ግብረ ፊልጶስ ሲምፖዚየም ተካሄደ

 ታኅሣሥ 16 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በማኅበረ ቅዱሳን የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር “ግብረ ፊልጶስ” የተሰኘ ሲምፖዚየም ታኅሣሥ 12 እና 13 ቀን 2006 ዓ.ም. በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ግቢ ውስጥ አካሄደ፡፡

gebra felp 1ታኅሣሥ 12 በብፁዕ አባታችን አቡነ ማትያስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የካናዳና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በጸሎት የተከፈተ ሲሆን፤ በመርሐ ግብሩ ላይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ጠረፋማ አካባቢዎች ከደቡብ ኦሞና ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ወረዳዎች ተጋብዘው የመጡ ከዚህ በፊት በሀገረ ስብከቱና በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ በጋራ ተምረውና ተጠምቀው የነበሩ አገልጋዮችና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

መጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ “ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ” በሚል ርዕስ ትምህርት በመስጠት ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ የየድርሻቸውን እንዲያበረክቱ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከጠረፋማ አካባቢ የመጡት ምእመናን የሥላሴን ልጅነት በጥምቀት ያገኙ በመሆናቸው በአካባቢያቸው ስላለው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ምን እንደሚመስል ተጠይቀው ሲመልሱ፡- “ማኅበረ ቅዱሳን በአካባቢያችን ከፍተኛ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በመስጠት ባለፈው ዓመት ብቻ ከ3700 በላይ ምእመናን የጥምቀት አገልግሎት አግኝተናል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ወደ አካባቢያችን በመምጣት ከጨለማ ወደ ብርሃን አውጥቶናል፡፡ ማኅበሩ በቀጣይነትም በቋንቋችን የሚያስተምሩ አገልጋዮችን እንዲያሰለጥንልን እንፈልጋለን፡፡ በአካባቢያችን የተለያዩ የእምነት ድርጅቶቸ በመግባት የቀደሙት አባቶቻችን ሃይማኖት የሆነውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ቤተ ክርስቲያን እንዳንከተል ከፍተኛ ግፊት እያደረጉብን ነው” ብለዋል፡፡

“የኦርቶዶክስ እምነት ጥንት የቀረ ነው፤ ማስተማር አትችሉም በማለት ከፍተኛ ስቃይ እያደረሱብን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስለሌለን በድንጋይ ላይ ቁጭ ብለን ነው የምንማረው፡፡ በደቡብ ኦሞ ኣሬ ወረዳ ብቻ በቅርቡ ከ800 በላይ ወገኖቻችን ጥምቀትን ያገኙ ሲሆን 365 ከሚሽን የተመለሱ፤ 200 ደግሞ ሃይማኖት አልነበራቸውም” በማለት በአካባቢያቸው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ገልጸዋል፡፡

ምን ትፈልጋላችሁ?` ተብለው ከብፁዕ አባታችን አቡነ ማትያስ ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱም፡-

gebra felp 2“ቤተ ክርስቲያን ያስፈልገናል፤ ምዕመናንን የምናስተምርበት ማሰልጠኛ የለንም፤ ተተኪ አገልጋዮችን በቋንቋችን እንዲያስተምሩን ሥልጠና የሚሰጥልን እንፈልጋለን፤ ወጣቶችን የምናስተምርበት ሰንበት ትምህርት ቤት የለንም፤ ሰው ወደ ሃይማኖታችን አምኖ ከመጣ ማስተማር ይጠበቅብናል፤ ካልተማሩ ለምን መጣን ብለው ጥያቄ ያነሱብናል፡፡ ስለዚህ መምህራንና አገልጋዮች ያስፈልጉናል፡፡ በመምህራን እጥረት እጅግ ተጠምተናል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶቻችን የምንከባከብበት ቁሳቁስ ያስፈልገናል፤ ምዕመናን ከፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተመልሰው መጠመቅ ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን ከሥራ እንባረራለን ብለው ይሰጋሉ፡፡ ስለዚህ አይዟችሁ የሚለንና የሚያስተምረን ብናገኝ ሁሉም ለመጠመቅ ዝግጁ ነው” በማለት ጥየቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን ስብከተ ወንጌል ማስተባበሪያ የትግበራ ከፍተኛ ባለሙያ መምህር ቀሲስ ይግዛው መኮንን የማኅበሩን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት አስመልከቶ ገለጻ አድርገዋል፡፡ በገለጻቸውም “ግልገል በለስ አካባቢ ምእመናን ዛሬም ተዘጋጅተው እንድናጠምቃቸው እየተማጸኑ ሲሆን ከ2100 በላይ ምእመናን ዛሬም የእኛን አገልግሎት እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡ ምእመናን ጠረፋማ አካባቢ ሄደን ስናጠምቅ እዚህ ያለው ምእመን የክርስትና አባትና እናት መሆን ይጠበቅበታል፤ ከረዩ ላይ ሄደን ስናጠምቅ የናዝሬት ሕዝብ ተከትሎን ሄዶ ነጠላና የአንገት መስቀል በመግዛት የክርስትና አባትና እናት ሆኖ መጥቷል፡፡ ስለዚህ እኛ ስናጠምቅ እናንተ ምእመናን ከጎናችን ሆናችሁ እንድትከተሉን እንፈልጋለን፡፡

በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ማትያስ ቡራኬ የመጀመሪያው ቀን መርሐ ግብር የተጠናቀቀ ሲሆን “እንዲህ ዓይነት የተቀደሰ ተግባር ማኅበሩ ሲያከናውን በማየቴ ተደስቻለሁ፤ ወደ ሀገረ ስብከቴ ካናዳ ስመለስ በዚያ የሚኖሩ ልጆቼን አስተባብራለሁ፡፡ ሓላፊነቴንም እወጣለሁ” ብለዋል፡፡

እሑድ በተካሄደው የሁለተኛ ቀን መርሐ ግብርም በርካታ ምእመናንና ከደቡብ ኦሞ፤ እንዲሁም ቤንሻንጉል ጉሙዝ የተጋበዙ ምእመናንና አገልጋዮች የተገኙ ሲሆን፤ ሐዋርያዊ ተልእኮ በኢትዮጵያ በቀድሞው፣ በመካከለኛውና በአሁኑ ዘመን ያለውን ሁኔታ የሚዳስስ ጥናታዊ ጽሑፍ በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ቀርቧል፡፡

ዲያቆን ያረጋል ባቀረቡት ጥናትም የቤተ ክርስቲያናችን ስብከተ ወንጌል አገልግሎት በአሁኑ ሰዓት በሚጠበቀው መልኩ እየተከናወነ ባለመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን ልጆቿን እየተነጠቀች መሆኑንና ይህንን አገልግሎት ውጤታማ ለማድረግ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ክርስቲያናዊን ግዴታ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

“ስብከተ ወንጌል አሰጣጣችን አካባቢያዊና ወቅታዊ ሁኔታን ያገናዘበ ያለመሆን ችግር ይታይበታል፡፡ የቤተ ክርስተያናችንን ማንነትና ትምህርቷን በሚገባ የተረዳን አንመስልም፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚታይ ነገር ላይ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ ለስብከተ ወንጌል የምንሰጠው ትኩረት እጅግ በጣም አናሳ ነው፡፡ አብዛኛው ሰው ለስብከተ ወንጌል አስተዋጽኦ ለማድረግ ሲሳተፍ አይታይም፡፡ በስብከተ ወንጌል መጽደቅ ያለበት ሰው ነው፡፡ የሚጸድቅም የሚኮነንም ሰው ነው፤ የስብከተ ወንጌል አሰጣጣችን በብዙ ችግር የታጠረ ስለሆነ የሁላችንንም ድጋፍና ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡”

“አንድ ወቅት አርብቶ አደር በሆኑት ቦታዎች የሚገኙ ወገኖቻችን እንዲጠመቁ ሲጠየቁ የሚጠጡት ወተት፣ የሚበሉት ሥጋ በመሆኑ ለአባቶቻችን አንድ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ መጠመቅ እንፈልጋለን፤ እንደ እናንተ ስንዴና ገብስ አናመርትም፤ እነዚህን እስክናመርት በጾም ወተትና ሥጋውን እንበላ ዘንድ ፍቀዱልን በማለት የጠየቁበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህ የሚያመለክተን አለመሥራታችንና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ላይ ትኩረት አለማድረገችንን ያሳያል፡፡” በማለት ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ በቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ ምዕመናን ያላቸውን ጥያቄዎች በማቅረብ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ከጠረፋማ አካባቢዎች ከደቡብ ኦሞና ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ወረዳዎች ተጋብዘው የመጡት የምእመናን፤ ተወካዮችና አገልጋዮች የተሰማቸውን ስሜት የገለጹ ሲሆን አገልጋይ ዲያቆናቱ መዝሙር አቅርበዋል፡፡