‹‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ›› (ምሳ. ፩፥፯)

ዲያቆን ዘካርያስ ነገደ

ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ፥ ልጁ ንጉሥ ሰሎሞን ደግሞ በምሳሌው የጥበብ መጀመሪያ ፈሪሃ እግዚአብሔርን ገንዘብ ማድረግ መሆኑን በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ጽፈዋል፡፡ (መዝ. ፻፲፥፲፤ ምሳ. ፩፥፯) ሰው የስሜት ሕዋሳቱን ተጠቅሞ በማየት፣ በመዳሰስ፣ በማሽተት፣ በመቅመስና በመስማት ጥበብን ገንዘብ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ከልደቱ እስከ ሞቱ የሚፈጽመውና ከተሰጡት ጸጋዎችም አንዱ ይህ ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ ጥበብን በእግዚአብሔር ፈቃድ ሊያገኝም ይችላል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለቅዱሳን እርሱ በወደደ እንዲያውቁት ይገለጥላቸዋል፡፡ በነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል›› እንዳለው ጥበብን ገንዘብ ለማድረግ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ያስፈልጋል፡፡ (ኢሳ. ፲፩፥፪) ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ፥ መንገድህን አመልክተኝ፤ ፍለጋህንም አስተምረኝ›› በማለት የለመነው ከእግዚአብሔር የሆነውን ጥበብ ፍለጋ ነው፡፡ (መዝ. ፳፬፥፬)

‹‹እግዚአብሔርን መፍራት ለጥበብ ዘውድዋ ነው›› እንደተባለ ከእግዚአብሔር የሆነው ጥበብ መጀመሪያው እርሱን መፍራት ነው፤(ሲራክ ፩፥፲፰)፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት ስንል በቁጣው ይቀሥፈኛል፣ በኃያልነቱ ያጠፋኛል ከሚል የሥጋትና የጭንቀት መንፈስ ሳይሆን የዓለም ፈጣሪ እርሱ መሆኑን በማመን በፈቃዱ መገዛትና መኖር ማለታችን ነው፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን በመጽሐፈ መክብብ ‹‹የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ ስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፥ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ትእዛዙንም ጠብቅ›› በማለት እግዚአብሔርን መፍራት ትእዛዙን መጠበቅ ማለት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ (መክ. ፲፪፥፲፫) በተመሳሳይ በመጽሐፈ ሲራክ ‹‹እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ለሕጉ ይገዛል፤ ወደ እርሱም ፈጥነው የሚሄዱ ሰዎች ፈቃዳቸውን ያገኛሉ›› ተብሏል፡፡     (ሲራ. ፴፭፥፲፬)

ቅዱስ ዳዊት ደግሞ በመዝሙሩ ስለ እግዚአብሔር ትእዛዛት፣ ስለ ሥርዓቶቹና ስለ ሕግጋቱ ‹‹የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስን ይመልሳል፤ የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው፤ ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል፡፡ የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፥ ልብንም ደስ ያሰኛል፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፤ ዓይንንም ያበራል፡፡›› ደግሞም ‹‹ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው›› በማለት ዘምሯል፡፡ (መዝ. ፲፰፥፯-፲፤ ፻፲፰፥፻፭)

በእግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ በራስ ፈቃድና ሐሳብ በመኖር እንዲሁም የእግዚአብሔርን ሕልውና በመካድ ከትእዛዛቱ በመራቅ ከእግዚአብሔር የሆነው ጥበብ አይገኝም፡፡ እግዚአብሔር ከሚጸየፋቸው ክፉ ሥራዎች መራቅና በመልካም ሥራዎች መታነጽ ያስፈልጋል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ እግዚአብሔርን ፍራው፥ ከክፋትም ሁሉ ራቅ፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ዐመፃን ይጠላል፤ ጥልንና ትዕቢትን፥ ክፉ መንገድንም ይጠላል፡፡ ልብህ በኀጢአተኞች አይቅና፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር›› ይላል፡፡ (ምሳ. ፫፥፯-፰፤ ፳፫፥፲፯-፲፰)

እግዚአብሔርን በመፍራት ለሚኖሩት የሚከፈላቸው ዋጋ የተገለጸ ነው፤ ነቢዩ ዳዊትም ሆነ ጠቢቡ ሰሎሞን በሥልጣን ዙፋናቸው ብዙ ዘመን እንደቆዩ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፏል፤ ሁለቱም ከእግዚአብሔር ስለሆኑና የእርሱን ሐሳብ ስለፈጸሙ በመንግሥታቸው አርባ፥ አርባ ዓመት ነግሠው አልፈዋል፡፡ (፩ነገ. ፪፥፲፤ ፲፩፥፵፩) ‹‹እግዚአብሔርን መፍራት ዘመንን ታረዝማለች፤ የኀጥኣን ዕድሜ ግን ታጥራለች›› ተብሎ የተነገረው በአባቶቻቸውን ሕይወት ተፈጽሟል፡፡ (ምሳ. ፲፥፳፯)

እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች  በተስፋ ይኖራሉ፤ ያለ ተስፋ ሃይማኖትም ሆነ ምግባር ሊኖር አይችልም፡፡ አበ ብዙኃን አብርሃም ከሀገሩ፥ ከዘመዶቹ ርቆ ወደማያውቀው ሀገር የሄደው በተስፋ ነበር፡፡ ከተሰጠው ተስፋ አንዱ ምድረ ርስትን መውረስ ነው፡፡ (ዘፍ. ፲፭፥፯-፳፩) ይህች የተስፋ ምድር ለአማናዊዉ ለሀገረ ሕይወት መንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነበረች፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች በሃይማኖት ቢኖሩ፥ በጥሩ ሥነ ምግባር ቢጠነክሩ ተስፋ የሚያደርጓት ዓይን ያላያትን፥ ጆሮም ያልሰማትን፥ በሰው ልቡና ያልታሰበችውን እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጃትን ርስታቸው መንግሥተ ሰማያትን የመውረስ ተስፋ አላቸው፡፡ ‹‹እግዚአብሔርን ለሚፈራ ጠንካር መታመን አለው፥ ለልጆቹም መጠጊያ ይኖራል፡፡›› (ምሳ. ፲፬፥፳፮)

በሃይማኖት ጸንተው፥ በምግባር ጎልምሰው ለእግዚአብሔር የታመኑ ቅዱሳን ባለጠግነትን ከክብር ጋርም ይጎናጸፋሉ፡፡ እነዚህም በመንፈስ ድሆች የተባሉ ሀብት፣ ሥልጣን ወይም ዕውቀት ሲኖራቸው ባላቸው ሳይመኩና ሳይታበዩ እግዚአብሔርን በመፍራት ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ የትሕትናን ሥራ በመሥራታቸው በኋለኛው ዘመን መንግሥቱን በመውረስ የሚያገኙት ናቸው፡፡ ‹‹እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት፣ ክብርን፣ ሕይወትም ነው፡፡››(ምሳ. ፳፪፥፬)

የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ኢዮሣፍጥ በእያንዳንዱ የይሁዳ ከተማ ውስጥ ፈራጆችን ከሾመ በኋላ ‹‹ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አትፈርዱምና፥ እርሱም በፍርድ ነገር ከእናንተ ጋር ነውና የምታደርጉትን ተመልከቱ፡፡ አሁንም እግዚአብሔርን መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን፤ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ዘንድ በደልና ለሰው ፊት ማድላት፣ መማለጃም መውሰድ የለምና ሁሉን ተጠንቅቃችሁ አድርጉ›› በማለት አሳስቧቸዋል፡፡ (፪ ዜና. ፲፱፥፭-፯)

ሆኖም በዚህ ትውልድ እንደሚታየው እግዚአብሔርን መፍራት ቀርቶ ከነመኖሩም በመዘንጋት ብዙ መከራዎች በአማንያን ላይ በልበ ደንዳኖች ግፍ እየተፈጸመ ነው፡፡ ዕርቅና ሰላምን ማስገኘት ያለባቸው ምድሪቱን እንዲገዙና ሕዝቡን እንዲጠብቁ የተሰየሙ ባለሥልጣናትም የሚያይ አምላክ የሌለ ይመስል ከግፈኞች ጋር ሲተባበሩ ይስተዋላሉ፤ በራስ ሐሳብና ጉልበት መመካት ግን ትርፉ ውድቀት ብቻ ነው፡፡

ባለሥልጣናት ፈሪሃ እግዚአብሔርን ገንዘብ በማድረግ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በተሰጣቸው ሥልጣን ፍትሕ ርትዕ ሊያሰፍኑ ይገባል እንጂ ከበዳዮችና ከገፊዎች፥ ከአሳዳጆችና ከገዳዮች ጋር ሊተባበሩ አይገባቸውም፡፡ እግዚአብሔር የሚፈሩትን በበረከቱ ይጎበኛቸዋል፤ ባለሥልጣን ሆነ ግለሰብ፣ ባለጸጋ ይሁን ደሃ፣ የተማረ ወይም ያልተማረ፣ ወንድ ሴት አይልም፤ ሁሉንም ያያል፤ ለሁሉም እንደ ዋጋው ይከፍላል፡፡ ‹‹እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥ ትንንሾችንና ትልልቆችን ሁሉ ይባርካል›› እንዲል፡፡ (መዝ. ፻፲፫፥፳፩)

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጸሎቷ ‹‹ኃይልን በክንዱ አደረገ፤ በልባቸው ሐሳብ የሚኮሩ ትዕቢተኞችንም በታተናቸው፤ ብርቱዎችንም ከዙፋናቸው አዋረዳቸው›› (የዘወትር ጸሎት) እንዳለች በትዕቢት አሽክላ የተያዙትን ግን ያዋርዳቸዋል፤ (ሉቃ. ፪፥፶፩-፶፪)፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ፍጡራን የሆን እኛ ከእግዚአብሔር ፈቃድ በመራቅ ከተጓዝንበት መመለስ ከወደቅንበትም ትቢያ እርሱን በመፍራት ልንነሣ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር እርሱን በመፍራት እንደ ሐሳቡ እንድንኖር ይርዳን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት እግዚአብሔር