ጌቴሴማኒ

ነሐሴ ፳ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ሥርወ ቃሉ ከዕብራይስጥ ቋንቋ የሆነው ጌቴሴማኒ “ጋት እና ስሜኒ” ከሚሉ ከሁለት ጥምር ቃላት የተገኘ ነው፡፡ ትርጉሙም “የዘይት መጭመቂያ”  ማለት ነው፡፡ ጌቴሴማንኒ የአትክልት ቦታ ዙሪያውን በወይራ ዛፎች የተከበበ ነው፡፡ በዚያም ብሩክ የተባለ ሸለቆ አለ፡፡ ይህም ስፍራ አምላካችን እግዚአብሔር ፍርዱን የሚያደረግበት እንደሆነ ይታመናል፡፡ የዚህ ሸለቆ ሌላኛው ስም “የኢዮሳፍጥ ሸለቆ” ነው፡፡  ኢዮሳፍጥ የሚለው ስያሜ “ጆቬ እና ሶፎጥ” ከሚሉት የዕብራይስጥ ቃላት የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም “እግዚአብሔር ይፈርዳል”  ማለት ነው፡፡ “አሕዛብን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ ወደ ኢዮሣፍጥም ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፤ ስለ ርስቴ፣ ስለ ሕዝቤ፣ ስለ እስራኤል፣ በዚያ ልፈርድባቸው እገባለሁ፤ ምድሬን ከፋፍለዋል፤ ሕዝቤንም በሕዝቦች መካከል በታትነዋልና” እንዲል። (ኢዩ.፫፥፪)

በብሉይ ኪዳን እንደተገለጸው የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕትነት የጀመረው በጌቴሴማኒ ነው፡፡ “ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ እነርሱንም፣ “ወደዚያ ሄጄ በምጸልይበት ጊዜ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው።  ጴጥሮስንም ሁለቱንም የዘብዴዎስን ልጆች ወስዶ ሊያዝን ሊተክዝም ጀመር። ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ አላቸው። ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ። አባቴ ቢቻልስ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ።

ወደ ደቀ መዛሙርቱም መጣ፤ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው። ደግሞ ሁለተኛ ሄዶ ጸለየና አባቴ፥ ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ፥ ፈቃድህ ትሁን አለ። ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። ደግሞም ትቶአቸው ሄደ፤ ሦስተኛም ያንኑ ቃል ደግሞ ጸለየ። ከዚያ ወዲያ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥቶ እንግዲህስ ተኙ፤ ዕረፉም፤ እነሆ፥ ሰዓቲቱ ቀርባለች፤ የሰው ልጅም በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው። (ማቴ.፳፮፥፴፮-፵፮፣ ማር.፲፬፥፴፪፣ ሉቃ.፳፪፥፴፱፣ ዮሐ.፲፰፥፩)

ከዚህ በኋላም በዚሁ ስፍራ የአስቆርቱ ይሁዳ እርሱን ለአይሁድ አሳልፎ ሰጠው፡፡ ”ገና እየተናገረ ሳለ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች የተላኩ ሰይፍና ቆመጥ የያዙ ብዙ ሰዎችም አብረውት ነበሩ። አሳልፎ የሚሰጠውም “እኔ የምስመው ሰው እሱ ነው፤ ያዙት” በማለት ምልክት ሰጥቷቸው ነበር። ይሁዳም በቀጥታ ወደ ኢየሱስ በመሄድ “ረቢ! ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎ ሳመው።  ኢየሱስ ግን “ወዳጄ፣ እዚህ የተገኘህበት ዓላማ ምንድን ነው?” አለው። በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ቀርበው ኢየሱስን ያዙት፤ አሰሩትም።

ሆኖም ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ሰዶ ሰይፉን በመምዘዝ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቆረጠው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ። ለመሆኑ በዚህች ቅጽበት ከ፲፪ ሌጌዎን የሚበልጡ መላእክት እንዲልክልኝ አባቴን መጠየቅ የማልችል ይመስልሃል? እንዲህ ከሆነ ታዲያ እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉት ቅዱሳን መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?”  በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ሰዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወንበዴ የምትይዙ ይመስል ሰይፍና ቆመጥ ይዛችሁ የመጣችሁት እኔን ለመያዝ ነው? በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ተቀምጬ አስተምር ነበር፤ ሆኖም ያን ጊዜ አልያዛችሁኝም። ይህ ሁሉ የሆነው ግን በነቢያት መጻሕፍት የተጻፈው እንዲፈጸም ነው።” በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ጥለውት ሸሹ። ኢየሱስን ያሰሩት ሰዎች ጸሐፍትና ሽማግሌዎች ወደ ተሰበሰቡበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት።”(ማቴ.፳፮፥፵፮-፶፯) ከዐራተኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ደግሞ ስፍራው ለከበሩ የክርስቲያን በዓለት እየተከናወነበት ነው፡፡

ጌቴሴማኒ የጌታችን መሥዋዕትነት የተደረገበት ብቻ ሳይሆን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም መቃብር ቦታ ነው፡፡ በክርስቲያኖች ዘንድ ከእመቤታችን ፍቅር የተነሣ የከበረ መቃብር ቦታዋን እንደ ዓይን ብሌን ይጠበቃል፡፡  ምንም እንኳን ቅድስት አናታችን እንደ ልጇ በክብር ተነሥታ ብታርግም ጌቴሴማኒ የሚገኘው የመቃብር ቦታዋ የከበረ ሥጋዋ አርፎበት ስለነበር ስፍራው የተቀደሰ እንደመሆኑ ሕዝበ ክርስቲያን በዚያ ለመባረክ በተለያዩ ክብረ በዓሎቿ ወደዘያ ይመጣሉ፡፡

በጌቴሴማኒ የሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው ኢዮሣፍጥም ሸለቆ፣ በሞሪያ ኮረብታና በድብረ ዘይት ተራራ መካከል ነው፡፡ በቅራቢያም የሚገኘው ቦታ የሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ የተወገረበትና ጌታችን በይሁዳ ለአይሁድ ተላልፎ የተሰጠበት ነው፡፡  የእመቤታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያኗም በመስቀል ቅርጽ የተሠራች ስትሆን ወደ እመቤታችን መቃብር የሚያስኬድ ባለ ፵፰ ሰፋፊ ደረጃዎች ያለው የካታኮምብ (የጉድጓድ) ሸለቆ ይገኛል፡፡ መቃብሩም በሞኖሊት አለት የተቀረጸ ነው፣ ዙሪያውን በሁለት መግቢያ ባለው ኪዩብ የተከበበ ሲሆን ይህም ምእመናን ከምእራብ መግቢያ ወደ መቃብሩ እንዲገቡ እና በሰሜን እንዲወጡ የሚያስችላቸው ስፍራ ነው።