ጳጉሜን ወር

ነሐሴ ፴ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በዓመት ውስጥ ካሉት ወራት የተለየች፣ ቀኖቿም ጥቂት እንዲሁም አጭር በመሆኗ የጳጉሜን ወር ተናፋቂ ያደርጋታል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን ኢትዮጵያ ካደላት ስጦታ አንዷ የሆነችውም ይህች ወር በዘመነ ዮሐንስ ስድስት ቀናት እንዲሁም ደግሞ በዘመነ ማርቆስ፣ በዘመነ ሉቃስና በዘመነ በማቴዎስ አምስት ቀናት ብቻ አላት፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን አስትምህሮ የጳጉሜን ወር የዓመት ተጨማሪ ወር እንላታለን፡፡  ምዕራባዊያኑ ግን ተጨማሪ ቀን እንደሆነች በማሰብ በዓመቱ ባሉ ወራት ከፋፍለዋታል፡፡

ጳጉሜን የሚለው ስያሜ “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም “ጭማሪ” ማለት ነው፡፡ በግእዝ “ወሰከ-ጨመረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ተውሳክ (ተጨማሪ) ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መዝገበ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገብ ቃላት፤ ገጽ ፱፻፭)

የጳጉሜን ወር ያሳለፍነውን ዓመት ትተን አዲሱን የምንቀበልበት፣ የክረምትን ወር አልፈን ወደ ጸደይ የምንገባበት እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከምድራዊ ወደ ዘላለማዊ እና ሰማያዊ ዓለም የምንገባባት ወቅት ነው፡፡ በዚህም በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጳጕሜን ወር የዓለም ፍጻሜ መታሰቢያ ተደርጋ ትታሰባለች፡፡

ጳጉሜን በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም መምጣት ወይም የፍርድ ቀን የዓለም መከራና ችግር እንዲሁም ሥቃይ ማብቂያ የመሆኑ ማሳያ ናት፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የክረምት ማብቂያና ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ ስለሆነ ነው፡፡ በአምላካችን መልካም ፈቃድ ወደ ሌላ አዲስ ዘመን ስንሻጋገር አዲስ ተስፋና በጎ ምኞትም ይዘን ስለሆነ ይህም የተስፋይቱ መንደር ርስተ መንግሥተ ሰማያትን አማላካች ነው፡፡ በዳግም ምጽአት ጊዜም ጻድቃን አዲሲቷን ምድር መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ተዘጋጅተው “ኑ የአባቴ ብሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” የሚባሉባት እንደመሆኑ ጳጉሜን ወር አዲሱን ዓመት ለመቀበል የምንዘጋጅበት ጊዜ ነው፡፡ (ማቴ.፳፭፥፴፬)

ይህም የሚያመለክተን በዚህች በተሰጠን የጭማሪ ወር ተጠቅመን ለነፍሳችን ድኅነት የሚሆነን ስንቅ መያዝ እንዳለብን ነው፡፡ ስለዚህም ከፈቃድ ጾም መከካል አንዱ የሆነው ጾመ ዮዲትን (የዮዲት ጾምን) እንጾማለን፡፡ መበለቲቱ ዮዲት በጾምና በጸሎት ተወስና በሕገ እግዚአብሔር በምትኖርበት ጊዜ በእርሷና በሕዝቡ ላይ የመጣውን መከራና ችግር አምላክ እንዲፈታላት የያዘችው ሱባኤ ከእግዚብሔር ዘንድ ምላሽና መፍትሔ እንዳሰጣት ሁሉ እኛም የችግራችን ቋጠሮ እንዲፈታልንና ካለንበት የመከራ አረንቋ አውጥቶ ወደ በጎ ዘመን እንዲያሸጋግረን ተስፋ በማድረግ ልንጾም እና በጸሎት ልንማጸን ይገባል፡፡

የፋርሱ ንጉሥ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ “ጠላት አጥፋ፤ ድንበር አስፋ፤ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና” ብሎ ለጦር አበጋዙ ሆሎፎርኒስ ትእዛዝ አስተላልፎ  ሕዝቡን እንደበደለው ሁሉ በእኛ በኢትዮጵያውያን ላይም እየደረሰ ያለው ግፍ መሆኑ ከማንም የሚደበቅ ነገር አይደለም፡፡ ሕዝበ እስራኤላውያንም በዚያን ጊዜ በምሬት አልቅሰዋል፡፡ እኛም በኀዘን ላይ እንደመሆናችን ይህ መከራ ጊዜ እስኪያልቅ ድረስ ማንባታችን አይቀሬ ነው፡፡

ሕዝቡ ግን እንደኛ በኀዘንና በልቅሶ ብቻ አልቀረም፡፡ ማቅ ለብሰው፣ አመድ ነስንሰውና ድንጋይ ተንተርሰው ወደ ፈጣሪያቸው በመጮህ መለመን ጀመሩ እንጂ። የጦር አበጋዙ ሆሎፎርኒስም በጭካኔ የበለጠ ሕዝቡን በማሠቃየት ውኃ የሚቀዱበትን ስፍራም ጭምር ተቆጣጥሮት ነበር፤ በግዴታ ማርኮም እጅ እንዲሰጡ አደረጋቸው፡፡ የእኛ ነበራዊ ሁኔታ ከዚህ አይለይም፡፡ ዳር ድንበራችን ተጥሶና ሰብአዊነታችን ተደፍሮ መኖር እስኪያቅተን ድረስ ግፍ ተፈጽሞብናል፡፡ የአካላዊ ሆነ የመንፈሳዊ ጥቃት ሰላባ ከሆንንም ሰንብተናል፡፡ ስለዚህም መፍትሔ እናገኝ ዘንድ ወደ ፈጣሪያችን አብዝተን መጮህ አለብን፡፡

ሕዝበ እስራኤል ሥቃያቸው በበዛ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር አመልክተዋል፡፡ በዚያም ጊዜ አንድ በአካባቢው ይኖር በነበረ ዖዝያን በተባለ አንድ ሰው ምላሽ እንደተሰጣቸው መጽሐፈ ዮዲት ላይ ተመዝግቦ እናገኘዋለን፡፡ እርሱም አምላክ ጸሎታቸውን እንዲሰማቸው ለአምስት ቀናት ይጾሙና ይጸልዩ ዘንድ ነግሯቸዋል፡፡ (ዮዲ. ፪፥፪-፳፰፣፬፥፲፫)

ሆኖም ግን ሕዝቡ ሐሳቡን ከመቀበል ይልቅ ንጉሥ ናቡከደነጾርን ከእነ ጦር ሠራዊቱ ተዋግተው ለመርታት ካልሆነ ግን እጅ ለመስጠት ወስነዋል። በዚህ ጊዜ መበለቲቱ ምክክራቸውን ከገሠጸቻቸው በኋላ ማቅ በመልበስ፣ አመድ በመነስነስና ድንጋይ በመንተራስም ሱባኤ ገብታለች። በሦስተኛው ቀንም እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቧን የምታድንበትን ጥበብ እንደገለጸላት ከታሪኳ እንረዳለን፡፡ ዮዲትም እግዚአብሔር የሰጣትን ውበት ተጠቅማ ሕዝቧን ከጥፋት የምትታደግበትን ጥበብ በመጠቀም ጠላታቸውን ድል ነሥታለች፡፡ (ዮዲ. ፱፥፲፫-፳፯፣ ፲፥፳፫፣፲፩፥፳፫፣ ፲፪፥፪፣፲፫፥፳)

እምነት ኃይልን ታደርጋለችና አምላካችን እግዚአብሔር ችግራችን እንደሚፈታልን በማመን በጾምና በጸሎት ብትንጋ ምላሽ እናገኛለን፡፡ በጾምና በጸሎት የተጋችው ዮዲት ጠላቶቻን ድል ማድረግ እንደምትችል በማመን ካሉበት ድረስ በመሄድ የተፈጥሮ ውበታን ተጠቅማ አሸንፋለች፡፡

ከዚያ ሁሉ አስቀድማ ግን ማድረግ ስላሰበችው ነገር የአምላኳን ርዳት በሱባኤ ጠይቃ ስለነበር ያለ ምንም ፍራቻ ለምታምንበት ነገር ሽንፈትም ሆነ ውድቀትን ሳታሳብ ያለጥርጣሬ ጠላቷን ተጋፍጣ በራሱ ግዛቱ አሸንፋዋለች፡፡ በዚህም ከራሷ አልፎ ለሀገሯ ሕዝብ መዳንና የሀገር ሰላም መገኛ ነበረች፡፡ እኛም ይህን ያለጥርጣሬ በማመን በዚህ በከፋ ወቅት በአንድነት ሆነን አምላካችን እንለምን፤ ኅብረት ጥንካሬ ነውና፡፡ የተሰጠንን የጊዜ ጭማሪ በመጠቀምም በጾም ተወስነን አብዝተን እንማጸን፡፡ እንደ ዮዲት ማቅ ለብሰን፣ አመድ ነስንሰንና ድንጋይ ተንተርሰን አብዝተን ልንጾምና ልንጸልይ ይገባል፡፡ ከመከራና ሥቃይ እንዲሰውረን፣ የእርስ በእርሱን ጦርነት እንዲገታልን፣ ያጣነውን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነትን እንዲመልስልን መጸለይና መጾም ያስፈልጋል፡፡

እንዲሁም በበዓለ በቅዱስ ሩፋኤል ጳጉሜን ሦስት ሰማያት የሚከፈቱበት (ርኅዎተ ሰማይ) በመሆኑ በዚህች በየዓመቱ እንደምናደርገው ሁሉ በዚህች በተከበረች ዕለት የቸርነት መልአኩ ለነፍሳችን ድኅነት ያሰጠን ዘንድ አብዝተን እንማልዳለን፤ በጸበሉም እንጠመቃለን፡፡

አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ጸሎታችን ሰምቶና ጾማችንን እንዲሁም ምግባራችንን ሁሉ ተቀብሎ ለምሕረት ያደርግልን ዘንድ ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡