የደሴ ማእከል ቅዱሳት መካናትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ስለቤተ ክርስቲያን ዘላቂ ልማት ከበጎ አድራጊዎች ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

 የካቲት 13 ቀን 2006 ዓ.ም.

ወርቁ በላይሁን ከደሴ ማእከል

የደሴ ማእከል ቅዱሳት መካናትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል “ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት በጋራ እንሥራ” በሚል መርህ ከደሴ ከተማ በጎ አድራጊዎች ጋር ቤተ ክርስቲያን በዘላቂነት ራሷን ለማስቻል እንዲረዳ ጥር 25 ቀን 2006 ዓ.ምdasa 2006 የግማሽ ቀን ውይይት አደረገ፡፡

መርሐ ግብሩ በጸሎት ተከፍቶ የበገና መዝሙር ከቀረበ በኋላ ስለቦሩ ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ፤ የመምህር አካለወልድ አዳሪ ት/ቤት እና ስለ አቡነ አኖሬዎስ ገዳም የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማትና የእደ ጥበብ ፕሮጀክት ዶክመንተሪ ፊልም ቀርቧል፡፡ በዶክመንተሪ ፊልሙም ገዳማትንና የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን ለመርዳት በተናጠል የሚደርገው ሩጫ ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ የሚያስገኝ ባለመሆኑ በተጠና መልኩ የተቀናጀ እንቅስቃሴ ማድረጉ የተሻለ እንደሚሆን አስገንዝቧል፡፡

የቀረበውን ዶክመንተሪ ፊልም መነሻ በማድረግ በተደረገው ውይይት በውይይቱ ተጋባዥ የነበሩት ሊቀ ትጉሐን አባ መፍቀሬ ሰብዕ እንደገለጡት “ብንተባበር የቤተ ክርስቲያንን ችግር መፍታት እንችላለን፣ ለዚህም ደግሞ ለኅብረተሰቡ እንደዛሬው ያለ ጥልቅ ትምህርት በመስጠት ግንዛቤውን መለወጥ አስተዋጽኦ የጎላ እንደሆነ” ገልጸዋል፡፡ አክለውም “የቤተ ክርስቲያን ልጆች እኛ እያለን ቤተ ክርስቲያን አትዘጋም፣ ጉባኤው አይታጠፍም ልንል ይገባል” ብለዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ወቅታዊ ሁኔታ የሚያሳይ የፎቶ ኤግዚቢሽን በመርሐ ግብሩ ለዕይታ ቀርቧል፡፡ በዕለቱ በመሪጌታ ይቻለዋል ጎሽሜ ‘ዕለት ዕለት የሚያሳስበኝ የአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ነው’ በሚል ርዕስ ሰፋ ያለና ጥልቅ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ በትምህርቱም “ቤተ ክርስቲያን ጥላ ዘቅዝቃ የምትለምነው እኛ ልጆቿ ግዴታችንን ስለማንወጣ፤ አስራት በኩራት ስለማንከፍል እንደሆነና አባቶቻችን ድር ቢያብር … እንደሚሉት ከተናጠል ይልቅ በኅብረት ሆነን ቤተ ክርስቲያናችንን በዘላቂነት ማልማት እንዳለብን ተገልጿል፡፡

አቶ አለማየሁ የተባሉ የውይይቱ ተሳታፊ እንደገለጹት “በደሴ ከተማ ያሉ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበርና ሁሉንም በመያዝ የተቀረጹ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ለቤተ ክርስቲያን ዘላቂ ልማት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ ይገባል” በማለት ገልጸዋል፡፡በመርሐ ግብሩ ላይ ስለታቀዱት ፕሮጀክቶች መረጃ የሚሰጥ በራሪ ወረቀትና ተሳታፊዎች ፕሮጀክቶቹን ለመደገፍ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ የሚሞሉበት ቅጽ ተዘጋጅቶ የተሰጠ ሲሆን በስራ ቦታና በመኖሪያ አካባቢያቸው ለሚያገኟቸው በጎ አድራጊዎች መልእክቱን እንደሚያስተላልፉና እነሱም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም በመርሐ ግብሩ የተገኙ፣ ተጠርተው ያልተገኙና ሌሎች በጎ አድራጊዎችንም በማካተት በተጠናከረ መልኩ በጋራ ለመንቀሳቀስና የቤተ ክርስቲያንን ልማት ለመደገፍ ይቻል ዘንድ ለየካቲት 23/2006 ዓ.ም ሌላ መርሐ ግብር ተይዞ የዕለቱ ውይይት ተፈጽሟል፡፡