ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ

ልጆች ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አንድ ደግ ሳምራዊ ለአንድ ሕግ አዋቂ በምሳሌ ያስተማረውን ትምህርት አቅርበንላችኋል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የደጉ እና ርኀሩኁ ሳምራዊውን ምሳሌ ጌታችን ለአንድ ሕግ አዋቂ ያስተማረውን በሉቃ.፲፥፳፭-፴፯ ላይ ተጽፎ ስለሚገኝ በጥሞና ታነብቡት ዘንድ እናሳስባችኋለን፡፡

አንድ ቀን አንድ የሕግ ባለሙያ ጌታችንን ሊፈትነው ቀርቦ «መምህር ሆይ የዘላለም ሕይወትን እንድወርስ ምን ልሥራ (ላድርግ)? ሲል ጠየቀው፡፡»

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕግ ዐዋቂው «በሕግ በመጽሐፍ የተጻፋውን አንተ እንዴት ታነባለህ? ብሎ ጠየቀው፤ ሕግ ዐዋቂውም ለጌታችን  ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም  በፍጹም ኃይልህም  በፍጹም አሳብህም ውደድ፤ ባልንጀራህንም  እንደራስህ ውደድ»  በማለት መለሰለት፡፡

ጌታችንም ለሕግ ዐዋቂው «እውነት መለስህ፡፡ የዘላለም ሕይወትን ለማግኘት በሕይወትም ለመኖር ከፈለክ ጌታ አምላክህን በፍጹም ነፍስህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደራስህ አድርገህ ውደድ» አለው፡፡

በዚህን ጊዜ ጌታችን ራሱን ከፍ አድርጎ ሌላውን ንቆ ጥያቄ ላቀረበው ሕግ ዐዋቂ ባልንጀራው ማን እንደሆነ እንዲረዳ እና ምን ማድረግ እንዳለበት የሚከተለውን ታሪክ በምሳሌ ሊነግረው እንዲህ  በማለት ጀመረ፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ሰዉ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ  ወረደ፤ ተጓዘ፡፡

ይህ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ በመንገድ ላይ እየተጓዝ ሳለ በድንገት ወንበዴዎችና ሽፍቶች አገኝተውት መጥተዉ አስቆሙት::ገንዘቡን ወሰዱ፤ ልብሱንም ገፈፉበት:: ደብድበዉም፤ አቁስለው ሊሞት ሲቃረብ በመንገድ ላይ ጥለውት ሔዱ:

አንድ ካህን በዚያ መንገድ ሲሔድ ያን ተደብድቦ የወደቀውን ሰው ቀርቦም ቢያየው ተጎድቷል፤ ነገር ግን ሳይረዳዉ አልፎ ጥሎት ሔደ፡፡

ከካህኑ ቀጥሎ ደግሞ አንድ ከሌዊ ወገን የሆነ ሰው በዚያ መንገድ ሲያልፍ በወንበዴዎች ተደብድቦ የወደቀዉን ሰዉ አገኘው እና አየዉ:: ነገር ግን እርሱም ሳይረዳዉ ዝም ብሎ በመንገድ ላይ እንዳየው እንደቀደመው ካህኑ ሌዋዊውም ገለል ብሎ አልፎት ሔደ::

አንድ ሳምራዊ ግን በዚያች መንገድ ሲሄድ አገኘው፤ አይቶም አዘነለት፤ ወደ ቆሰለው ቀርቦ በቁስሉ ላይ እንዲያደርቅለት ወይን አደረገለት፤እንዲያለሰልስለት ደግሞ ዘይት በቁስሉ ላይ አፈሰሰለት፡፡

ደጉ ሳምራዊው የተደበደበውን ተጓዠ ሰው ቅርብ ወዳለው እንግዳ ማረፊያ ስፍራም ከአስገባው በኋላ እየተንከባከበዉ፤እያስታመመው የሚፈልገውን እያደረገለት አብሮት በሰላም አደሩ፡፡

በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዶች ማረፊያ ማደሪያ ወይም ማደሪያ ቤት ባለቤት ኃላፊ ለሆነው ሰው ሰጠዉ፡፡ ከሰጠዉም በኋላ «የምትከስረዉን ሁለ እኔ ስመለስ እከፍልኀለው» ብሎ የተደበደበውን ሰው አደራ ሰጥቶ ወደ ሌላ ስፍራ ሔደ፡፡

ልጆች! የጌታችንን ምሳሌውን እየተከታተላችሁ ነው አይደል? መልካም! ታዲያ ለዚህ ተደብድቦ በመንገድ ላይ ለወደቀዉ ሰዉ ባልንጀራዉ የሆነለት የትኛዉ ሰው  ይመስላችኀኋል?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሳሌውን ታሪክ የእግዚአብሔርን ሕግ ዐዋቂ ለሆነው ሰው ነግሮ ከጨረሰ በኋላ «ከእነዚህ ከሦስቱ ከካህኑ፣ከሌዋዊዉ እና ከሳምራዊዉ በወንበዴዎች እጅ  ለወደቀዉ  ባልንጀራ የሆነዉ ማንኛዉም ይመስልሃል?» ሲል የሕግ ዐዋቂዉን ጥያቄ ጠየቀዉ::

ጌታችን ኢየሱስም ሕግ አዋቂ ለሆነው ሰው እንዲህ አለው «አንተም የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ፣ በሕይወት ለመኖር ሕግን ማወቅ፣ ስለ ፈጣሪ ሕግ መናገር ፣ለሚጠየቁ ጥያቄዎች መልስን መስጠት ብቻ ሳይሆን፤ እንደ ሳምራዊዉ ሰዉ የአንተን እርዳታ ለሚፈልጉ ማንኛውም ሰው መልካምን አድርግ» በማለት ነገረው፡፡

«የወደቁ ሰዎችን እርዳ ፣ምሕረት አድርግ ፣ተንከባከብ፡፡ ባልንጀርነት ማለት ምሕረት ማድረግ ማለት ነው፡፡ ሒድ አንተም እንደ ሳምራዊው ምሕረት አድርግ በሕይወት ትኖራለህ»  አለው፡፡

ልጆች በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ባልንጀራ የሚባለው በጉርብትና የሚኖርን ፤በአርአያ  ሥላሴ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ የሰውን ዘር በሙሉ ይመለከታል፡፡ ደጉ ሳምራዊ እንደተመለከትነው በመንገድ ላይ ወድቆ ያገኘውን ቁስለኛ አንስቶ መልካም ነገር ስላደረገለት፣ ከወንበዴዎች እጅ ስላዳነው፣ምሕረትም ቸርነትም ስለአደረገለት ባልንጀራው ተብሏል፡፡ በመንገድ ላይ ወድቆ ላገኘው ሰው ባልንጀራው ነው፡፡ ታዲያ የእናንተ ባልንጀራችሁ ማን ነው? የሰው ልጅ በሙሉ ባልንጀራችሁ ነው፡፡ ይህም ባልንጀራችሁን እንደ ራሳችሁ ውደዱ! የሚለውን ሕግ ያስተውሰናል፡፡

ባልንጀራን መውደድ ማለት የሰውን ዘር ሁሉ ማንንም ከማን ሳየበላልጡ እኩል በሆነ ፍቅር መመልከትና ማክበር ነው፡፡እንደ ራስ መውደድ ማለት ደግሞ ለራስ የሚፈልጉትን መልካም ነገር ለባልንጀራ ማድረግ ነው፡፡ለራሳችሁ መከበር አለመናቅን እንደምትፈልጉ ባልንጀራችሁን አክብሩ ውደዱ አትናቁ!!! «ባልንጀራን የሚንቅ ይበድላል!» (ምሳ.፲፩ ፥፳፯)

ልጆች ትእዛዙን ጠብቁ! ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትወዱታላችሁ? አዎ ካላችሁ እርሱ ደግሞ የሚላችሁ ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ ነው፡፡ ትእዛዙም እኔ እንደወድኳችሁ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ ይላል፡፡ እንደዚሁም እንደ ደጉ ሳምራዊዉ ባልንጀራችሁን ውደዱ ፣ደግ ሁኑ፣ደግ አድርጉ፤ የተቸገረ ማንኛዉም ሰዉ መርዳት ይገባችኋል:: ሰዎች የእናንተን እርዳታ በሚፈልጉበት ጊዜ ደጉ ሳምራዊውን ኢየሱስ ክርስቶስን በማሰብ በማንኛዉም ጊዜ አድርጉ፡፡ ያን ጊዜ ሰላማዊው ንጉስ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናንተ ጋር ይሆናል!!! «ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ከእናንተ ነኝ፡፡» (ማቴ.፳፰፥፳)

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!!!

ምንጭ፤ ደጉ ሳምራዊ- የሕፃናት መጽሐፍ ፳፻፲ ዓ.ም.