የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፮

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ፲፮ ቀን ፳፻፲ .

ጋብቻ በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በሁለት ተፈላላጊ ፆታዎች ስምምነት የሚገነባ መንፈሳዊ ተቋም ነው፡፡ “ወንህነሰ ንብል ከመ ሰብሳብ ንጹሕ ወልደት ዘአልቦ ርኵስ፤ እስመ ፈጠሮሙ እግዚአብሔር ለአዳም ወለሔዋን ከመ ይብዝኁ ሕዝብ፤ እኛስ ጋብቻ ንጹሕ እንደ ኾነ፣ ልደትም ርኵሰትም እንደሌለበት እንናገራለን፡፡ ሕዝቡ ይበዙ ዘንድ እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን ፈጥሯቸዋልና” እንዳሉ ቅዱሳን ሐዋርያት (አመክንዮ)፡፡ ስለኾነም ሃይማኖትን የሚያስክድ፣ ንጽሕናን የሚያሳጣ ፈተና እንደዚሁም ሞት ካልኾነ በቀር መሠረቱ እግዚአብሔር ነውና ጋብቻ እንዲሁ አይፈርስም፡፡

ለዚህም ነው ባልና ሚስት ሥርዓተ ተክሊል በሚፈጽሙበት ዕለት በሕመም፣ በችግር ወይም በሌላ ጥቃቅን ምክንያት እንደማይለያዩ በእግዚአብሔር ፊት የመሐላ ቃላቸውን የሚሰጡት፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ከሚገጥመን ልዩ ልዩ ፈተና ሁሉ እንዲጠብቀንና መፍትሔ እንዲያመጣልን ወደ ትዳር ሕይወት ከመግባታችን በፊትም ኾነ ከገባን በኋላ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ የሕይወት መመሪያችን ብናደርግ ሕይወታችን የተስተካከለ ይኾናል፡፡ በእግዚአብሔር ቃል የተሰበረ ልብ መንፈሳዊነትን ያላብሳልና፡፡ መንፈሳዊነት ደግሞ ፍቅርን እንጂ ጥላቻን አያስቀድምም፤ መቀራረብን እንጂ መለያየትን አይመርጥም፡፡

ጌታችን “ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ዂሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል፡፡ ዝናብም ወረደ፤ ጐርፍም መጣ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንም ቤት ገፋው፡፡ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም፤” በማለት እንደ ተናገረው (ማቴ. ፯፥፳፭)፣ ቃሉን በሕይወቱ የተገበረ ክርስቲያን ምንም ዓይነት ፈተና ቢደርስበት ሳይሰናከል ሃይማኖቱን ይጠብቃል፡፡ እንደዚሁ ዂሉ በጋብቻ የሚኖሩ ክርስቲያኖችም ልዩነታቸውን በማጥበብ በጋራ ይኖራሉ እንጂ መፋታትን አይመርጡም፡፡

በመንፈሳዊ ፍቅር የሚያምን ክርስቲያን በየሰበቡ ጥላቻን አያመነጭም፤ ትዳሩን ለማፍረስም አይጣደፍም፤ ነገሮችን በጥንቃቄ ይመረምራል እንጂ፡፡ ፍቅር፣ ትዕግሥትን፣ እዝናትን፣ መተሳሰብን፣ ትሕትናን፣ ቅንነትን፣ ጽድቅንና ተስፋን ያመጣልና፡፡ “ፍቅር ያስታግሣል፤ ያስተዛዝናል፤ ፍቅር አያቀናናም፤ ፍቅር አያስመካም፤ ፍቅር ልቡናን አያስታብይም፡፡ ፍቅር ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም፤ አያበሳጭም፤ ክፉ ነገርን አያሳስብም፡፡ ጽድቅን በመሥራት ደስ ያሰኛል እንጂ፣ ግፍን በመሥራት ደስ አያሰኝም፡፡ በዂሉ ያቻችላል፤ በዂሉም ያስተማምናል፡፡ በዂሉም ተስፋ ያስደርጋል፤ በዂሉም ያስታግሣል፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ (፩ኛ ቆሮ. ፲፫፥፬-፯)፡፡

ጋብቻ ክቡር፣ መኝታውም ቅዱስ እንደ መኾኑ አንድ ባል ለአንዲት ሚስት፤ አንዲት ሚስት ለአንድ ባል ኾነው እንዲኖሩ እግዚአብሔር አምላካችን ሥርዓት ሠርቶልናል፡፡ አምላካችን “ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም፤ ስለዚህ የምትረዳውን ጓደኛ እንፍጠርለት” እንጂ “የሚረዱትን ጓደኞች እንፍጠርለት” አላለም (ዘፍ. ፪፥፲፰)፡፡ ይህም አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት፤ አንዲት ሴት ለአንድ ወንድ መፈጠሯን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህን አምላካዊ ሕግ በመጣስ በሚስት ላይ ሌላ ሚስት፤ በባል ላይ ሌላ ባል መደረብ ነውርም ኀጢአትም ነው፡፡ ከብዙ ወንዶች (ሴቶች) ጋር መዘሞት፤ የትዳር አጋርን በየጊዜው መቀያየር የእግዚአብሔርን ሕግ መተላለፍ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ቅዱሱን ጋብቻ ማሳደፍ፤ ሰውነትንም ማቈሸሽ ነው፡፡ እንደዚህ የምናደርግ ሰዎች ካለን ይህ ልማዳዊ ኀጢአት ፍጻሜው ውርደትና ሞት መኾኑን በመረዳት በንስሓ ልንመለስ ይገባናል፡፡

፩.፯ ፍቺ እና ሁለተኛ ጋብቻ

ጋብቻ፣ ዓላማውም ጠባዩም አንድነት ነው፡፡ ስለዚህም በጋብቻ ሕይወት መፋታት እንደማይገባ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ ምክንያቱም ጋብቻ እስከ ሞት ድረስ አብረው የሚዘልቁበት፣ ዘርን የሚተኩበትና ልጆችን ወልደው ለቁም ነገር የሚበቁበት፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተው ከኖሩበት ደግሞ ሰማያዊ መንግሥትን የሚወርሱበት የአንድነት ሕይወት ነውና፡፡ ስለኾነም እንዲሁ በቀላሉ አይፈርስም፤ ጥንዶቹም በሰበብ አስባቡ ሊፋቱ አልተፈቀደላቸውም፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ባልና ሚስት ሕይወት ሲያስተምር “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፡፡ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፡፡ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይኾናሉ፡፡ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” በማለት አንድነታቸው እንደማይለያይ ማስተማሩ መፋታት ተገቢ አለመኾኑን ያስረዳናል (ማቴ. ፲፱፥፭-፮)፡፡

በተመሳሳይ ትምህርት “እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ አንድ አድርጎ ጠብቆልን የለምን? እርሱም የሚፈልገው ምንድር ነው? ዘር አይደለምን? ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ፤ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል፡፡ ‹መፋታትን እጠላለሁ› ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፤” በማለት ባልና ሚስት ሊፋቱ እንደማይገባ ነቢዩ ሚልክያስ ተናግሯል (ሚል. ፪፥፲፭)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም “ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፤ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር፡፡ ወይም ከባልዋ ትታረቅ፤ ባልም ሚስቱን አይተዋት … በሚስት ታስረህ እንደ ኾንህ መፋታትን አትሻ” በማለት ፍቺ ተገቢ አለመኾኑን አስተምሯል (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፲-፳፯)፡፡

መምህራነ ቤተ ክርስቲያንም የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃለ ትምህርት መነሻ አድርገው “ወአልቦ ዘይጸልዕ እግዚአብሔር ዘየዐቢ ኃጢአት ዘእንበለ ዘይድኅር ብእሲቶ ወያወስብ ካልእተ …፤ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ከሚያገባ ሰው የበለጠ እግዚአብሔር የሚጠላው ኀጢአት የለም፡፡ ይህ ሥራ በእግዚአብሔር ዘንድ የተናቀ ነውና፡፡ በነቢያትና በሐዋርያት ሥልጣንም የተለየ (የተወገዘ) ነውና” ሲሉ የባልና ሚስት መፋታት በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ተግባር መኾኑን ይናገራሉ (ተአምረ ማርያም፣ ፲፩ኛ ተአምር፣ ቍ. ፳፰)፡፡

የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በፍቅርና በአንድነት መኖርን የሚሰብክ በመኾኑ ፍቺን አጥብቆ ይከለክላል፡፡ ከተጋቡ በኋላ የሕይወት መሰናክሎችን በመፍታት አብሮ መኖር እንጂ መለያየት ክርስቲያናዊ ሥርዓት አይደለምና፡፡ በመኾኑም ችግሮችን በውይይት በመፍታት፣ በመመካከርና በመፈቃቀር ተስማምቶ እስከ ሞት ድረስ መኖር ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በትዳር ሕይወት እጅግ የከበደና መፍትሔ የሌለው ችግር ሊመጣ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ለጉዳዩ መፍትሔ በሚያመጣ መልኩ መወያየት፣ ከንስሓ አባት ጋር መመካከር፣ በጾም በጸሎት መትጋትና እግዚአብሔርን መማጸን ይገባል፡፡

ኾኖም በመካከላቸው በሃይማኖት ወይም ሊፈታ በማይችል ልዩ ልዩ ምክንያት ለጉዳትና ለሞት የሚያደርስ ግጭት በተደጋጋሚ ከተከሠተ፤ አንዳቸው ወይም ሁለቱም ከትዳር ውጪ ከሔዱ (ዝሙት ከፈጸሙ) እነዚህን ችግርች በምክክር መፍታት፣ በንስሓም ማጽዳት ካልተቻለ መፋታት ይፈቀዳል፡፡ ከዂሉም በላይ ከሁለቱ አንዱ በሞት ከተለየና በሕይወት የቀረው አካል ጋብቻ መመሥረት ከፈለገ ሁለተኛ ማግባት ይቻላል፡፡ ያም ኾኖ ግን በሕገ ቤተ ክርስቲያን ከተጠቀሰው ምክንያት በቀር መፋታት አይገባም (ፍትሐ ነገ. አን. ፳፬፣ ቍ. ፲፩-፲፯)፡፡

ከላይ በተጠቀሱ ምክንያቶች መፋታትና ሁለተኛ ጋብቻን መመሥረት ቢቻልም ከዚያ በፊት ችግሮችን በውይይት ለማስተካከልና ለመስማማት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባን መዘንጋት የለብንም፡፡ ምክንያቱም ‹‹መፋታት ይፈቀዳል›› በሚል ሰበብ በሚረባውም በማይረባውም ጉዳይ ጋብቻን ማፍረስ ተገቢ አይደለምና፡፡ ነገር ግን እጅግ የከበደና መፍትሔ የሌለው ችግር ከመጣ ቀደም ሲል እንደ ገለጽነው መፋታትና አስፈላጊ ከኾነም ሁለተኛ ጋብቻ መመሥረት ይፈቀዳል፡፡ በዚህ መልኩ የተፋቱ ጥንዶች አስፈላጊነቱ ተጣርቶ እስከ ሦስት ጊዜ ድረስ ጋብቻ ሊፈጽሙ እንደሚችሉ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ተወስኗል፡፡ ከሦስት ጊዜ በላይ ጋብቻን መፈጸም ግን እንደ ዝሙትና እንደ ርኵሰት ይቈጠራል፡፡

“እስመ አውስቦ ቀዳማዊ ዘበአሐቲ ብእሲት፤ ወአውስቦሰ ዳግሚት ካልእት ተሐፅፅ እምቀዳሚት፡፡ ወአውስቦሰ ሣልስ ምኑን ውእቱ፤ ወአልቦ በኀቤነ እምድኅረዝ አውስቦ ሕጋዊ፤ በአንዲት ሴት የሚኾን (የሚፈጸም) የመጀመሪያ ጋብቻ ደግ ነው፤ ሁለተኛይቱ ግቢ ከመጀመሪያይቱ ታንሳለች፡፡ ሦስተኛው ግቢ ግን የተናቀ ነው፡፡ ከሦስተኛው ግቢ በኋላም መጽሐፍ ያዘዘው ግቢ የለም፤” እንዲል (ፍት. ነገ. አን. ፳፬፣ ክፍ. ፩፣ ቍ. ፵፮-፵፫)፡፡ ጉዳዮቹን በመጠኑ ለመዳሰስ ያህል፣ ሁለተኛ ጋብቻ (ፍቺ) ከሚፈቀድባቸው መንገዶች መካከል ዋና ዋናዎቹን እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል፤

ይቆየን