‹‹ጌታውን ያስደሰተው አገልጋይ ታማኝና ቸር አገልጋይ ነው›› ቅዱስ ያሬድ

                                      ሚያዚያ ፬፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ከማንም አስቀድሞ አገልግሎት ለአምላካችን እግዚአብሔር ይገባል፤ በጥንተ ተፈጥሮ በመጀመሪያው ቀን የተፈጠሩት መላእክት ፈጣሪያቸውን ዘወትር ያለማቋረጥ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ እንደሚያመሰግኑት ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በመጽሐፈ አክሲማሮስ ገልጾልናል፡፡ (አክሲማሮስ ዘእሑድ) በዕለተ ዓርብ ሰው ሲፈጠር እንደ መላእክቱ የፈጠረውን ጌታውን እንዲያመሰግን፣ እንዲያገለግል እንዲሁም ስሙን እንዲቀድስና ክቡርን እንዲወርስ በመሆኑም የቀደመ ሰው አዳምም አምላኩን እያመሰገነና በገነትም በጸሎት እየተጋ ኖሯል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስና በሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቦ እንደምናገኘው ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ አምላኩን ለማመስገን ባለመፍቀዱ ተረግሞ ወደ ምድር ከተጣለ በኋላ የሰውን ዘር በተለያዩ መንገዶች በማሳት፣ ከቀናው መንገድና ከጽድቁ ጎዳና በማስወጣት ፈጣሪያቸውን እንዳያገለግሉ ያደርጋል፡፡ (ዘፍ.፩-፰፣ አክሲማሮስ ዘዓርብ)

ይህ በእርግጥ አስከፊና አሳዛኝ ቢሆንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት  ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ›› በማለት እንደ ነገራቸው ምንም እንኳን ጠላታችን መከራ አጽንቶና ተስፋ አስቆርጦ ብኩንና ከንቱ ሊያደርገን ቢጥርም መከራውን አልፈን፣ ሥቃያችንን ተቋቁመንና ችግራችን ተወጥተን በመልካም አገልግሎት ወደ አምላካችን መንግሥት መግባት ይቻለናል፡፡ (ዮሐ.፲፮፥፴፫)

መልካም አገልግሎት ለእግዚአብሔር አምላክ በሰውነታችን በበጎነታችን፣ በቅንነታችን፣ በትሕትናችን፣ በዕውቀታችንና በጉልበታችን የምናቅርበው የጸሎት፣ የጾም፣ የምጽዋት፣ የትሩፋትና የፍቅር አገልግሎት ነው፡፡ አምላካችንን ከማመስገን በተጨማሪ ዘወትር እርሱን በመፍራት በዕለት ኑሮአችን ልናስበውና ልናገለግለው ይገባል፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ሰው በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስት ቢሆን ክፋትና ኃጢአት ከመሥራት ርቆ ይኖራልና፡፡ በቅንነትና በትሕትና የተሞላ የማኅበራዊ ሕይወትም ይኖረዋልና፡፡ ለሌሎች ሰዎችም መልካም ከማድረግ አይቦዝንም፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ባካበተው የመንፈሳዊ እና ዓለማዊ ዕውቀት እንዲሁም ባለው ጉልበት አምላኩን ዘወትር ያገለግላል፤ ይህም ተግባሩ ለጌታው የታመነ ታማኝና ቸር አገልጋይ ያሰኘዋል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ የሐዲስ ኪዳን ክፍል ወንጌል ላይ ቅዱስ ማቴዎስ የጻፈውን አንድ ታሪክ እናንሣ፤ ‹‹አንድ ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ባለጸጋ ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤  ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ ለአንዱ አምስት መክሊት፣ ለአንዱ ሁለት፣ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድር ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ።››

ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ “ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት” አለ። ጌታውም “መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” አለው።

ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ “ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት” አለ። ጌታውም “መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” አለው።

አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ “ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ” አለ። ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፦ “አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁበት እንዳጭድ ካልበተንሁበትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፤ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር። ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት፤ ዐሥር መክሊትም ላለው ስጡት፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳን ይወሰድበታል። የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።›› (ማቴ.፳፭፥፲፬-፴)

ባለ ጸጋ የተባለው ጌታችን ነው፡፡ መክሊት የተባለው ደግሞ ከአምላካችን የተጠን የተለያዩ የአገልግሎት ጸጋዎች ናቸው፡፡ በታማኝነት ያገለገሉት ሰዎች ምሳሌ በምድራዊ ሕይወታቸው በተሰጣቸው ጸጋ በትጋት አምላካቸውን አገልግለው በመልካም ዕረፍት ገነት የገቡት ቅዱሳን ሰዎች ናቸው፤ መክሊቱን የቀበረው ሰነፍ አገልጋይ ደግሞ በተሰጣቸው ጸጋ በታማኝነት ማገልገል  ሲገባቸው ያላገለገሉ ሰዎች ምሳሌ ነው፡፡

ጌታቸው ሊቆጣጠራቸው የመምጣቱ ነገር ጌታችን በዕለተ ምጽአት ለፍርድ ሲመጣ ለሁሉም በሠራው ሥራ መጠን ዋጋ ለመስጠት እንደሚመጣ የሚያመለክት ነው፡፡ ያገለገሉትን ታማኝ አገልጋየችም ለእያንዳንዱ ‹‹ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!››  ማለቱ ታማኝ አገልጋዮች መንግሥተ ሰማያትን እንደሚወርሱ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ሰነፉ አገልጋይ ወደ ጨለማና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ቦታ መወርወሩም ኀጥአን ወደ ገሃነመ እሳት መጣላቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ጌታውን ያስደሰተው አገልጋይ ታማኝና ቸር አገልጋይ ነው›› በማለት የተናገረው ይህን የወንጌል እውነት የሚገልጽ ነው፡፡ ታማኝነትና ቸርነት ለአገልግሎታችን እጅጉን አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ታማኝ መሆን ያለ ጥርጥርና በፍጹም እውነት ለአምላካችን መገዛት፣ መታዘዝና መኖር እንዲሁም በሕጉ መኖር ነው፡፡ ይህም ለእርሱ ታምነን ያለ ሐሰት፣ ያለ ስርቆት፣ ያለ አመንዝራነት እና ያለ ክህደት ወዘተ. እንድንኖር ይረዳናል፡፡ በተሰጠንም ክሂሎት፣ ተሰጥኦና ትሩፋት ማገልገል ያስችለናል፡፡ በአንደበታችን እንድናመሰግናው፣ በእጆቻችን አጨብጭበን፣ በጣቶቻችን በገና ደርድረንና መሰንቆ መትተን እንድንዘምርለት፣ በጉልበታችን እንድንሰግድለት በልባችን እንድናፈቅረው አስተምሮናል፡፡

ቸር በመሆን ለሌሎች በለጋስነት ካለን ነገር በመስጠትና በማካፈል መኖርን አሳይቶናል፡፡ አንድ ዳቦ ያለው ግማሹን ለሌላው እንዲያካፈል፣ ሁለት ልብስ ወይም ጫማ ያለው ለሌለው እንዲሰጥ፣ ከማዕዳችን ለተራቡ እንድናበላ፣ ከማድጋችን ለተጠሙ እንድናጠጣ፣ ለተቸገሩትና ላዘኑት ቸርነት በማድረግ እንድናስተዛዝን፣ የታመሙትን እንድናስታምም የአምላካችን ቅዱስ ቃል ያዘናል፡፡ እኛም እንደ መልካም ልጆቹ ለእርሱ በመታዘዝ ታማኝና ቸር አገልጋይ እንሁን!

የአምላካችን እግዚአብሔር ቸርነትና ረድኤት አይለየን፤ አሜን!