ledeteegzie.jpg

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል

ledeteegzie.jpg

የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን አስመልክቶ በመካነ ድር አድራሻችን እንዲሁም በስልክ ተደጋጋሚ ጥያቄ በመጠየቁ ይኽንን አስመልክተን ከማኅበረ ቅዱሳን የሚዲያ ዋና ክፍል ኃላፊ ከሆኑት ከዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ጋር ጥቂት ቆይታ አድርገን የሚከተለውን ምላሽ አግኝተናል መልካም ንባብ፡፡

አማርኛ መካነ ድር፡- ብዙ ምዕመናን በስልክና በኢሜል የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አርብ ነውና የሚውለው፣ ይበላል? ወይስ አይበላም? የሚል ጥያቄ አንስተዋል፤ የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዐት መሠረት አድርገው ምላሽ ቢሠጡን?
 
ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ፡- ፆመን በመብልና በደስታ ከምናከብራቸው በዓላት ውስጥ ሦስቱ ልደት፣ ጥምቀትና ትንሣኤ ናቸው፡፡ ‹‹ወእምድኅረዝ ፍትሑ ፆመክሙ እንዘ ትትፈሥሁ ወእምትሐስዩ ሶበ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ተንስአ እምነ ምውታን….››፣ ‹‹….ከዚህ በኋላ ፈፅሞ ደስ እያላችሁ ፆማችሁን በመብልና በመጠጥ አሰናብቱ…›› እንዲል ፍትሐ ነገሥት ከትንሣኤ ጋር አነካክቶ በሚናገረው አንቀጽ፡፡ ትንሣኤ ሁሌም እሑድ ቀን የሚውል በመሆኑ ቀዳሚት ስኡርን በአክፍሎት ከመፆም በቀር ሌላ ተጨማሪ ትዕዛዝ የሌለበት መሆኑን የቤተ ክርስቲያናችን የሥርዐት መጽሐፍ ያስረዳሉ፡፡ ጥምቀትና ልደት ግን ከአዋድያት በዓላት ውስጥ ስለሆኑ የሚውሉበት (የሚከብሩበት) ዕለት የሚለዋወጥ ነው፡፡ ረቡዕና አርብን ጨምሮ በማንኛውም ዕለት ቢውሉ የሚበላ (የማይፆም) መሆኑን በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡ ለምሳሌ፡- በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት ፆመ ነቢያት 44 ቀን የሚፆም ሲሆን 40 ቀን የሙሴ፣ 3 ቀን የአብርሃም ሶርያዊው አንዷ ቀን ደግሞ ጋድ በመሆን ስለሚፆም በዓሉ ረቡዕም ዋለ አርብ ሁልጊዜ ይበላል እንጂ አይፆምም፡፡
በመሆኑም ይኽ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አርብ ዕለት የሚውል ቢሆንም የሚበላ (የማይፆም) መሆኑን የቤተ ክርስቲያናችን የሥርዐት መጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡
አማርኛ መካነ ድር፡- በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐት መሠረት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን እንዴት ማክበር አለብን?

ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ፡-
ከላይ የጠቅስናቸው ሦስቱም በዓላት በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐት መሠረት ቅዳሴያቸው በመንፈቀ ሌሊት ይከናወናል፡፡ ከቆረብን በኋላም ፆሙን በመበል፣ በመጠጥ፣ በፍፁም መንፈሳዊ ደስታ ማሰናበት እንደሚገባን በመጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል፡፡ መንፈሳዊ ደስታ ሲባል ግን ጥቅም (ረብ) የሌለው ነገር በመናገር ማክበር እንደሌለብን (እንደማይገባን) የተረዳ ነው፡፡ አንድ ሰው መብል መጠጥ በማብዛት ሊደሰት አይገባውም፤ በእውነት ሌሎችም በዚህ አልተጠቀሙም፡፡ እህልን ልንሄድበት ልንቆምበት ነው እንጂ ልንሰናከልበት አልተሰጠንምና፡፡
በእነዚህ በዓላት አንድ ሰው ከቤተሰቡ በሞት እንኳ ቢለየው አያልቅስ ምክንያቱም በበዓላቱ የምናገኘው ደስታ ካጣነው ቤተሰብ ጋር የሚነፃፀር ስላልሆነ፤ በዚህ ዓለም በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ያገኘ ሰው አንድ ልብስ ጠፋብኝ ብሎ እንደማያዝን፤ በጌታችንም በልደቱ፣ በጥምቀቱና በትንሣኤው ያገኘነው መንፈሳዊ በረከት ከፍተኛ ስለሆነ በእነዚህ እለታት ማዘን ማልቀስ ፈፅሞ የተከለከለ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን የሥርዐት መጽሐፍት ቀኖና ይገባዋል ይላሉ፡፡

አማርኛ መካነ ድር፡-
በመጨረሻም የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
 
ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ፡- እንግዲህ በመጽሐፍትም እንደተጠቀሰው በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት እንዲያደርግልን የእርሱ ፈቃድ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡