ይቅርታ

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
መጋቢት ፳፮፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? ትምህርት የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት የሚደግፈንና በምድራዊ ኑሯችን ወደፊት ለመሆን የምንመኘውን ለማግኘት የምንጓጓበት መንገድ ነው! በዚህ ምድር ስንኖር መመገብ ያስፈልገናል፤ ለመመገብ ደግሞ መሥራት አለብን፤ ምክንያቱም በቅዱስ መጽሐፍ አምላካችን እግዚአብሔር ለአባታችን ለአዳም ‹‹በሕይወትህ ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ…›› በማለት ነግሮታልና፡፡ (ዘፍ.፫፥፲፯) ስለዚህ በምድር ስንኖር ጥረን ግረን መብላት አለብን፡፡

ልጆች! ለመሥራት ደግሞ ትምህርት ያስፈልጋል፤ ነገ አድጋችሁ በተለያየ ኃላፊነት ላይ ሆናችሁ አገርን እንድታገለግሉና እንድትመሩ ዛሬ በርትታችሁ ጠንክራችሁ ተማሩ! የወላጆቻችሁ ድካማቸው የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ እያሟሉ እንድትማሩ የሚያደርጓችሁ እናንተ ጎበዝ፣ ብልህ፣ አስተዋይና ታማኝ ስትሆኑ ለማየት ነው፡፡ መልካም! ለዛሬ የምንማማረው ባለፈው የጀመርነውን የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ቀጣዩን ክፍል ‹‹ይቅርታ›› በሚል ርእስ ይሆናል፡፡ መልካም ቆይታ!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ይቅርታ ማለት የበደለን ሰው መልሶ አለመበደል ማለት ነው፤ ለምሳሌ የሰደበን ሰው መልሶ አለመሳደብ፣ ክፉ ያደረገብንን ሰው እኛም እንደ እርሱ ክፉ አለማድረግ፣ በይቅርታ ማለፍ ይህ ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አንዱ ነው፡፡ የበደለን ሰው ይቅር ማለት መታደል ነው፡፡ ልጆች! በማንኛውም ነገር ሁሉ ይቅር ባይ ከሆንን ሰዎችን በይቅርታ ስናልፍ እግዚአብሔር ይባርከናል፤ እኛንም ይቅር ይለናል፤ ‹‹አባታችን ሆይ›› እያልን በምንጸልየው ጸሎት ላይ ‹‹…እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል…ይቅር በለን…›› የሚል ኃይለ ቃል አለበት፤ (ማቴ.፮፥፲፪) ታዲያ ልጆች! በዚህ ጸሎት ላይ እንዳለው የይቅርታ ሰዎች መሆን አለብን፡፡ በቤት ውስጥ ካሉ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን አልያም ሰፈር ውስጥ ካሉ ወይም በትምህርት ቤት ከምናውቃቸው ጓደኞቻን ጋር በአንዳንድ ነገር ልንጣላ (ላንግባባ) የሚያስችሉ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ! እኛ ከሆንን የበደልናቸው ይቅርታን መጠየቅ አለብን፤ ወይም እኛ ተበድለን ከሆነ ይቅርታን ማድረግ አለብን፡፡ ቂም ከመያዝ እነርሱ እንዳደረጉብን መጥፎ ያልነውን ነገር እኛ ደግመን ማድረግ የለብንም፤ በይቅርታ ማለፍ አለብን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅርታ ማድረግ እንዳለብን አስተምሮናል፤ በመስቀል ላይ የተሰቀለልንም እኛን ይቅር ብሎን ነው፤ ጌታችን በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ መከራ ለሚያደርሱበት ይቅርታን አድርጎላቸዋል፤ የምናምነው የክርስትና እምነት መሠረቱ የእርሱ ይቅርታ ነው፡፡ እኛም ሰዎችን ይቅርታ ብንልና መልካም ምግባር ቢኖረን እግዚአብሔር በእኛ ደስ ይለዋል፤ ሰዎችንም ወደ መልካም ምግባር እንዲመጡ ምክንያት መሆን እንችላለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በመጽሐፍ ቅዱስ ተበድለው ይቅርታን ያደረጉ፣ በዚህም ምግባራቸው ክብርን ያገኙ፣ ለክፉ ሰዎችም ከክፋታቸው መመለስ ምክንያት የሆኑ ብዙ አባቶቻችንና እናቶቻችን አሉ፤ ለአብነት እንዲሆነን የዮሴፍን ታሪክ በአጭሩ እንመልከት፡፡ ልጆች! ይህ ታሪክ በስፋት በኦሪት ዘፍጥት (ምዕራፍ ፴፯፣፴፱፣፵‐፵፱) ተመዝግቦ እናገኘዋለን፤ ዮሴፍ መልካም ምግባር የነበረው ልጅ ነበር፤ ታዲያ ወንድሞቹ ቀኑበት፤ ከዚያም ለባርነት ሸጡት፤ በዚያም በነበረበት ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበር፤ ከሚደርስበት መከራ ሁሉ ይጠብቀው ነበር፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! መልካም ነገር በሠራን ጊዜ ሰይጣን ተስፋ ሊያስቆርጠን ከመመስገንና ከመከበር ይልቅ ፈተና ያመጣብናል፤ ታዲያ በዚህ መማረር የለብንም፤ በመልካምነታችን ቀንተው ክፉ ለሚያደርጉብን ሰዎች እኛም በእነርሱ ክፉ ማድረግ የለብንም፤ በትዕግሥትና በይቅርታ ማለፍ አለብን፡፡ ይገርማችኋል! ዮሴፍ በግብጽ በነበረ ጊዜ ብዙ መከራ ደረሰበት፤ እግዚአብሔር ግን ከፍ አደረገው፤ መልካም ሰው ስለነበረ ሹመት አገኘና ባለ ሥልጣን ሆነ፤ ከብዙ ዘመን በኋላ ክፉ ያደረጉበት ወንድሞቹ ችግር ገጠማቸውና እርሱ ካለበት አገር መጡ፡፡

ይገርማችኋል ልጆች! ዮሴፍ ወንድሞቹ የበደሉትን በደል ሁሉ ሳይቆጥር መልካም አደረገላቸው፤ እነርሱ የሠሩትን ክፉ ሥራ አስታውሰው ይበቀለናል፤ ክፉ ያደርግብናል ብለው ሲፈሩ እርሱ ግን ይቅርታ አደረገላቸው፡፡ እነርሱ ምንም ክፉ ቢያደርጉበት እርሱ እንደ እነርሱ ክፉ አላደረገባቸውም፤ ይቅርታ አደረገላቸው፤ ‹‹ወደዚህ ስለሸጣችሁኝ አትፍሩ፤ አትቆርቆሩም፤ እግዚአብሔር ለሕይወት ከእናንተ በፊት ልኮኛልና›› አላቸው፡፡ (ዘፍ.፵፭፥፭)

አይገርምም ልጆች! ደብድበው መከራ ያደረሱበትን፣ በባርነት የሸጡትንና ከሚወደው አባቱ ለይተው ወደ ስደት የዳረጉትን ወንድሞቹን ሲያገኝ ያንን ሁሉ ረስቶ ይቅር አላቸው፤ የእነርሱ ክፋት ሳይሆን ለእርሱ የታወሰው የእግዚአብሔር ምሕረትና ጥበቃው ነበርና ቂም አልያዘም፡፡ ልጆች! ምን ጊዜም ማሰብና ማስታወስ ያለብን የሰዎችን ክፉ ሥራ ሳይሆን እነርሱ ክፉ ሲያደርጉብን ከክፉ የጠበቀንን የእግዚአብሔርን ፍቅርና ምሕረት ነው፤ ስለዚህም ልጆች የእግዚአብሔርን ቸርነት ስናስብ ደግሞ ልባችን ቂም ከመቋጠር (ከመያዝ) እንዲሁም ክፉ ነገር ከማሰብ ይነጻል፤ ልባችን ንጹሕ ከሆነ የይቅርታ የፍቅር ሰዎች እንሆናለን፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹አቤቱ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ…›› በማለት እንደጸለየው ልባችን ከቂም በቀል ርቆ የይቅርታ ሰዎች እንድንሆን እኛም እንጸልይ፤ (መዝ.፶፥፲) ጌታችን ‹‹..ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና…›› በማለት አስተምሮናልና፡፡ (ማቴ.፮፥፲፬) ይቅርታ ማድረግ ክብሩ ለራስ ነውና የይቅርታ ሰዎች እንሁን!

አምላካችን ይቅር ባይ ሆነን ለክብር እንበቃ ዘንድ ማስተዋሉን ይስጠን፤አሜን!

ቸር ይግጠመን!!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!