የደጉዋ እናት ልደት/ለሕፃናት/

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በሊያ አበበ

በኢየሩሳሌም አገር የሚኖሩ ኢያቄምና ሃና የተባሉ በጣም ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ ኢያቄምና ሃና ለእግዚአብሔር የታዘዘ  በተቀደሰ ጋብቻ ውስጥ በብዙ ዘመናት አብረው ቢኖሩም በነዚያ ጊዜያት ወስጥ አንድ ልጅ እንኳ ስላልነበራቸው እጅግ ያዝኑ ነበር፡፡ ወደ ቤተ መቅደስ እየሄዱ እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ አጥብቀው ይለምኑት ነበር፡፡

ከእለታት አንድ ቀን ኢያቄምና ሃና እርግቦች ጫጩቶቻቸውን ሲያጫውቱ ተመልክተው “ለነዚኽ ወፎች እንኳ ልጆችን የሰጠህ አምላክ ለእኛስ መች ይሆን ልጅ የምትሰጠን?” ብለው እጅግ አምርረው አለቀሱ፡፡ ከሐዘናቸውም ጽናት የተነሳ እንቅልፍ ያዛቸውና ተኙ፡፡

 

በተኙ ግዜም ለሁለቱም እግዚአብሔር መልካም ፈቃዱን በህልም ገለጠላቸው፡፡ ኢያቄም በህልሙ ሃና በእቅፍ ውስጥ ከፍሬዎች ሁሉ የምትበልጥ መልካም ጣፋጭ ፍሬ ይዛ ተመለከተ፡፡ ሃና የኢያቄም በትር ለምልማ፣ አብባና አፍርታ ተመለከተች፡፡ ከእንቅልፋቸውም ነቅተው ስለ ህልማቸው ተነጋገሩ፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሆንላቸው በጸሎት ጠየቁ፡፡ እግዚአብሔር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ ቢሰጣቸው አድጎ እኛን ያገልግለን ይታዘዘን ሳይሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ እንዲሆን እንደሚሰጡት ቃል ገቡ፡፡

 

ከዚህ በኋላ ነሐሴ 7 ቀን ሃና ፀነሰች፡፡ ሃና በእርጅናዋ ጊዜ መፅነሷ የተመለከቱ ዘመዶቿና ያገሯ ሰዎች ተገርመው እየመጡ ይጠይቋት ነበር፡፡ ከነዚህም ሰዎች መካከል አንዱ ዐይነ ስውር የነበረችው የአርሳባን ልጅ ናት፡፡ የአርሳባን ልጅ ወደ ሃና መጥታ እውነትም ሃና መጽነሷን ለማረጋገጥ ሆዷን ዳሰሰቻት፡፡ በአድናቆትም ሳታስበው ዐይኗን ስትነካ ዐይኗ በራላት፡፡ በሌላ ግዜም የአጎቷ ልጅ በህመም ምክንያት ይሞትና ሃና ትወደው ስለነበር ልታለቅስ ወደአረፈበት ቤት ትሔዳለች፡፡ እንደደረሰችም አስክሬኑ በተቀመጠበት መካከል አልጋ ዙሪያ ስታለቅስ ሳለ ድንገት ጥላዋ ቢያርፍበት የሞተው ሰው ተነስቶ ሃና የአምላክ እናት የምትሆን እመቤታችንን እንደምልድና በዚህም ሃና እጅግ የከበረችና ምስጋና የሚገባት መሆኗን መሰከረ፡፡

 

ሃና በፀነሰች ግዜ የተደረጉ ብዙ ተአምራትን አይሁድ አይተው ገና በፅንስ ግዜ ይህን ያክል ተአምራት ያደረገ ሲወለድማ ብዙ ነገር ያደርጋል ብለው በምቀኝነት ተነሳስተው ኢያቅምና ሃናን ሊገድሏቸው ተነሱ፡፡ እግዚአብሔር ግን መልአኩን ልኮ ኢያቄምና ሃና ወደ ሊባኖስ ተራራ እንዲሸሹ አደረጋቸው፡፡ በዚያም ሆነው ግንቦት 1 ቀን ከንጋት ኮከብ ይልቅ የምታበራ እጅግ ያማረች የተቀደሰች የምትሆን ልጅን ወለዱ፡፡ ስሟንም ማርያም አሏት፡፡ ልጆች እኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡