የዩኒቨርሲቲዎች የታሪክ እይታ ከድጥ ወደ ማጡ

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በአራት የዩኒቨርሲቲ መምህራን “የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ፤The History of Ethiopia and the Horn” በሚል እርስ ለመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማስተማሪያ የሚሆን ጥራዝ አዘጋጅቷል። ዝግጅቱ ለመስከረም አልደርስ ብሎ ይሁን ሌላ ምክንያት ኖሮት ባይታወቅም ለሁለተኛው መንፈቀ ዓመት ሊሰጥ መታሰቡ ተሰምቷል። ስርጭት ላይ ሊውል የተቃረበ የሚመስለው ጥራዝ በሙያው ብቃት ባላቸው ምሁራን መዘጋጀቱም ተገልጧል፡፡ የታሪክ ትምህርት እንዳይሰጥ ተከልክሎ የቆየው የገዥው መደብ መጠቀሚያ ሆኖ ስለኖረ እንደ ገና በአዲስ መልክ መጻፍ አለበት ተብሎ   መሆኑን ልብ ማለት ይገባል።

የታሪክ አጻጻፍ መርሕ የማይገዛ መሆኑ

ታሪክ የሚያጠና ሰው ሙያው መረጃን አሟጦ የመጠቀም ግዴታ ይጠበቅበታል። በተለይም ትውልድ የሚያንፅ መጽሐፍ አዘጋጅ ተብሎ የሚታጭ አካል የተጣለበትን ኃላፊነት የሚወጣ መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል። ታሪክን ለማስተማሪያ ብሎ ለማዘጋጀት ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ሙያዊ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን ሥነ ምግባራቸው እና ሚዛናዊ አመለካከታቸው እምነት የሚጣልባቸው መሆን አለበት። ታሪክን ለማጻፍ የሚፈልገው አካልም ዕውቀትንና ችሎታን ወደ ጎን ብሎ በቀረቤታ፣ በወገንተኝነት፣ በቋንቋ መመሳሰል እየመረጠ የሚያጽፍ መሆን የለበትም። እንዲህ አይነት አሠራር የምንከተል ከሆነ ከማንወጣው አዘቅት ውስጥ እንደሚከተን በማሰብ ካለፈው ልንማር ይገባል። አሁንም ታሪክን ለፖለቲካ ትርፍ ለመጠቀም እና እውነት የሆነውን የሚገልጡትን ሳይሆን ለምናራምደው ፖለቲካ ይጠቅመናል ብለው ያሰቡትን ፈጠራ ማጻፍ ይጎዳናል። እዚህ ላይ ብላታ ደሬሳ አመንቴ ተናግረውታል ብሎ የልጅ ልጃቸው ሰለሞን ደሬሳ የጻፈውን መተግበር ታላቅነት መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን።

ብላታ ደሬሳ አመንቴ የልጅ ኢያሱ ወዳጅ ነበሩ። ኢያሱ በራስ ተፈሪ ከሥልጣን ሲፈነገል ግን ከተፈሪ ጋር ተባበሩ። ምሥጢሩን የሚያውቁት ልጃቸው ይልማ ደሬሳ ለምን ወዳጅዎን ኢያሱን ትተው ከማይወዱት ተፈሪ ጋር ተባበሩ ሲሏቸው እሳቸውም እውነት ነው ለእኔ ኢያሱ ወዳጄ ስለሆነ ይጠቅመኝ ነበር። ለአገሬ ግን ተፈሪ ይሻላታል። እኔም የምተባበረው እኔን ብቻ ከሚጠቅመኝ ጋር ሳይሆን አገሬን ከሚጠቅማት ጋር ነው ብለዋል (ደቦ፣ 2010፣–)። ታላቅ የሚያሰኘውም እንደዚህ ዐይነት ተግባር መፈጸም ነው። ይህንን ስልት ፋሽስት ኢጣሊያ ልትጠቀምበት ፈልጋ ነበር። ጀግኖቹ እነ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ግን እኛ የተጣላነው ከተፈሪ እንጂ ከአገራችን ጋር አይደለም ብለው ተፋልመውታል። በዚህም ታሪክ በመልካም ሲዘክራቸው ይኖራል። ታሪካችንን ለመጻፍ የሚመረጡ አካላትም እንዲህ ያለ የመንፈስ ልዕልና ሊኖራቸው ይገባል። አድሎ እየሠሩ ሌላውን የመተቸት ሞራላዊ ልዕልና ሊኖራቸው እንደማይችልም ሊረዱት ይገባል።

የመሰለውን አፈ ታሪክ  ጽፎ የምርምር ሥራ አስመስሎ ማቅረብ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደ ሚያመዝን ጸሐፊውም፣ አጻፊውም ሊረዱት ይገባል። የታሪክ ስሕተት ተፈጥሯል እያሉ የመጀመሪያም ሁለተኛ ደረጃም መረጃ የሚገኝላቸውን ትቶ አፈ ታሪክ ይዞ መቅረብ በምንም ተአምር በምርምር የተረጋገጠ የታሪካችን አካል ሊሆን አይችልም። የተወሰኑ አካላት ተመርጠው ቢጽፉት እንኳ ልዩ ልዩ ምሁራን ሊተቹበት ይገባ ነበር ብለን እናምናለን።

ታሪክን እንዲጽፉ የሚመረጡ ምሁራን የተማሩት ትምህርት ከሚጽፉት ርእሰ ጉዳይ ጋር ያለው ዝምድና መታየት አለበት። በሙያው ቢመረቁ እንኳ ከጣት ጣት ይበልጣል እንደሚባለው ያላቸው ልምድ፣ ተጠያቂነት፣ ተአማኒነት እና ሌሎችም ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ጉዳዮች መታየት አለባቸው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስንጠቀምበት የቆየው ስሕተት አለበት ሲሉ የቆዩት እነሱ ስላልጻፉት ነውም ያሰኛል።

ስንማረው የቆየውን የታሪካችን አካል አድርገን ለመቀበል ይቸግረናል ሲሉ የቆዩ እንደነበሩ ሁሉ ይህንንም የታሪካችን አካል አይደለም የሚሉ እንደሚነሡ ሊታወቅ ይገባል። ጸሐፊዎች ለአገር አሳቢነታቸው፣ ለትውልድ ተቆርቋሪነታቸው፣ የነገውን አገር ተረካቢ ኢትዮጵያዊ በጽኑ መሠረት ላይ ለመትከል ያላቸው ቀናዒነት መታየት ይኖርበታል። ከወገንተኝነት፣ ከአድሎ፣ የመንደር ወሬን የምርምር ውጤት አስመስሎ ከማቅረብ ነፃ መሆን ይገባቸዋል። እንዲህ ካልሆኑ ‹‹ታሪክ ለታመመ አእምሮ ፍቱን መድኃኒት ነው፤ History is a medicine for a sick mind›› (ሥርግው፣ 1972፣ መግቢያ) ብለው የሙያው ሊቃውንት የሚመሩበትን ዲስፕሊን መና ማስቀረት ነው።

ታሪክ ለመጻፍ የሚነሣ አካል ፖለቲከኞች ወይም የግል ጥቅም አሳዳጆች እናተርፍበታለን ብለው ካዘጋጁት የሐሰት ትርክት ነፃ መሆን ይኖርበታል። የተጻፉ እና የቃል አስረጅዎችን፣ አሉባልታ እና ስም ማጥፋቶችን አበጥረው እና አንጠርጥረው ወደ እውነት ለመጠጋት የሚያደረጉት ጥረት አስቀድመው ባበረከቷቸው ሥራዎቻቸው መገምገም ይኖርባቸዋል። የምንደኝነትን መሰናክል ዐልፈው የኖላዊነት እና የእውነተኛ መምህርነትን ተግባር የሚወጡ፣ ተማሪዎቻቸው ምናበ ሰፊ እንዲሆኑ እንጂ እገሌ ተነካብኝ ብለው አገር የሚበጠብጡ ምሁር መሳዮችን ለማውጣት የማይደራደሩ መሆን ይገባቸዋል።

በያዝነው የትምህርት ዘመን መንግሥት እስከ አሁን አገልግሎት ላይ የቆየውን የትምህርት ፍኖተ ካርታ መቀየሩን ገልጧል። ተቋርጦ የነበረውን የታሪክ ትምህርት እንደገና ለማስቀጠል የማስተማሪያ መጽሐፍም አዘጋጅቷል። እስከ አሁኑ ለየት የሚያደርገው አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት እና አሳብ አስተያየት የሰጡበት መሆኑ ነው። በዚህም ይበልጥ ኢትዮጵያውያንን የሚገልጽ አድርጎ ለማዘጋጀት መታሰቡን እንድንገምት አድርጎናል። መጻሕፍቱ ሲዘጋጁ የተነገረው በተግባር መገለጥ አለመገለጡን መጻሕፍቱ ተዘጋጅተው ሲቀርቡ የምናየው ይሆናል።

የጸሐፊዎቹ ማንነት

 ‹‹Module for History of Ethiopia and the Horn For HLIS›› በሚል ርእስ የተዘጋጀውን ማስተማሪያ ጥራዝ ያዘጋጁት አካላት የትምህርት ሁኔታቸው ባይገለጥም ሦስቱ እስከ ሦስተኛ ድግሪ የተማሩ አንደኛው ደግሞ እስከ ማስተርስ የተማረ መሆኑ ተመልክቷል። ስማቸውም ሱራፌል ገልጌሎ (PhD) ከአዲስ አበባ ዩኒበርሲቲ፣ ደሬሳ ዴቡ (PhD) ከጂማ ዩኒቨርሲቲ፣ ደረጀ ሂነው (PhD) ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ እና መሠረት ወርቁ (MA) ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ናቸው። ሰዎቹን እንዴት እንደመረጣቸው የሚያውቀው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቢሆንም እነዚህ ሰዎች እስከ አሁን ሲዘጋጁ በነበሩ የታሪክ መጻሕፍት ላይ ተሳትፎ ስለማድረግ አለማድረጋቸው፣ ስለሚዛናዊ አስተሳሰባቸው የሚታወቅ ነገር የለም።

የምሁራኑን ማንነት  ‹‹በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለዩኒቨርሲቲ እና ኮሌጆች የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ከሚሰጡ ኮመን ኮርሶች (ሁሉን አቀፍ ትምህርቶች) አንዱ ለሆነው የታሪክ ትምህርት የተሰናዳው ማስተማሪያ መጽሐፍ ተከልሶ እና ተበርዞ መዘጋጀቱ ተጠቃሽ ነው። ሰነዱ ከ1990ዎቹ ወዲህ በተመረቁ አራት ወጣት መምህራን መሰናዳቱ ተሰምቷል። ሞጁሉ ከዩኒቨርሲቲዎች ቀድሞ እጁ የገባው (‹‹ሻዶው አዘጋጅ ሊሆንም ይችላል››) ጃዋር መሐመድ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ መለጠፉ ይታወሳል›› (ፍትሕ መጽሔት፣ ቍጥር 58 ታኅሣሥ 2012፣ 6) የሚለው ይገልጠዋል ብለን እናምናለን። ይህ ሐሳብ ብዙ ጉዳዮች እንደታጨቁበት መረዳት የሚገባ ሲሆን ብሉይን በአዲስ ለመተካት ያሰበ አካል አዲስ አቀራረብ እና የተለየ ነገር አቀርባለሁ ብሎ በማሰብ ሊያዘጋጀው እንጂ ሰው ስለተቀየረ ብቻ አዲስ ነገር እንደሚገኝ እያሰቡ ገንዘብን፣ ጊዜን፣ የሰው ኃይልን፣ ማባከን ተገቢ አለመሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን።

ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት አካላት አዘጋጁት ተብሎ የቀረበው ማስተማሪያ ጥራዝ በዋናነት ቅኝት ላይ ያተኮረ፣ ከሀገር በቀል እና ግእዝ ምንጮች ይልቅ ለዐረብ የቃል ትውፊት ዕውቅና የሰጠ፣ ኢትዮጵያ እንደ ማኅበረሰብ ለሦስት ሺህ ዘመን የተጓዘችበትን መንገድ እና ዱካ አጥፍቶ ሌላ ለመገንባት የሞከረ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት ‹‹ሕወሐት በ1968 ዓ.ም ባወጣው የፓርቲው መግለጫ ትግሌ ጸረ ጽዮናዊ እና ጸረ አውሮፓ ኢምፔራሊዝም ነው ይልና ጓዳዊነቱን ወደ ዐረቡ ዓለም ያደላ መሆኑን ያትታል›› (የሺ ሀሳብ፣ 2012፣ 57-58) የተባለው በዚህ ጥራዝ ጎልቶ ወጥቷል። ይህ አስተሳሰብ አሁንም መስመር የያዘ እና ከአድሏዊ አመለካከት የጸዳ ባለመሆኑ በመጽሐፉ ተንጸባርቋል። የማስተማሪያ መጽሐፉ የሚፈልገውን ደግፎ የሚጠላውን ካጣጣለ በኋላ ማጣፊያው ስለሚያጥርበት ትምህርቱ ላይ ሳይሆን ስልቱ ላይ መጠበብ ያበዛል።

ያለፈውን ስሕተት የሚደግም መሆኑ

ታሪካችንን መማራችን የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም። የሚያከራክረው ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች በተግባር መገለጥ አለመገለጣቸውን ስንመረምር የምንደርስበት እውነት ነው። መጽሐፉ ግእዝንም፣ እንግሊዝኛንም ወደ ጎን ትቶ ዐረብኛ ምንጮች ላይ ብቻ ተንጠልጥሏል። ይህ የሚያመለክተው ደርግ የጀመረው ክርስትናን እና ምዕራባውያንን ገሸሽ አድርጎ ዐረቦችን የማቀፍ ስትራቴጂ እስከ አሁንም አለመስተካከሉን ነው። ከተጻፈ መረጃ ይልቅ አፈ ታሪክ ላይ መሠረት አድርጎ ሊያስደስታቸው የፈለጋቸውን አካላት ለማስደሰት ብዙ ታትሯል። ምን አልባትም አስቀድመን እንደጠቀስነው በክርስቲያኖች ላይ ጂሓድ ያወጀው አካል እንዲህ አድርጋችሁ ጻፉ ብሏቸውም ይሆናል። የሚበጀው  ክርስቲያኑም፣ ሙስሊሙም፣ አባ ገዳውም፣ የባሕል እምነት ተከታዩም፣ ይሁዲውም ሆነ ፕሮቴስታንቱ ተችቶበት የተሻለ ሊያግባባ የሚችል ታሪክ ይዞ መቅረብ ነው። የዐረብ ምንጭ ለምን ተጠቀሙ ማለታችን ሳይሆን ለዚያ የተሰጠው ተአማኒነት ለሌሎች ለምን ተነፈገ ማለታችን ነው።

ለሃይማኖቶች የተሰጠ ሽፋን

መጽሐፉ ስለሃይማኖቶች ባቀረበው ሐተታ ውስጥ ባሕላዊ እምነቶችን በ3 ገጽ፣ ይሁዲነትን በ1 ገጽ፣ ኦርቶዶክስ ክርስትናን በ1 ገጽ፣ እስልምናን በ4 ገጽ ጠቅልሎ አቅርቦታል። አድሎው የሚጀምረው ከዚህ ነው። ከ34 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያን ስትሠራ ለኖረች፣ አገር ስትወረር አብራ ለመከራ እየተዳረገች ለመከራውም ለደስታውም ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዕውቅና መንፈግ የጤንነት አይመስለንም። አልፎ አልፎ እንዲያውም ቂሙን ለመወጣት ሲሞክር ወይም ሌሎች የጫኑትን እውነት አስመስሎ ሲያቀርብ ይታያል።

ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚመጣ ሁሉ ማየት የሚፈልገው እና የሚመራመረው የቤተ ክርስቲያን አሻራ ባረፈበት ቅርሳችን መሆኑ እየታወቀ በረከቷን ፈልጎ እሷን መጥላት ምን አይነት ፈሊጥ ነው? ያሰኛል። በማያውቁት ወይም ቀርበው ባልጠየቁት በቤተ ክርስቲያን እና ሃይማኖታዊ ጉዳይ ገብቶ መዘባረቅም ከትችት አያድንም። የቤተ ክርስቲያን ሲሆን የማያውቁትን የገባቸው አስመስለው በማቅረብ እና ሾላ በድፍን አጠቃላይ ገለጣ ሰጥተው ያልፉና ስለእስልምና ሊያስረዱ ሲሞክሩ የሃይማኖት ሰባኪ ሆነው ያልተጻፈ የዐረብ ምንጭ ጠቅሰው እንድናምናቸው ይታትራሉ። ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲጽፉ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ስም ለማጥፋት የተጠቀሙበትን እውነት አስመስለው ያቀርባሉ። ስለእስልምና ሲጥፉ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ታሪክ ጸሐፊዎች ያልደረሱበትን አፈ ታሪክ የዐረብ ምንጮች እንደሚገልጡ አድርገው ታሪክን ለማዛባት የሚችሉትን ያህል ጥረት ያደርጋሉ። እንዲህ አይነቱ ተግባር ትውልድን የሚያንጽ ታሪክ ይጽፋሉ ተብሎ ኃላፊነት ከተጣለባቸው ምሁራን የሚጠበቅ አይደለም።

ለሀገር ውስጥ መረጃ ምንጭ ትኩረት መንፈግ

ዜና መዋዕሎችን ከአፈ ታሪክ ጋር የተቀየጡ ብሎ የሚተቸው እና ገድላትን ከሃይማኖት ዐውድ ወጥተው ነገሥታት ሀገር ለማቅናት የሔዱበትን መንገድ እንደሚያሳዩ ብቻ አድርጎ የሚፈርጀው መጽሐፉ የአንድ የእስልምና እምነት ተከታይ ያልተጻፈ ታሪክ ጠቅሶ በትክክል የእስልምናን አስተምህሮ እንደሚያሳይ አድርጎ ያቀርባል። በአንፃሩ በገድላት ውስጥ የሚገኘውን ጽንዓት፣ሥነ ጽሑፍ፣ ሥነ ማኅበረሰብ፣ ባሕል፣ ፎክሎር፣ የጥንቷን ኢትዮጵያ አስተዳደር፣ ታሪክ፣ ወሰን አከላለል፣ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የነበረውን ታሪካዊ ሁኔታ ለማጥናት እንደሚጠቅሙ ማሳየት አይፈልጉም። ስለእስልምና በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተማራማሪዎች የተጻፉትን መረጃዎች ትቶ በቅርብ የተነሡ የተበድለናል ሮሮ የሚያሰሙ ወገኖች ደጋፊዎቻቸውን በስሜት ለመንዳት ያመቸናል ብለው የፈበረኩትን ልቦለድ እውነት አስመስሎ ያቅርባል። ይህም ጥላ ሆኖ መጽሐፉን ያጻፈ አካል አለ ተብሎ የተጠቆመው ወደ እውነት እንዲጠጋ ያደርጋል። ይህን ከመጽሐፉ በመጥቀስ እናብራራው።

መጽሐፉ በገጽ 15 እንዲህ ይላል “The value of Manuscript is essentially religious”፤ ‹‹የብራና መጻሕፍት ይዘት በዋናነት ሃይማኖታዊ ነው›› የሚለው ጥቅል ፍረጃ የተሳሳተ ነው። ይህ ጥቅል ድምዳሜ ልምድ የሌላቸው አጥኝዎች የብራና መጻሕፍት ሃይማኖታዊ ናቸው በማለት እንዳይመራመሩባቸው መንገድም፣ ፍላጎትም ይዘጋል። ከብራና መጻሕፍት መካከል ዋና ትኩረታቸው ሃይማኖታዊ የሆኑም ያልሆኑም መኖራቸው በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገር አጥኝዎች የተረጋገጠ ሆኖ ሳለ እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረስ ተገቢ አይደለም። ለምሳሌ ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ፣ መጽሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን፣ መጽሐፈ መድኃኒት፣ አንጋረ ሰላስፋ፣ ፊሳሎጎስ፣ መጽሐፈ በርለዓም ወየወሴፍ ፣ የዓለም ታሪክ፣  ዐውደ ነገሥት፣ ልዩ ልዩ ዜና መዋዕሎች፣ ክብረ ነገሥት፣ ታሪከ ነገሥት እያሉ መጥቀስ ይቻላል። የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ እና የእስራኤል የሥነ ገድል አጥኝዎች በብራና መጻሕፍታችን ሲመራመሩ የሚኖሩት ከሃይማኖታዊ ዐውድ የዘለለ ጠቀሜታ ስላላቸው መሆኑን ለጥራዙ አዘጋጆች ማስገንዘብ እንወዳለን። የውጭ አገር ተጓዦች የጻፏቸውን ማስታወሻዎች መጥቀሱ መልካም መሆኑን ብንጠቅስም ተማሪዎቹ ምርቱን ከገለባ ለመለየት እንዲችሉ አልፎ አልፎም ቢሆን ሒሳዊ ዳሰሳ ቢቀርብባቸው መልካም መሆኑን ለማስገንገብ እንፈልጋለን።

የተዘጋጀው ጥራዝ ስለክርስትና እንዲህ ይላል፡- Evidences show that Aksumite king Ezana (r.320-360) dropped pre christian gods like Ares (Hariman), Maharram(War gods), Arewe (serpant python gods), Bahir(Sea gods) and Mider (earth gods) and embranced Christianity. Instrumental in conversion were Syrian brothers, Aedesius and Fremnatos (page 38). አንድ ሀገር ምንም በክርስቶስ ያምናል ተብሎ ቢነገር ሙሉ በሙሉ ክርስቲያን ሆኖ ሕግጋቱን ጠንቅቆ ይፈጽማል ተብሎ አይታሰብም። አልፎ አልፎ ባዕድ አምልኮ እና በጣዖታት ማምለክ  ሊኖር ይችላል። እንኳን በዚያን ዘመን ዛሬም ቢሆን ጣዖት ማምለክ አልጠፋም። ኢትዮጵያ በመንግሥት ደረጃ የጦርነት አምላክ፣ የባሕር አምላክ፣ የመሬት አምላክ እያለች ጣዖት አቆማ ታመልክ ነበር የተባለው ሊታመን የሚችል አይደለም። በግእዝ የተጻፈውን ቃል እንደ ባዕድ አምልኮ መቍጠር አለማወቅን ወይም ሌሎች ያሉትን ማስተጋባትን ያሳያል። አርዌ ማለት በግእዝ እባብ ማለት ነው። ባሕር ማለትም የውኃማ አካላት መጠሪያ ነው። ምድር ማለትም የደረቅ መሬት (የየብስ) መጠሪያ ነው። በድንጋይ ላይ ጽሑፎች እነዚህ ቃላት መገኘታቸው ኢትዮጵያ ባዕድ አምላክ ታመልክ ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ ለመናገር ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም። የእነዚህ ፍጥረታት ሥዕል በሐውልቶች ላይ መገኘቱ በምን ምክንያት ከባዕድ አምልኮ ጋር እንደሚገናኝ የሚያውቁት በራሳቸው ሥነ ልቡና የእኛን ሀገር ታሪክ ለማጥናት የሞከሩ ነጮች እና አሁንም የእነሱን ሐሳብ ለመሞገት ሳይሆን እንዳለ ተቀብለው ለማስተጋባት የሚታትሩት የእኛው ወገኞች ናቸው። ለዚህም ቢሆን አሳማኝ መረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።

በሬ ወለደ ትርክት

ኢትዮጵያ በክርስትና ማመን የጀመረችው በ34 ዓ.ም በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በባኮስ ወይም በአቤላክ አማካኝነት ነው። የቍስጥንጥንያው ፓትርያርክ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ኢትዮጵያውያን በዕለተ ጰንጤ ቆስጤ በኢየሩሳሌም እንደተገኙ፣ ለሐዋርያት በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ያስተምሩ ዘንድ 71 ቋንቋዎች በተገለጠላቸው ጊዜ የበረከቱ ተሳታፊዎች እንደነበሩ ጽፏል። ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ያላካተተበትንም ምክንያት በቍጥር ጥቂት ስለነበሩ መሆኑን አስረግጦ ተናግሯል። እሱ ብቻ ሳይሆን የላቲን ቤተ ክርስቲያን አባት የሚባለው አባ ጀሮም፣ ታሪክ ጸሐፊው ሩፊኖስ እና ሌሎችም ስለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሐዋርያዊ አገልግሎት ጽፈዋል። ጃንደረባው ለወገኖቹ ሐዋርያ ሆነ በማለት የመጀመሪያው የአፍሪካ ሐዋርያ መሆኑንም ተናግረዋል። ታሪክ ጸሐፊዎቻችን ማመን የማይፈልጉት ወይም እንደ አፈ ታሪክ የሚቈጥሩት ይህንን እውነት ነው። ይህን እውነት አልቀበልም ያለ ሰው የሌለ አፈ ታሪክ እየጠቀሰ እውነት ለማስመሰል ሞክሯል። ከተመራማሪ የሚጠበቀው ያልተሔደበትን መንገድ በምርምር  ታማኝ ከሆነ መረጃ ላይ ደርሶ አዲስ እውነትን ማሳየት ነው።

ለምሳሌ ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ስለዮዲት ጉዲት ጥንት ሲነገር ከነበረው የተለየ መረጃ ሲያገኙ ሁለቱንም አቅርበው ውሳኔውን ለአንባቢ ይሰጣሉ። የዚህ መጽሐፍ አዘጋጆች ግን ንጉሣችን አርማህን በቅርብ የተነሡ እና መረጃ የሌላቸው ወገኞች የሚያስተጋቡትን የሐሰት ትርክት እውነት አስመስለው ንጉሡን አስልመው ሲያቀርቡ ቤተክርስቲያን ምን እንደምትል ጠይቀው ማረጋገጥ አልፈለጉም። አንዳንድ የዐረብ ምንጮች ብለው ቢነግሩንም እስከ አሁን ያልተደረሰበት በዐረቦች እጅ የሚገኝ መረጃ እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል። ኖሮ እኛ ብንደብቀው እንኳ ምዕራባውያን ከዐረቦች እኛ በልጠንባቸው እውነቱን ሸፍነውት እንደማይቀሩ ሊታወቅ ይገባል። ይህ ጉዳይ እውነት ቢሆን ኖሮ አሁን ተምረናል ብለው ከሚያስቸግሩ ወገኖች በተሻለ መልኩ ሊታመን እንዲችል አድርጎ የዘመኑን መንፈስ የጻፈው ዐረብ ፋቂህ ይመዘግበው ነበር። በእስልምና ላይ የተማራመሩት እነ ፕሮፌሰር ጆን ስፕንሰር ትሪሚንግ ሐም እና ሌሎችም መረጃ አግኝተው አያልፉትም ነበር። ይህን አምኖ ለመቀበል የቸገራቸው ታሪክ ጸሐፊዎች ያልተጻፈ ታሪክ ንጉሥ አርማህ ሰልሟል ብለው ሲጽፉ መረጃ ለመያዝ እንኳ አልፈለጉም።

እውነቱ  ከቤተ መንግሥት ወገን የነበረው ኢትዮጵያዊው ባኮስ ክርስትናን ተቀብሎ ወደ አገሩ ተመልሶ ሲያስተምር መኖሩ ቢታወቅም በኋላ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንበረ ጵጵስናን ማምጣቱ ነው፡፡ የመንበረ ጵጵስና መገኘት ደግሞ በቀላሉ ካህናት እና ዲያቆናት እየሾሙ፣ በየቦታው አብያተ ክርስቲያን እንዲተከሉ ስለሚያደርግ ይህ የሆነው እ.ኤ.አ.330 ነው። የውጭ ሀገር ታሪክ ጸሐፊዎች የሚስቱት ወይም ሆን ብለው በዓላማ አድበስብሰው የሚያልፉት ይህን እውነት ነው። ኢትዮጵያ የግብፅ አንድ ሀገረ ስብከት  ሆና ጳጳስ ሲሞትብን ግብፅ እየሔድን ስናመጣ መቆየታችን ዓለም ያውቀው ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው። ኢትዮጵያውያን አስቀድሞ የጸና እምነት እንደ ነበራቸው የሚያስገነዝበው ነገሮችን ሁሉ በእምነት ዓይን ብቻ የተመለከተው የቅዱስ አትናቴዎስ ንግግር ነው። ካለ ሰባኪ በማመናችን ተደንቆ ለጵጵስና የምትገባው  ቋንቋቸውን የምታውቀው አንተ ነህ ብሎ ጳጳስ አድርጎ ላከልን። ዛሬ ቢሆን ኖሮ ከሶርያ መጥተህ እንለው ነበር። ከሰሜን መጥተህ፣ ደቡብ መጥተህ፣ እዚህ ማገልገል ካለብሔርህ አባታዊ መልእክት ማስተላለፍ አትችልም እንለው ነበር። እውነት የሆነው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ባኮስ አስቀድሞ በቤተ መንግሥት ሲያስተምር የኖረውን እና ተተክሎ እንዲቆይ ያደረገውን የክርስትና ትውፊት አባ ሰላማ በክህነት ማጽናቱ ነው።

ምንም እንኳ ክርስትና አስቀድሞ በባኮስ ቢሰበክ አባ ሰላማ ሙሉ አደረገው። የጎደለውን ሞላው፣ ሊላላ የነበረውን አጠበቀው። ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን አባ ሰላማ የበኩሉን አስተዋጽዖ አደረገ። ምዕራባውያን የሚሸሹት ይህንን እውነት ነው። ይህንን እውነት የማይቀበሉትም ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ቀድማ ክርስትናን ተቀበለች ብለው ማመንም፣ መስማትም ስለማይፈልጉ ነው። ታሪካችንን ወስደው እና የመካነ ሥላሴ መነኩሴ ከሆነው ከአባ ጎርጎርዮስ ታሪካችንን ተምሮ ስለኢትዮጵያ የጻፈውን ኢዮብ ሉዶልፍ የአፍሪካ የታሪክ አባት ሲሉት ስለመምህሩ አባ ጎርጎርዮስ ማንሣት አይፈልጉም። መታወቅ ያለበት ክርስትናም፣ እስልምናም በኢትዮጵያ ላይ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፋቸው ነው። ፖለቲካ በተቀያየረ ቍጥር መንግሥትን እየተጠጉ የክርስትናን አሻራ ለማጥፋት መሞከር ዕልቂትን እንጂ ሰላምን አያመጣም። የሚገባው የሁሉንም ወገኖች ታሪክ ሚዛናዊ አድርጎ ማቅረብ እና ሁለቱም ታሪካችን የኢትዮጵያዊነት መታወቂያችን መሆኑን አምነን መንከባከብ ነው። የእኛን እያፈረሱ የእነሱን እንድንቀበል መሞከር ግን ታሪክን በታሪክ ሊቃውንት ስም ሸፍኖ ከመካነ አእምሮዎቻችን ውስጥ ማስገባት በመሆኑ ሊያስማማን አይችልም። እውነት ከሆነም በግልጽ ይቅረብና ተካራክረን እውነት አርነት ያወጣው የታሪካችን አካል ሆኖ ይቀጥል።

ነጮች በዓላማ ያበላሹትን የታሪክ ጥናት እንደ እውነት በመያዝ የጥፋት ዓላማ አስፈጻሚ ከመሆን ይልቅ በሚገባ ተመራምሮ እውነት ከሆነው ዘንድ መድረስ ይገባል። የተለመደው የተሻለ ነገር ሳይዙ ከባለ ጊዜ እየተጠጉ ታሪክን መሸርሸር ነው። ይህ መቆም ይኖርበታል። እንዳይቆም ብንፈልግም ዘመኑ በየስርቻው የተደበቀውን እውነት እየመዘዙ ሐሰተኛን የሚረቱበት በመሆኑ  ታሪክ ጸሐፊዎቻችን ወደ ተሻለ እውነት የሚያደርሰንን መረጃ አቅርቡልን እንጂ ተጨማሪ ብጥብጥ አትፍጠሩ። የነጭ እና የዐረብ የጥፋት ዓላማ አስፈጻሚዎች አትሁኑ። የጣሊያን እና የዐረብ ዓላማ አስፈጻሚዎች ክርስትናን የተቀበልንበትን ዘመን ለሦስት መቶ ዓመታት ወደ ኋላ ይገፉታል። ይህንን የሚያደርጉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አሻራ ለማደብዘዝ ነው። ለእነርሱ የሚቀለውም ወገኖቻችንን በማስተማር ስም ዓላማቸውን ጭነው በመላክ ጠበቃ እንዲሆኗቸው ማድረግ ነው።

ይቆየን