ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው

ትኅሣሥ 17 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

tsreha tsion 2በማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል መደበኛና ኢ-መደበኛ አባላት በአገልግሎት ዙሪያ ለመወያየትና ከጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር አባላት ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንዲቻል ከአዲስ አበባ በምዕራብ አቅጣጫ ቡራዩ አካባቢ ወደሚገኘው ጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር መንደር ታኅሣሥ 12 ቀን 2006 ዓ.ም. የጉዞ መርሐ ግብር አካሒዷል፡፡

አባላቱ አንድ የማኅበረ ቅዱሳን አገልጋይ በተከራየላቸው መለስተኛ አውቶብስ (ሃይገር ባስ) በመሳፈር ከ45 ደቂቃ ጉዞ በኋላ ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት ላይ የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር ደረስን፡፡ በማኅበሩ አባላት በመሠራት ላይ የሚገኘውን የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን እየተሳለምንና በነፋሻማው አየር እየታገዝን ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡ ግቢው በተለያዩ አጸዶች ተውቧል፡፡ ነፍስ ምግቧን ታገኝ ዘንድ ትክክለኛው ሥፍራ በመሆኑ የነፍሳችንን ረሃብ ለማስታገሥ ቸኩለናል፡፡ የአባቶችን ቡራኬ ተቀብለን አጭር የግል ጸሎታችንን አድርሰን ለጉብኝቱ ተዘጋጀን፡፡ ጉብኝቱ የተጀመረው ስለ ጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር አመሠራረት ዲያቆን ደቅስዮስ ገለጻ በማድረግ ነበር፡፡

የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር አመሠራረት

የማኅበሩ መሠረት ሰንበት ትምህርት ቤት ነው፡፡ 1980 ዓ.ም. መጀመሪያ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሰንበት ትምህርት ቤቶች መናፍቃን ሰርገው በመግባት የራሳቸውን ዓላማ ለማስፈጸም ጥረት ያደረጉበት ወቅት ነበር፡፡ ጉዳዩ ያሳሰባቸው የሰንበት ትምህርት ቤቶች ተወካዮችና አባላት በመመካከር የጋራ ጉባኤ ሊኖር እንደሚገባ ውሳኔ ላይ ተደረሰ፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የነበረው የደርግ መንግስት እንቅስቃሴ ስላሰጋው እንዲዘጋ አደረገው፡፡

የወጣቶቹን እንቅስቃሴ ደርግ ቢዘጋውም የተወሰኑ የሰንበት ትምህርት ቤት አመራሮች በመሰባሰብ “ማኅበረ ደብረ ዘይት” በሚል ስም ማኅበር አቋቋሙ፡፡ በማኅበረ ደብረ ዘይት ሥርም “አሠረ ሐዋርያት” በሚል ከሰንበት ትምህርት ቤቶች የተውጣጣ ማኅበር ተቋቁሞ ቆይቶ ጠንካራ አገልግሎትን ለመፈጸም “በአንድነት ለምን አንኖርም? ለምን ቋሚ የሆነ ቦታ አይኖረንም?” በሚል ተነሳስተው፤ ፕሮጀክት በመቅረጽ እና ሕጋዊ ሰውነት እንዲኖረው በማድረግ በ1980 ዓ.ም. በአንድነት ለመኖር ለከተማና ቤት ሚኒስቴር ጥያቄያቸውን በማቅረብ ሕጋዊ ሰውነት አገኝቶ 41‚000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መሬት ተሰጣቸው፡፡

tsreha tsion 3ማኅበሩ ዓላማዬ ብሎ የተነሳው አባላቱ ያላቸውን ሥጋዊና መንፈሳዊ ሀብት በማዋሀድ እርስ በእርስ በመረዳዳትና በመደጋገፍ በሰላምና በፍቅር በአንድነት በመኖር ለኅብረተሰቡ አርአያና ምሳሌ ለመሆን፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት በሚደረገው አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያን እድገትና ልማት አቅም በፈቀደ ሁሉ አስተዋጽኦ ለማበርከት፤ ለኅብረተሰቡ አርኣያ ለመሆን ወዘተ የሚሉ ናቸው፡፡

የአንድነት ኑሮው በተቀናጀና በተጠናከረ ሁኔታ የሚመራ ሲሆን፤ አባላቱ በተለያዩ የሥራ መስኮች በመሠማራት በየወሩ ሰርተው የሚያገኙትን ገንዘብ ለማኅበሩ በማስረከብ፤ ማእድ በየቀኑ በአንድነት በመመገብና በአንድነት በመጸለይ የአንድነት ኑሯቸውን ይመራሉ፡፡ የእኔ የሚሉት ንብረትም ሆነ ሐብት የሌላቸው ሲሆን እርስ በእርስ በመረዳዳትና በመደጋገፍ ከራሳቸው አልፈው አቅመ ደካሞችን በመደገፍ የበጎ አድራጎት ተግባር በመፈጸም ራሳቸውን ለእግዚአብሔር አሳልፈው በመስጠት ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡“ያመኑትም ሁሉ አንድ ልብና አንዲት ነፍስ ሆነው ገንዘብ ይኖሩ ነበር፡፡ በውስጣቸውም የሁሉ ገንዘብ በአንድነት ነበር እንጂ ይህ የኔ ገንዘብ ነው የሚል አልነበረም፡፡ . . . እነርሱም ለእያንዳንዱ እንደፍላጎቱ ይከፍሉት ነበር፡፡” ሐዋ.ሥራ 4፡32-37 ላይ ያነበቡትን ህይወት መረጡ፡፡

ዓላማውንም ለማሳካት በአንድነት በመኖር፤በ1984 ዓ.ም. በዘጠኝ አባላት በግቢው ውስጥ የተወሰኑ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት የአንድነት ኑሮው ተጀመረ፡፡ በአሁኑ ወቅት 22 አባወራች በግቢው ውስጥ ሲኖሩ በአጠቃላይ 150 የሚደርሱ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት በመሰማራት፤ በስነጽሑፍና ኅትመት አገልግሎት በመሳተፍ፤ ሰባኪያነ ወንጌልን በማሰልጠን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

ለልጆቻቸው መማሪያ የሚሆን ትምህርት ቤት ባለመኖሩ በግቢው ውስጥ መዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤት በመክፈት ሥራውን የጀመረው ትምህርት ቤት እስከ 8ኛ ክፍል በማድረስ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ በትምህርት ቤቱ ውስጥ በአነስተኛ ክፍያ፤ እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ እናት አባት የሌላቸው፤ አቅመ ደካማ ለሆኑ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን የትምህርት ቁሳቁስንና ልብሳቸውን በመቻል በነጻ ያስተምራል፡፡ በጎ አድራጊ ምእመናን በሚሰጡት ገንዘብ አማካይነት ማኅበሩ እገዛ ያደርጋል፡፡፡ በቅርቡም አንድ በጎ አድራጊ በለገሱት ገንዘብ አቅም ለሌላቸው ልጆች የቁርስና የምሳ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ትምህርት ቤቱንም ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትነት ለማሳደግ ማኅበሩ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡

በልማት ዘርፍ የጓሮ አትክልት በመትከል፤ የወተት ላሞችን በማርባትና ወተቱን ለልጆቻቸው በመጠቀምና በመሸጥ፤ የኦቾሎኒ ቅቤ “ጽዮን ኦቾሎኒ” የተሰኘ በማዘጋጀትና ለገበያ ያቀርባል፡፡

ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት የመለከት መጽሔትን በማዘጋጀት በሚገኘው ገቢ የልማት ሥራዎችን በመሥራትና ከበጎ አድራጊ ምእመናን በሚገኝ ድጋፍ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ከ1990 ዓ.ም. ጀምሮም የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ለመስጠት በመወሰን ከተለያዩ የኢትዮጵያ ጠረፋማና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በአገልጋዮች እጥረት ምክንያት ከማይሰጥባቸው አካባቢዎች አገልጋዮችን በመመልመል፤ ከአኅጉረ ስብከት ጋር በመሥራት ሙሉ ወጪያቸውን በመቻል በበጋ ለሦስት ወራትና ከዚያም በላይ በክረምት ስልጠና መስጠት የጀመረው ማኅበሩ፤ ቤተ ክርስቲያንን በስብከተ ወንጌል ዙሪያ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ተግቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ እስከ 2005 ዓ.ም. ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ 800 ሰልጣኖችን በስብከተ ወንጌል አገልግሎት አሰልጥኖ ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ አሰማርቷል፡፡

ከተለያዩ በጎ አድራጊ ምእመናን በሚያገኘው ድጋፍም ባለ ሁለት ፎቅ ሕንጻ በመገንባት 120 ሰልጣኞችን ማስተናገድ የሚችል መኝታ ቤት፤ መማሪያ ክፍሎች፤ ቤተ መጻሕፍት፤ መመገቢያ አዳራሽና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መስጫ ሁለገብ አዳራሽ በመሥራት ለአገልግሎት አውሏል፤ በአሁኑ ጊዜም 60 ሰልጣኞችን በአንድ ጊዜ እየተቀበለ ያሰለጥናል፤ ቀሪው 60 ሰልጣኞችን ለመቀበል ሕንፃውን በማጠናቀቅ ላይ ሲሆን ለሰልጣኞች የሚሆን የመኝታ ቁሳቁስ ለማሟላት ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡

ብፀዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የማኅበሩን የአገልግሎት እንቅስቃሴ ለመጎብኘት በመጡበት ወቅት በግቢው ውስጥ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ በመፍቀድ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ዘመን የመሠረት ድንጋይ በማኖር፤ የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በመቃኞ ተሠርቶ አገልግሎት በመሥጠት ላይ ይገኛል፡፡ አገልግሎቱንም ለማስፋት እንዲቻል አዲስ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ በመገንባት ላይ ነው፡፡

ማኅበሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ቤተ ክርስተያንን በማገልገል ላይ ሲሆን በየዓመቱ የበዓለ ጰራቅሊጦስ ዕለት የማኅበሩን አገልግሎት የሚደግፉ ምእመናንን በማሰባሰብ የእግር ጉዞ በማድረግ የገቢ ማሰባበስብ ሥራውን ያከናውናሉ፡፡ ዲያቆን ደቅስዮስ የተረከልንን በዓይናችን አየነው፡፡

tsreha tsion 6ማኅበሩ እያከናወናቸው የሚገኙ የልማት ሥራዎችን፤ በግቢው ውስጥ የሚገኙ ቤቶችን ፣ የአፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤቱን፤ የማኅበሩ አባላት በ1985 ዓ.ም. ወደዚህ ቦታ ተመርተው ሲመጡ ልጆቻቸውን ለማስተማር አንድ ክፍል ሠርተው የአጸደ ሕፃናት ትምህርት ማስተማር እንደጀመሩ በቀጣይነትም ትምህርት ቤቱን ወደ አንደኛ ደረጃ በማሳደግ ተጨማሪ ክፍሎችን በመሥራት በአካባቢው የሚገኙትን እናት አባት የሌላቸውን፤ በችግር ውስጥ የሚገኙትን በመለየትና በነጻ በማስተማር እንዲሁም በአነስተኛ ክፍያ እየከፈሉ ሌሎችም እንዲማሩ ለማድረግ ያላቸውን ዝግጅትሁሉ ጎበኘን፡፡

ትምህርት ቤቱን ጎብኝተን እንዳጠናቀቅን ቀድሞ ቤተ ክርስቲያኑ ከመሠራቱ በፊት የአንድነት ጸሎት የሚያደርሱበት ወደነበረው አነስተኛ አዳራሽ አመራን፡፡ አዳራሹ በንጽሕና እንደተጠበቀ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች በአግባቡ በሁለት ረድፍ ቦታ ቦታ ይዘዋል፡፡ ከፊት ለፊት ሥዕለ ማርያም ተሰቅሏል፡፡ ቀና ብለን ግድግዳውን ስንመለከት በቁጥር በርከት ያሉ ፎቶ ግራፎች ግድግዳው ላይ በረድፍ ተሰቅለዋል፡፡ ማንነታቸውንና ለምን እንደተሰቀሉ ጠየቅን፡፡ ዲያቆን ደቅስዮስ በማይሰለች አንደበቱ አንድ በአንድ ማስረዳቱን ቀጠለ፡፡

“እነዚህ አባቶች የዚህ የአንድነት ማኅበሩ ባለ ውለታዎች ናቸው፡፡ እዚህ ፎቶግራፋቸውን የሰቀለንበት ምክንያት ለማኅበሩ ከነበራቸው ፍቅርና የአገልግሎት ድርሻ ከፍተኛውን ሥፍራ የነበራቸው በመሆናቸው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዚህ ዓለም በሕይወት አይገኙም፡፡ እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ ወደራሱ ጠርቷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት እናስባቸዋለን፡፡” በማለት ካስረዱን በኋላ ወደ እያንዳንዱ ፎቶ ግራፍ እየጠቆሙ ማንነታቸውን ይነግሩን ጀመር፡፡

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ /አባ ወልደ ንሣይ/ ማኅበሩን በጸሎት በማሰብና በመጎብኘት አባታዊ ምክራቸውን በመለገስ፤ አባ ገብረ ሥላሴ ተድላ ባዕድ አምልኮን በመቃወምና በማስተማር ይተጉ የነበሩ፤ ሊቀ ጉባኤ አበራ በቀለ በጸሎትና በምክር፤ አባ ይትባረክ፤ አባ ጴጥሮስ፤ መምህር ግርማ ከበደ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ፤ ዲያቆን ረዳ ውቤና ሌሎችንም አባቶች የቤተ ክርስቲያንና የዚህ አንድነት ኑሮ ማኅበር ባለውለታ መሆናቸውን ነገሩን፡፡ ከአዳራሹ ወጥተን የወተት ላሞች ማደሪያንና የብሎኬት ማምረቻ፤ የጓሮ አትክልት ሥፍራዎችን ጎብኝተን ለውይይት ወደ ተመረጠልን አዳራሽ አመራን ፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን የሚዲያ ክፍል አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት እና ጠንካራ ጎኖችን ለማበልጸግ እንዲቻል፤ የተሻለ አገልግሎት በጥራትና በብቃት ለመስጥት የተለያዩ አሳቦች ተነሥተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ወደፊት ማኅበሩ በሚዲያ ዘርፍ ሊያከናውናቸው የታሰቡትንና አሁን በመሠራት ላይ የሚገኙትን ተግባራት እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችም ትኩረት ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል በጋራና በመደጋፍ መሥራት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡