር ተጣላ፡፡ ጥል ካለ ዘንድ መለያየቱም እየሰፋና እየከፋ መሄዱ የማይቀር ነውና ከአዳምና ከሔዋን የተገኘ የሰው ዘር በሙሉ እርስ በእርስ መጣላቱንና መለያየቱን በስፋት ቀጠለበት፤ በዚህም ሂደት የሰው ልጅ ሕይወት ጣዕም የለሽና መራራ ሆነች፤ ሁሉም በአምልኮ ባዕድና በድንቁርና ተዋጠ፣ ቀለም፣ እምነት፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ መልክአ ምድር አካባቢያዊ ባህል፣ ሀብት፣ ሥልጣን፣ ዕውቀት የመሳሰሉት ሁሉ ሰውን እርስ በርሱ ለያይተው ለከፋ ጉዳት ዳረጉት፡፡ እነዚህ ሁሉ ኃጢአት ወልዳ ያሳደገቻቸው አለመታዘዝ ውጤቶች እንጂ ከጥንተ ፍጥረት የተገኙ አይደሉም፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ “በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ” በማለት የገለጸው (ሮሜ.፭፥፲፱)። በአጠቃላይ ግን ይህንን ታሪክን ከአዳም ውድቀት አንስቶ እስከ  ክርስቶስ ድረስ ያለውን ዘመን ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹በጨለማና በሞት ጥላ የሚኖር ሕዝብ›› ብሎ ገልጾታል (ኢሳ.፱፥፪)፡፡

ያ ዘመን ሰላምና ፍቅር የጠፋበት ዘመን ነበር፡፡ በረከት የራቀበት ጊዜም ነበር፡፡ ያ ዘመን የሰው ዘር በአጠቃላይ በሰማይም ሆነ በምድር በነፍሱም ሆነ በሥጋ ከባድ የሆነ የሞት ቅጣትን ያስተናገደበት ዘመን በመሆኑ ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኩነኔ ተብሎ ተገልጿል (ሮሜ.፭፥፲፪-፲፱)፡፡ ይሁንና ምሕረትና ይቅርታ ገደብ የለሽ ፍቅርና አዘኔታ ገንዘቡ የሆነ እግዚአብሔር አምላክ አንድ ቀን ሰውን ከዚህ የሞት ቅጣት እንደሚታደገው ከመጀመሪያው አንሥቶ ተስፋውን ያሰማ ነበር፡፡

ከዘመን በኋላ እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት የባህርይ ልጁ የሆነ ቀዳማዊ ቃልን ወደ ዓለም ላከ፤ እሱም መጥቶ ሥጋችንን ተዋሕዶ፤ የጥል ምክንያት የሆነውን ኃጢአትን ያጠፋ በመስቀል ላይ  ተሰቅሎ  ነው፡፡ በዚህ መሥዋዕት ምክንያት እግዚአብሔር የዓለሙን ወይም የሰውን ኃጢአት ይቅር ብሎ የምሕረት በሩን ከፈተ፤ ባለመታዘዝ  ምክንያት  የተገነባው የጥል ግድግዳ ፈራርሶ በጥምቀትና በቅዱስ ቁርባን አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር አንድነትን መመሥረት ተቻለ፡፡

በቀለም፣ በዘር፣ በፆታ፣ በሃይማኖት ወዘተ. ተፈጥሮ የቆውን የሰው ከሰው መለያየት ቀርቶ ሁሉም በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምኖ እንዲድን የሁሉም መዳኛ የሚሆን ስም ሰጠ፤ ‹‹ከሰማይ በታች ከዚህ ስም በቀር የምድንበት ሌላ ስም የለምና›› ተብሎም ተጻፋ (የሐ.ሥራ ፬፥፱-፲፪)፡፡ በዚህም የማይታየው አምላክ ታየ  የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ ተገለጠ፡፡

እንግዲህ የጥል ግድግዳው በዚህ ሁሉ ስለፈራረሰ ዛሬ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት የሚከለክል የለም፣ የኃጢአት ግንብ ቢኖርም እንኳ በንስሐ ይናዳል፤ በቀለም፣ በዘር፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በዕውቀት፣ በሀብት በሥልጣን ወዘተ. ከእግዚአብሔር ምሥጢረ ድኅነት የሚከለከል የለም፣ የሚጠየቀው አንድና አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ማመንና መጠመቅ ቀጥሎም በሥነ ምግባር ተወስኖ መኖር ነው፡፡ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ጸንቶ የቆው የጥል ግድግዳ የፈራረሰው በጌታችን በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕትነት ነው፤ መሥዋዕትነቱም የተፈጸመው በመስቀል ላይ ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ጥልን በመስቀሉ ገደለ›› ተብሎ የተነገረው፡፡ መግደል ማለት  ማጥፋት፤ ህልውናን ማሳጣት ማለት ነው፡፡ የቀደመው ጥል በመስቀሉ ጠፋ፣ በመስቀል የተፈጸመው ምሥጢር ጥልን ማጥፋት ብቻ አይደለም ዕርቅን፤ ሰላምን አንድነትንና ነጻነትንም ሰጥቱዋል፡፡ (ሮሜ.፭፥፲-፲፩፣ ፪ተሰ. ፪፥፲፫-፲፭)

‹‹ወደ ቀድሞ የአንድነትና የመቻቻል ባህላችን እንድንመለስ የወቅቱ ሁኔታ ግድ ይለናል፡፡ የመስቀሉን በዓል ከማንኛውም ክፍለዓለም በላቀ ሁኔታ የምናከብር እኛ ኢትዮጵውያን ክፍተቶቻችንን በዕርቅና በይቅርታ ዘግተን ወደ ወንድማዊ ፍቅራችንና ወደ ልማታችን መመለስ እንዴት ያቅተናል? ስለዚህ የሀገርና የሕዛቦች አንድነት ከፖለቲካዊ ርእዮትና አመለካከት በላይ መሆኑን መላው ሕዛባችን ተገንዝቦ ከመለያየት፣ ከመፈናቀል፣ ከመጨካከንና ከመገዳደል ርቆ መከባበሩና አንድነቱን ተቀዳሚ ምርጫው እንዲያደርግ አባታዊ ምክራችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን›› ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ተናግረዋል፡፡

መስቀልን ስናከብርና ስናስታውስ ሁለት ነገሮችን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ አንደኛው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ያዳነን ክርስቶስንና የክርስቶስ ፍቅርን ሲሆን ሁለተኛው ደግም በመስቀል ላይ የተፈጸመው ድኅነታችን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ከዚህም እኛም እርሱን ልንመስል ይገባል፤ ያውም በፍቅር፡፡

የመስቀል በዓልን አመት ጠብቆ ማክበር ብቻ ትርጉም የለውም፡፡ በዓሉን ለመንፈሳዊ ሕይወታችን እድገትና ለውጥ ካላዋልነው ማለት ነው፡፡ በመንፈሳዊ በዓላት ጽድቅና ቅድስናንን ካልገዛንበት ትርጉም የላቸውም፡፡ ምክንያቱም መንፈሳዊ በዓላት ለመንፈሳዊ ሕይወት የተሠሩ ናቸውና፡፡ እንደማንኛውም ሰው የሥጋን ተግባርን ብቻ ፈጽመንበት ካሳለፍን ዋጋ የለውም፡፡ ስለዚህም መንፈሳዊ ተግባራትን ልንፈጽመበት ይገባል፡፡ ስለዚህ የመስቀልን ትርጉምን በሕይወታችን ልንገልጽ ይገባል፡፡ መስቀል ፍቅር ነው፤ ሰላምና አንድነትም ነው፡፡  መስቀል ነጸነትና ክብርም ነው፡፡ መስቀል ልዩነት የጠፋበትና አንድነት፤ ሰላምና ፍቅርን የተገነባበት ነው፡፡ ዛሬ በመካከላችን ሰላምና ፍቅር የለም፡፡ አንድነትና መቻቻልም ጠፍቱዋል፡፡ ጭካኔም በስቱዋል፡፡ አለማዊነት ወርሶናል፡፡ ሥጋዊነት በባርነት ገዝቶናል፡፡ የዘር፣ የብሔር፣ የጎሳ፣ የቋንቋና የድንበር ጉዳይ ሰላማችንን አሳጥቶናል፡፡ የፖለቲካም ተገዥዎች ሁነናል፡፡ የገንዘብና የዓለም ፍቅርም ከመስቀሉ ፍቅር በልጦብናል፡፡ ስለዚህም እነዚህን ክፉ አረሞችን ከልባችን በማውለቅ የመስቀል ፍቅርን ልናነግስ ይገባል፡፡

መስቀሉን ማሰብ (ማክብር) ማለት ክርስቶስንና የክርስቶስን የማዳን ምሥጢር ማሰብ ማለት ነው፡፡ መስቀል ሰላምን፣ አንድነትን፣ ነጻነትና ዕርቅን የሚሰብክና የሚያስተምር፣ ስለድኅነተ ሰብእ የሚመሰክር፤ የእግዚአብሔር የማዳን ዓርማ፣ የድልና የአሸናፊነት ምልክት ነው፤ ኃጢአትና ሞት ተሸንፈውበታልና (፩ቆሮ.፲፭፥፶፭-፶፯)፡፡ ከዚህ አኳያ የክርስቶስ መስቀል ተራ ነገር ሳይሆን በስተጀርባው ነገረ ክርስቶስን ያዘለ በመሆኑ ክርስቶስንና የማዳን ተግባሩን እንደዚሁም የምንድንበትን መንገድ የሚያስተምረን ቅዱስ የሆነ ትእምርተ አድኅኖ ነው፡፡

አይሁድ የመስቀሉን ተአምር በማዮታቸው ቆፈረው ቀብረውታል፡፡ ክርስትናን ለማጥፋት የታሰበው ዛሬ የተጀመረ ክፉ ተግባር አይደለም፡፡ ዛሬ በከፍተኛ ድምቀት የምናከብረው የመስቀል በዓል ከተቀበረበት ጉድጓድ የወጣበትን ለማሰብ ብቻ ሳይሆን መስቀሉ ከፍተኛ መድረክ አግኝቶ የክርስቶስን አዳኝነት ለዓለም ሕዝብ እንዲሰብክ እንዲያስተምርና እንዲመሰክር ለማድረግ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን የመስቀልን በዓል በከፍተኛ ሁኔታ የምታከብርበት ዋና ምክንያት የጥል ግድግዳን የሚያፈርስ፣ መለያየትን የሚንድ፣ በምትኩ ደግሞ ሰላምን፣ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን፣ መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ መተማመንን፣ መቻቻልን፣ መተጋገዝን ፍጹምና ዘላቂ የሆነ ፍቅርን የሚሰጥ ክርስቶስ የተሰቀለበት በመሆኑ ነው፡፡ መስቀል ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› ብሎ ለገዳዮቹ ምሕረትንና ይቅርታን ያሳየበት ነው፡፡ ፍጹም ፍቅርን ይሰብካል፤ መስቀል በንሥሐ ለቀረበ በደለኛ ‹‹ዛሬውኑ ከኔ ጋር በገነት ትኖራለህ›› እያለ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ እንዲኖር ተፈቅዶለታል፣ መስቀል ለሰው ድኅነት ሲባል ራስን አሳልፎ በመስጠት ፍጹም ድኅነት ተሰብኮበታል፤ ሌላም ለሰው ልጅ እጅግ  ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች ተፈጽመውበታል ፡፡

ዛሬ በሀገራችን የሚከሰተው የጥል የጥላቻና የልዩነት መንፈስ የመስቀሉን ስብከትና ትምህርት በቅጡ ካለማዳመጥና ካለማስተዋል የተነሣ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ከክርስቲያን ይህ ክፉ ተግባር መራቅ ይኖርበታል፡፡ የመስቀልን ምልክት በአካሉ፣ በአንገቱ፣ በግንባሩና በልብሱ የተሸከመ ሰው ወንድሙን አይጠላም፤ መናናቅንም አያስተናግድም፤ መከፋፈልን፣ መለያየትን፣  መጨቃጨቅንና ራስ ወዳድነትን የመሳሰሉ የዲያብሎስ የጥፋት ሠራዊት መስቀልን ባነገበ ክርስቲያን ዘንድ ቦታ የላቸውም፡፡ የመስቀል ትርጉም ሰላምና ፍቅር መሆኑን መረዳት አቅቶን በጥላቻ ዓይን መተያየት ትንሽነት ነው፡፡ መስቀል የገደለውን ጥልን፣ ጥላቻቸንና ልዪነትን እንደገና ጎትተን እንዳናመጣው በእጅጉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ከሰላምና ከፍቅር፣ ከመከባበርና ከመተማመን፣ ከወንድማማችነትና ከመፈቃቀር ጥቅም እንጂ ጉዳት እንደሌለ ሁሉም የሚገነዘበው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታም ይህንን ያረጋገጠ ነው፤ በሰላምና በፍቅር ስንኖር ብዙ ነገሮችን ልንሠራ እንችላለን፤ ይህ ፍቅርና ሰላም እስከተጠበቀ ድረስ ሌሎች ብዙ አስደናቂ ነገሮችን መሥራት እንችላለን ዋናው ቁም ነገር የመስቀሉን ትምህርት መቀበልና መከተል ነውና፡፡

የዓለም ቤዛ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን የፈጸመው በመስቀል ላይ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ቅዱስ መስቀል በክርስትናው ዓለም የመዳን፣ የዕርቅ፣ የሰላም፣ የአንድነትና የፍቅር እንዲሁም የተስፋ አርማ በመሆን ያገለግላል፡፡

ቅዱስ መስቀል የልዑል እግዚአብሔር የፍቅሩ ምሥጢር መገለጫም ነው፡፡ አንድ ልጁን ለሁሉ ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን ወዶታልና (ዮሐ. ፫፥፮)፡፡ በአጠቃላይ ቅዱስ መስቀል በክርስቶስ  አዳኝነት የሚያምኑ ሁሉ ወደ  መንግሥተ ሰማያት የሚደርሱበት መሰላል ነው፡፡

ይህም በመሆኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የመስቀልን ታላቅነት ለሕዝበ ክርስቲያኑ ታስተምራለች፡፡ ‹‹ለመስቀልከ ንሰግድ… ለመስቀልህ እንሰግዳለን፤ በመስቀሉ ሕዝቡን አዳነ፤›› እያለች ሕዝበ ክርስቲያኑ ለመስቀሉ ክብር እንዲሰጥ ድምጿን  ከፍ አድርጋ ትሰብካለች፡፡ መስቀሉንም በማንሣት  በሁሉም ማዕዘን ሕዝቧን ትባርካለች፡፡

የማይመረመር እጅግ ጥልቅና ረቂቅ ሰፊና ምጡቅ የሆነው የእግዚአብሔር ጥበብ በቅዱስ መስቀል ላይ ተገልጧል፡፡ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አበው እንደተናገሩት እግዚአብሔር ይህን ዓለም ከፈጠረበት ጥበቡ ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል፡፡ ምክንያቱም የዚህ ዓለም ተፈጥሮ ‹‹ይሁን›› በሚል ቃል ነው፤ ድኅነቱ ግን አምላክ ሰው ሆኖ በመስቀል ላይ በመሞቱ ነው፡፡ ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አይሁድ ምልክትን ይፈልጋሉ፤ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይፈልጋሉ፤ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፡፡ ይህም ለአይሁድ መሰናክል ነው፤ ለአሕዛብ ደግሞ ሞኝነት ነው፤ እግዚአብሔር ለጠራቸው ግን አይሁድም ቢሆኑ ግሪኮች ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኃይል ነው፤ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው›› (፩ቆሮ.፩፥፳፪-፳፬)፤ በማለት ገልጾታል ፡፡

የዓለምን ድኅነት የሚያስረዳው ቅዱስ ወንጌል መሆኑ ግልጥ ነው፤ ይሁን እንጂ ቅዱስ መስቀልን ከቅዱስ ወንጌል መለየት አንችልም፡፡ ወንጌል የሰው ልጆችን ድኅነትና ሕይወትን የሚያበስር ሲሆን የሰዎች ድኅነትና ሕይወት የተፈጸመው ግን ጌታችን በመስቀል ላይ በመሞቱ ነው፡፡ ስለዚህ የተነገረው የመዳን ተስፋ ሁሉ በመስቀል ላይ ተፈጽሟል፡፡

እንግዲህ በመስቀሉ የተገኘውን ሕይወት፣ ሰላም፣ ነፃነትና ክብር ጠብቆ በፍቅር መኖር ይገባናል፡፡ በፍቅር መኖር ማለትም ምንጊዜም ተማምኖ፣ ተከባብሮና ተሳስቦ በሰላም መኖር ማለት ነው፡፡ ቅዱስ መስቀል በተአምራት አድራጊነቱና የክርስቶስ የአዳኝነቱ መሳሪያ በመሆኑ በጎልጎታ ተቀብሮና የጉድፍ መጣያ ሆኖ ለብዙ ዓመታት ቆይቷል፡፡ ነገር ግን የፈጣሪ ሥራ በፍጡር ሊደበቅ ስለማይችል በቅድስት እሌኒ ፍለጋ ኪራኮስ በተባለ አረጋዊ መሪነት በደመራ ጢስ (በዕጣን ጢስ) አመላካችነት ተገኝቷል፡፡ እነሆ ይህን ምክንያት በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ መስከረም ፲፮ ቀን በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ታከብረዋለች፡፡

ቅዱስ መስቀል በክርስትናው ዓለም ሁሉ በተመሳሳይ ወር በተለያየ መልክ ይከበራል፡፡ ይኸው የቅዱስ መስቀል በዓል በሀገራችን ኢትዮጵያ ከሌላው ዓም እጅጉን በላቀና በደመቀ አከባበር ሥነ ሥርዓት ሕዝባዊ፣ ሀገራዊ፣ ቤተ ክርስቲያናዊና ዓለም አቀፋዊ በሆነ መልኩ የሚከበር ሲሆን በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ የውጭ ሀገር እንግዶችም የበዓሉ ታዳሚዎች በመሆን ያከብሩታል፣ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱንም ያደንቃሉ፤ ተመልሰው ወደ ሀገራቸው በሚሄዱበት ጊዜም ስለ ሕዝባችን እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊ እምነት ስለ ሀገራችን ሰላምና ስለ ቤተክስቲያን ታላቅነት ይመሰክራሉ፡፡

በመላው ኢትዮጵያ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊ መሠረቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም፣ በስምምነት፣ በመከባበርና በመደማመጥ እንዲከበርና ከበዓል አከባበር ሥነ ሥርዓቱም በኋላ ሕዝበ ክርስቲያኑ በመጣበት አኳኋን ወደየቤቱ በመመለስ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና የፍቀር ባለቤት መሆኗን ለሌሎች ትምህርት ሊሰጥ በሚችበት ሁኔታ በዓሉን ማክበር ይጠበቅበታል፡፡

መስቀል በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠርን እኛ የሰው ዘሮች ከኃጢአት ባርነት ነፃ የወጣንበት ድኅነተ ነፍስ ያገኘንበት ከእግዚአብሔር ጋር የታረቅንበት ኃይልን ጽድቅን ፍቅርና ሰላምን መዳንና መረጋጋት ያገኘንበት የክርስቲያናዊ ሕይወታችን ዓርማ ነው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ ምእመናን ሁሉ የመስቀል በዓልን በምናከብርበት ጊዜ በሀገራችን ኢትዮጵያ በሰላም ጉዳይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ሁሉ በመወያየት፣ በመደማመጥና በመተማመን የምንፈታበት የቀደሙ አባቶቻችን በፍቅርና በአንድነት በመኖር ያወረሱንን ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በመጠበቅ፣ ይበልጥ በማሳደግና አርአያነታቸውን በመከተል መሆን ይኖርበታል፡፡ ሰላምና ፍቅሩን እርሱ ይስጠን የመስቀሉ በረከትም ከሀገራችን ኢትዮጵያ ጋር ይሁን፤ አሜን፡፡