የጸሎት ጊዜያት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ 

ጥቅምት ፴፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? ትምህርት እንዴት ነው! አዲሱን ዓመት ከተቀበልን እነሆ ሁለት ወራት አለፈን፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ ልጆች! በዓመት ውስጥ ፫፻፷፭ (ሦስት መቶ ስድሳ አምስት) ቀናት አሉ፤ ከእነዚያ ላይ ከ፷ (ስድሳ) በላይ ቀናትን አሳለፍን፤ ለመሆኑ በሕይወታችን በእነዚህ ባለፉ ቀናት ምን ምን ነገር ተገበርን!? ትናንት ከነበራችሁ ዕውቀት (ግንዛቤ) ላይ ምን ጨመራችሁ? ምንስ ለውጥ አመጣችሁ? በሕይወታችን እያንዳንዷን ቀን ትርጉም ሊኖራት ያስፈልጋል፤ ጠዋት የሌሊቱን ሲመሽ የውሏችን ምን ምን ነገር እንደሠራን፣ ምን ለውጥ እንዳመጣን ሁሌ ማታ ራሳችንን እንጠይቅ! ያልሠራነው ካለ ለመሥራት፣ ያልገባን ያልተረዳንን ለመረዳት፣ መልካም ነገር ሆኖ ያላገኘነውን ለማግኘት መጣር ያስልጋል!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሌላው ዋና ነገር ደግሞ ቤተ ክርስቲያን በመሄድም መንፈሳዊውን ትምህርት በመማር በሥነ ምግባር ልትታነጹ ይገባል፤ በዕለተ ሰንበት በመሄድ ማስቀደስ መንፈሳዊ ትምህርት መማር አለባችሁ፤ አያችሁ ልጆች! በመንፈሳዊውም ሆነ በዘመናዊውም ትምህርት ተምራችሁ ማደግ አለባችሁ፤ ያኔ ለራሳችሁ ከዚያም ለቤተ ሰብ እንዲሁም ለአገራችሁ መልካም ነገርን መሥራት ይቻላችኋል፡፡ መልካም!!!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ባለፈው ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ከሆኑት ስለ ጸሎት ጥቂት ብለናችሁ ነበር! እንደ አቅማችን ልንጸልይ እንደሚያስልግ ነግረናችሁ ነበር፤ ለዛሬ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ስለ ጸሎት ጊዜያት እንማማራለን! በቅድስት ቤተ ክርስያን ሥርዓት አባቶቻችን ለጸሎት የምንተጋባቸው ጊዜያት እንዳሉ ሥረዓት አበጅተውልናል፤ ይህ መደረጉ ከእነዚህ ጊዜያት ውጪ አይጸለይም፤ ሳይሆን እግዚአብሔር ያደረገልንን ውለታ እያስታወስን በጸሎት ጊዜ ሐሳባችንን ሳይከፋፈል፣ ሌላ ነገር ሳናስብ ውለታውን፣ ፍቅሩንና ቸርነቱን ብቻ እያሰብን እንድንጸልይ ነው!

ነቢዩ ንጉሡ ዳዊት ‹‹…ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ …›› በማለት እንደገለጸው ምእመናን ለጸሎት በቀን ውስጥ  ሰባት ጊዜ መትጋት እንዳብን ሥርዓት ተበጀልን (ተሠራልን)፤ (መዝ.፻፲፰፥፻፷፬) ታዲያ ልጆች! እነዚህ ሰባቱ የጸሎት ጊዜያት የትኞቹ ናቸው? ምሳሌነታቸው ምንድን ነው? የሚለውን እንመልከት፡፡

ጠዋት ዐሥራ ሁለት ሰዓት በዚህ ሰዓት ለጸሎት መትጋት ያስልጋል፤ የመጀመሪያም ምክንያታችን ጨለማውን (ሌሊቱን) ጊዜ በሰላም አሳልፎ፣ ከክፉ ነገር ተጠብቀን ብርሃን እንድናይ ስለደረግን እናመሰግነዋን፡፡ አያችሁ ልጆች! እግዚአብሔር ቸር ነው! እኛ እንቅልፍ ሲወስደን የምናየው፣ የምንሰማው ምንም ነገር የለም፤ ታዲያ አምላካችን ቅዱሳን መላእክቱን ልኮ ምንም እንዳንሆን  ይጠብቀናል፤ ይህ ሰዓት አባታችን አዳም የተፈጠረበት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ የሚመጣበት ሰዓት ነው፤ ታዲያ በዚህ ሰዓት ለጸሎት ስንተጋ ለእኛ ሲል በፍርድ አደባባይ መቆሙን፣ የእኛ ፈጣሪ መሆንን እናስባለን፡፡

ጠዋት ረፋድ ሦስት ሰዓት፡- ይህ ሰዓት ጌታችንን መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ተራራ ለመውሰድ ጉዞ የተጀመረበት ነው፤ ሌላው ደግሞ በዚህ ሰዓት ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን እንደምትወልደው የምሥራች ያበሠረበት ነው፤ እንዲሁም ጌታችንን ለመረጣቸው አንድ መቶ ሃያ ቤተ ሰቦች (፲፪ (ዐሥራ ሁለት) ሐዋርያት፣ ፸፪ (ሰባ ሁለት) አርድዕት፣ ፴፮ ቅዱሳን አንስት እናቶቻችን) የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በጽርሐ ጽዮን የተሰጠበት ሰዓት ነው፡፡

ከቀኑ ስድስት ሰዓት (እኩለ ቀን)፡- ይህ ሰዓት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ብሎ ምንም በደል ሳይኖርበት በሐሰት ተከሶ በቀራንዮ አደባባይ በቅዱስ መስቀል ላይ የተሰቀለበት ሰዓት ነው፤ ይህንን ውለታውን እያስታወስን በጸሎት እንተጋለን፡፡

ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት (ቀትር)፡- ይህ ሰዓት ጌታችን በመስቀል ተሰቅሎ ብዙ መከራን ካደረሱበት በኋላ የተለያዩ ድንቅ ድነቅ ተአምራቶች ተፈጸሙ፤ ከዚያም ጌታችን ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው የለየበት ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ለጸሎት ስንበረታ ይህንን ውለታውን እናስታውሳለን፡፡ ለእኛ ሲለል መሞቱን፣ ለእኛ ሕይወት እንደሰጠንና ሰላምን እንዳጎናጸፈን እናስታውሳን፡፡

ከቀኑ ዐሥራ አንድ ሰዓት (ሠርክ)፡- ይህ ሰዓት ጌታችንን ቅዱስ ሥጋ ቅዱስ ዮሴፍና ቅዱስ ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው በኢዲስ መቃብር ያኖሩበት ሰዓት ነው፤ ሌላው ጌታችንን ወደ ሲዖል ወርዶ ነፍሳትን ያወጣበትም ነው፤ ለእኛ ሲል መቃብር ማደሩን እንዘክራለን፡፡

ማታ ሦስት ሰዓት (ምሽት)፡-ጌታችንን ሐሙስ ምሽት በጌተ ሴማኒ የጸለየበት ለቅዱሳን ሐዋርያትም ተግተው እንዲጸልዩ ያስተማረበት ነው፤ ሌላው በዚህ ሰዓትም አይሁድ ጌታችንን በይሁዳ እየተመሩ መጥተው ጌታችንን የያዙበት ነው፡፡ በሰዎች ላይ ክፉ ማድረግ ባልጀራን መካድ እንደማይገባ እንማርበታለን፡፡

ሌሊት ስድስት ሰዓት (መንፈቀ ሌሊት)፡- ይህ ሰዓት (ጊዜ) ጌታችንን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመቃብሩ ድንጋይ ሳይነሣ (መቃብሩ ዝግ እንደሆን) ሞትን ድል አድርጎ የተነሣበትና የእኛንም ትንሣኤ ያሠረበት ነው፡፡

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ እነዚህ የጸሎት ጊዜያት በሕይወታችን ልዩ ትርጉም ያላቸው ናቸው፤ ባለፈው ስለ ጸሎት ስንማማር ጸሎት ማለት አንደኛው ትርጉሙ ምስጋና ማለት ነውና ያደረገልንን እያስታወስን ለምስጋና በጸሎት መትጋት ያስፈልገናል፡፡

አያችሁ ልጆች! እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገልን ነገር ተነግሮ አያልቅም፤ ነገር ግን በተወሰነ መልኩ እንዲህ እንድናስታውሰው አባቶቻችን በጸሎት ጊዜ እንድያስታውስ አደረጉን፡፡ እንግዲህ በእነዚህ ጊዜያት ቆመን፣ ጊዜ መድበን ለመጸለይ ባያመቸንም ባለንበት ሆነን ግን በውስጣችን ይህን ማስታወስ፣ ለተወሰነ ደቂቃም በወስጣችን ጥቂት እንኳን ጸሎት ልናደርስ ያስልጋል፡፡

አምላካችን የምጸልየውን ጸሎት ተቀብሎልን በጎ ምላሽ ከእርሱ የምናገኘኝበት ያድርግልን! በቸርነቱ ይጠብቀን! ለአገራችን ለሕዝቦቿ መጸለይን እንዳትረሱ! በጸሎት ብዙ ጥቅም ይገኛልና፤ በርቱ፤ ይቆየን!!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!