የዲላ ዮኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ የተመሠረተበትን አስራ ስድስተኛ ዓመቱን አከበረ

መጋቢት 6 ቀን 2005 ዓ.ም.


በዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ

በማኅበረ ቅዱሳን በዲላ ወረዳ ማእከል ሥር የሚገኘው የዲላ ዮኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ የተመሠረተበትን ዐሥራ ስድስተኛ ዓመቱን በዋለሜ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን በደመቀ ሁኔታ አከበረ፡፡

ግቢ ጉባኤው ከየካቲት 29 ቀን እስከ መጋቢት 1 ቀን 2005 ዓ.ም የተመሠረተበትን በዓል ሲያከብር በማኅበረ ቅዱሳን የአዋሣ ማእከል ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፏል፡፡ ማእከሉ በወከለው በአቶ ታደሰ ፈንታ በኩል ባስተላለፈው መልእክት “ዛሬ የምሥረታ በዓላችሁን የምታከብሩ ተማሪዎች ከመደበኛው ትምህርታችሁ ጎን ለጎን መንፈሳዊ ተግባራችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪያችንን በማቅረብ ነው” በማለት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡

 

አያይዞውም “የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች በዕድሜ ዘመናችሁ ሁሉ በሥርዓተ አምልኮ መጽናት፣ በግቢ ቆይታችሁ በምታገኙት መንፈሳዊ ዕውቀት በመደገፍ ሀገራችሁንና ቤተ ክርስቲያናችሁን ማገልገል፣ ማኅበራችሁ ማኅበረ ቅዱሳን አሁን በመስጠት ላይ ያለውን አገልግሎት በማጠናከርና ከማኅበሩ ጎን በመሆን ለቤተ ክርስቲያን ያላችሁን ታማኝነት ትወጡ ዘንድ እናሳስባችኋለን” ብሏል፡፡

የዲላ ዮኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ጉባኤ ሰብሳቢ ተማሪ ገብሬ ወርቁ ስለግቢው ምሥረታ በዓል አከባበር ሲናገር “የዘንድሮን ምሥረታ በዓል ግቢ ጉባኤው ሲያከብር ወጣቶች ቤተ ክርስቲያን የምትጠብቅባቸውን መንፈሳዊ አገልግሎት በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል በማሰብ ነው” ብሏል፡፡

 

የዲላ ዋለሜ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መላከ ሰላም አምሳሉ ሣለ በምሥረታ በዓሉ ላይ በመገኘት አባታዊ ምክራቸውን የለገሱ ሲሆን መላከ ሰላም አምሳሉ በምክራቸው “የዲላ ዮኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ በዚህ ደብር መኖሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ የወንጌል አገልግሎት ላይ ከፍተኛ መንፈሳዊ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ በመሆኑም የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የምሥረታ በዓላችሁን ስታከብሩ መንፈሳዊ አገልግሎታችሁን ወደ ፊትም አጠናክራችሁ ለመቀጠል በማሰብ መሆን አለበት” ሲሉ መክረዋል፡፡

በምስረታ በዓሉ ላይ በተጋባዥ መምህራንና መዘምራን፣ በተመራቂ ተማሪዎች እና በግቢ ጉባኤው ተማሪዎች ስብከቶች፣ መዝሙሮችና ልዮ ልዮ መንፈሳዊ መርሐ ግብራት ቀርበዋል፡፡ እንዲሁም ከሠላሳ በላይ የሚሆኑ የግቢው ተመራቂ ተማሪዎች በምስረታ በዓሉ ላይ በመገኘት ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ልምዳቸውንና ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡

አቶ ፍፁም ኩራባቸው የ2001 ዓ.ም የዲላ ዮኒቨርስቲ ተመረቂ ሲሆን በምሥረታ በዓሉ ላይ በመገኘቱ የፈጠረበትን ስሜት ሲናገር “በምሥረታ በዓሉ ላይ በመገኘት ሳከብር ቀድሞ በግቢ ውስጥ የነበረኝን መንፈሳዊ አገልግሎት በማስታወስ ወደ ፊት በበለጠ ለማገልገል የሚያስችለኝን መንፈሳዊ ስንቅ የምንሰንቅበትና ለግቢ ተማሪዎች ከወንድሞቻችን ጋር በመሆን ተሞክሯችንን የምናስተላልፍበት ልዮ ጊዜ በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ” ሲል ተናግሯል፡፡

በተያያዘም በምሥረታ በዓሉ ላይ የግቢ ጉባኤው የአዳራሽ አሠሪ ኮሚቴ ግቢ ጉባኤው በ600 ካሬ ሜትር ላይ እየሠራ ያለው አዳራሽ እየተፋጠነ እንደሆነ ገልጸል፡፡ የአዳራሽ አሠሪ ኮሚቴው በተወካያቸው በተማሪ ፍርዴ ጥላሁን በኩል ባቀረበው ሪፖርት “ተማሪዎች ቃለ እግዚአብሔር የሚማሩበትን አዳራሽን ለመሥራት እስከ አሁን አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር እንደፈጀና በቀጣይ ሊሠሩ ስላሰቧቸው የበር፣ የመስኮት፣ የኮርኒስ እንዲሁም የማጠቃለያ ሥራ የዕርዳታ ጥሪ” አቅርበዋል፡፡

የዲላ ዮኒቨርስቲ ግቢ ጉባኤ በተማሪዎች ከፍተኛ ትጋትና በአካባቢው ምእመናን ተነሳሽነት የዋለሜ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያንን አንጾ ቅዳሴ ቤቱን በ1994 ዓ.ም እንዲከበር ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡