የዩኒቨርሲቲዎች የታሪክ እይታ ከድጥ ወደ ማጡ

…….ካለፈው የቀጠለ

ዶግማን ማዛባት

በመጽሐፉ ገጽ 39 In 16th and 17th centuries, Jesuits tried to convert Monophysite EOC to Dyophysite catholicየሚለው መረቅ እና ፍትፍት የተቀላቀለበት ነው። ካቶሊኮች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮችን ካቶሊካዊ ለማድረግ፣ ክህነትንም ከግብፅ ከሚመጣ ጳጳስ ከሚሰጥ ይልቅ ከሮም በሚላክ ጳጳስ እንደገና  እንድንቀበል ሞክረው ነበር። በዚህም ምክንያት ብዙ ደም መፍሰሱ እውነት ነው። ትክክል ያልሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን እምነት ጠላቶቿ ስም ለማጥፋት የሚጠቀሙበትን ቤተ ክርስቲያናችን እንደምታምንበት አድርጎ Monophysiteብሎ መጥራቱ ነው። ይህ ቃል የግሪክ ሲሆን ትርጉሙም መለኮት ሥጋን ዋጠው፣ መጠጠው እና ባሕርይውን በማጥፋት አንድ ባሕርይ ሆነ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ያፈነገጠ ነው። የሚቀጠለውም ለአውጣኬ ኑፋቄ ነው። የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮ በትክክል የሚገልጠው Miaphysiteየሚለው የግሪክ ቃል ነው። ትርጉሙም ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ፣ ከሁለት አካል አንድ አካል በተዋሕዶ ከበረ ማለት ነው። ተዋሕዶውም በመጠፋፋት ሳይሆን በተዓቅቦ ሥጋም ባሕርይውን  ሳይተው፣ መለኮትም ባሕርይውን ሳይለቅ የተፈጸመ መሆኑን አምኖ መመስከር ነው። ዋጠው መጠጠው በጉባኤ ኬልቄዶን የተሰበሰቡ መለካውያን አውጣኬን የከሰሱበት ኑፋቄ ነው። መለካውያን የኦርቶዶክስን አስተምህሮ ወደ አውጣኬ ለማስጠጋት የሚጠቀሙበት ስም ቤተ ክርስቲያንን አይወክልም። ቅዱሱ አባት ዲዮስቆሮስ ምንታዌን አልቀበልም ስላላቸው ድሮም አለቃቸው ሊዮን በሚገባ ሳይረዳው የኖረውን ቃል በክህደት ስላጸናው እምነታችንን Monophysiteብለው መጥራት ጀመሩ። ስሕተት የሚሆነውም ሰዎች ያላሉትን የሚያምኑበት አስመስሎ እንዲህ ነው የሚያምኑ ብሎ መናገር እና ሌሎችንም ለማሳመን መሞከር ነው። ስለዚህ ካቶሊካውያን ሊቀይሩ የመጡት ሃይማኖታችን Monophysite ሆኖ ወደ Dyphysite ሳይሆን  Miaphysite ብለን የምናምነውን Dyphysite ብላችሁ እመኑ ብለው ነበር። ስላልተሳካላቸውም የብዙ ኢትዮጵያውያን ደም ፈሰሰ።

የቤተ ክርስቲያንን ውለታ ጥላሸት መቀባት

  “EOC Spread to centeral, south, east and west parts following their conquest by the northern Christian kingdom. People were baptized as a government obligatory decree. Lately monopolization of burial places by church forced people to accept Tewahdo (page 39). ይህንን አንቀጽ የጻፈው ደጋፊ ለማግኘት የሚሻ ፖለቲከኛ ቢሆን ባልገረመንም ነበር። የጻፉት ግን በታሪክ ምሁራን ስም የተሰበሰቡ እና መንግሥት ትውልድ ይቀርፃሉ ብሎ ኃላፊነት የጣለባቸው ምሁራን ናቸው። እነዚህ ምሁራን ሲባል የሰሙትን በምርምር ማረጋገጥ ሲገባቸው ለኢትዮጵያ አንድነት የማዕዘን ድንጋይ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን መምታት ዓላማችንን ያሳካልናል ብለው ያሰቡ ወገኖች ላለፉት አምሳ ዓመታት በሐሰት የፈበረኩትን ፕሮፓጋንዳ እውነት አስመስለው የታሪክ ሰነድ አድርገው አቀረቡልን። ሰነዱ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ እንደ ፈጠራ ሥራ አንድ ቦታ ቁጭ ብለው የጻፉት እንጂ በምርምር ያረጋገጡት አለመሆኑን ከሚያስገነዝበው ጉዳይ አንዱ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥትን እጅ ጠምዝዛ የፈለገችውን ስታስፈጽመው የኖረች አስመስሎ ማቅረቡ ነው። በሌላ አነጋገር መንግሥት  አገር መምራቱን ትቶ ቤተ ክርስቲያንን ከጎኑ አድርጎ ወንጌል ሲሰብክ የኖረ ያስመስላል። ይህ ሳብ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት እና እንዳትናገር ለማሸማቀቅ ያስችለናል ብለው የፈጠሩት ነው። በዘውዳዊው አገዛዝ የተማረረውና መፍትሔውም እግዚአብሔርን መካድ የመሰለው ማርክሲዝምን ርዕዮተ ዓለም አድርጎ የተነሣው የሶሻሊስት አቀንቃኝና የብሔር ፖለቲካን ቀይጦ የያዘው ወጣት በአንድነት ተስማምቶ የገዛህ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንም ጭምር ናት ብንለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሰማናል ብለው ከመምህራቸው ከሌሊን የተማሩትን ሊያስተምሩን ነው። ማንም ምሁር በእውነት ላይ ተመሥርቶ ይህንን ትርክትና ርዕዮት ሊቃወም ከተነሣም በሳይንሳዊ መንገድ እና በምርምር ሳይሆን የድሮ ሥርዓት ናፋቂ በማለት እናሸማቅቀዋለን ብለው የፈጠሩት መሆኑን መረዳት ይገባል። ይህን ሐሳብ ላለፉት አምሳ ዓመታት ሲያስተጋቡት እንደኖሩ አሁንም ምሁር በሚሏቸው ሆድ አደሮች ይህንኑ ሐሳብ በከፈቷቸው ብዙኃን መገናኛዎች ሲያደነቁሩን ውለው እንደሚያድሩ ይታወቃል።

በፖለቲካ ፍልስፍና ግራ የተጋቡና የራሳቸው ሀገር በቀል መፍትሔ ማመንጨት የተሳናቸው የሐሳብ  መካን የሆኑ ምሁራን ትውልድ የሚጠቅም አጀንዳ ስለሌላቸው የሞኝ ልቅሶ መልሶ መልሶ እንዲሉ ይህንን ያህል ዘመን ተናግረው አልሰለቻቸውም። የሚያመዛዝን አእምሮ ያለው ሰው አልቀበላቸው ስላለ ዩኒቨርሲቲዎቻችንን ጥላ አድርገው ቀረቡ። ለሀገር ሰላምና ለሕዝብ አንድነት የማይጠቅምና ግጭትን በትምህርት ስም በዘለቄታዊነት ለመትከል የሚሠሩ የሀገርና የእውነት ጠላት ብቻ ሳይሆን የቤተክርስቲያን ፀር የሆነ አቋም ይዞ የወጣቱን ትውልድ   አእምሮ በሐሰት ለማጠብ መመኮር፣ ክርስቲያኖችን ብቻ ሳይሆን ለእውነት የመቆሙትን ሁሉ የሚያስቆጣ ተግባር ነው፡፡

ሀገር የሚያንጽ ተግባር ከመፈጸም ይልቅ ቡድናዊነት የሚበልጥባቸው፣ ትውልድ ሲበጠበጥ የትርፍ እንጀራችንን እንጋግራለን ብለው ያሰቡ ወገኖች የፖለቲካ መርሐ ግብር አድርገውት የኖረውን ሰነድ ለታሪክ ማስተማሪያ አድርገው አቀረቡልን። ከ1966 ዓ.ም በኋላ ሥልጣን ላይ የወጡ  አካላት አፍቃሬ ዐረብ በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያንን በመጥላት ያልተጻፈ ስምምነት ነበራቸው። ‹‹የኅብረተሰባዊነት አብዮት ከኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ይልቅ ለእስልምና የተሻለ ዕድል ነበረው።…በኢትዮጵያም በ1968 ዓ.ም የሞስሊሞች ምክር ቤት (ሙጅሊስ) ተቋቁሟል›› (የሺህ ሀሳብ፣ 2012፣ 144-145) የሚለው ከትናንት እስከ ዛሬ ባለመስተካከሉ ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ከኦርቶዶክሳውያን ሁሉ ይጠበቃል። ቤተ ክርስቲያን ያበረከተችውን እየተጠቀሙ ቤተ ክርስቲያንን ሲያሳድዱ መኖራቸው የሚያስቅም፣የሚገርምም ነው። የፊውዳሉ ሥርዓት ጠበቃ አድርገው  በጭፍን ስለሚጠሏት በተባራሪ የሰሙትን ሁሉ እውነት አስመስለው ያቀርባሉ።

በመጀመሪያ ደረጃ ቤተ ክርስቲያን መንግሥትን እየተከተለች፣ በጦር እያስፈራራች ሃይማኖቷን እንዳስፋፋች አድርጎ ማቅረብ የተዛባ አስተሳሰብ የወለደው መሆኑን መናገር እንፈልጋለን። ይህ ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኗን ታሪክ በማዛባት የቀረበው ሐሳብ እንዲስተካከል እንጠይቃለን።

እውነቱ ግን በተቃራኒው ነው። ቤተ ክርስቲያን ያለሰለሰችው የአረማውያን እና የአሕዛብ ልቡና ወደ ማእከላዊ መንግሥት ለመታቀፍ እንዳላስቸገረ እና መንግሥት የራሱን ሥራ ለመሥራት እንዳገዘው መረዳት ይገባል። ያለፈው ሥርዓት ፈጽሞታል ለሚሉት ጥፋት ቤተ ክርስቲያንን ተጠያቂ ማድረግ አንደበቷን ዘግታ እንድትቀመጥ ለማድረግ የተሸረበ ሴራ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ገለጻው እውነታን ያላገናዘበ መሆኑን መረዳት እና ተገቢውን መልስ መስጠት አስፈላጊ ሲሆን በሕግ መጠየቅ ይገባል። የኢትዮጵያ ሠራዊት ምን ያህል የተደራጀ ሆኖ ሀገር እንደ ወረረ የሚያውቁት ጸሐፊዎቹ ናቸው። ራሱን ቅኝ ተገዥ አድርጎ የሚያይ ምሁር ግራ ቀኝ አመዛዝኖ ታሪክን ይጽፋል ተብሎ አይታሰብም።

ንጉሡን አጅቦ የሚሔድ ሠራዊት መኖሩ ባይካድም አገር ስትወረር ኢትዮጵያዊው ገበሬ ቤት ንብረቱን ትቶ እየዘመተ ሀገር ሲጠብቅ የኖረ እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ቀኝ እጅ ሆኖ ያላመኑት በግዳጅ እንዲጠመቁ  ሲያደርግ አልኖረም። ወታደር ሆኖ ሀገር የጠበቀው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ የሆነው ብቻ ስለሚያስመስል ሌሎች እየኖሩ ያሉት ኦርቶዶክሳውያን በጠበቋት ሀገር ነው እንዲባል ራሳቸውን እንዳጋለጡ  ጸሐፊዎች አልተረሰዱትም። እንዲህ አይነት መረጃ ካለም አምጥቶ መከራከር ነው። ሀገር ሲጠብቅ የኖረው ወታደር እንኳን ለሌላ የሚተርፈው ለራሱ የሚሆነው የሃይማኖት ትምህርት አልነበረውም።

በደቡብም ሆነ በምሥራቅ እና በምዕራብ ኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት የተተከሉት ከቤተ ክህነት በተሰጠ ተልእኮ ሳይሆን በሊቃውንቱ እና በካህናቱ ግለሰባዊ ጥንካሬ አማካኝነት ነው። ካህናት፣ መነኮሳት እና ሊቃውንት ከሰሜን ወደ ደቡብ ተዘዋውረው ያረፉበትን አካባቢ ነዋሪ አስተምረው አንዳንዶችም ቤት ንብረት አፍርተው መኖራቸው አይካድም። ይህ ደግሞ ሀገራችን ብለው የፈጸሙት፣ ከእግዚአብሔር እናገኘዋለን ብለው ያከናወኑት እንጂ ለመንግሥት ቀኝ እጅ ለመሆን አይደለም።

የቤተክርስቲያን መዋቅር ከነገሥታት ጋር እጅ እና ጓንት ሆኖ መንግሥት ወግቶ ድል ሲያደርግ  ቤተክርስቲያን አስገድዳ ታጠምቅ ነበር የሚለው ፈጠራ እንጂ በመረጃ የሚረጋገጥ እውነት አይደለም። ይህ በማን ዘመነ መንግሥት እና መቼ፣ በየትኛው የኢትዮጵያ ክፍል እንደተፈጸመ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል። ቤተክርስቲያን በማስገደድ ርስት ነቅላ፣ ሃይማኖት አስቀይራ አታውቅም። ‹‹የእምየን  ወደ  አብየ››  ከሆነ አንገት በመቅላት እስከ ዘመናችን የደረሰው፣ አሁንም በጥንቱ እኩይ ድርጊቱ  የቀጠለው ማን እንደሆነ ይታወቃል። ታሪክ ጸሐፊ ተብለው የተሰየሙት  አካላት ይህንን እውነት እንዳይናገሩ ወይ ፈርተዋል አልያም በገንዘብ አፋቸውን ተለጉመዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያንን የመንግሥት ቀኝ እጅ አድርጎ ማቅረብ

ከጥንት እስከ ዛሬ ቤተክርስቲያን  የተስፋፋችው  በገዳማውያን እንጂ በመንግሥት ደጋፊነት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ መንግሥት ሲሳሳት በመገሠጻቸው ለመከራ የተዳረጉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መነኮሳት እንጂ የሌላ እምነት ተከታዮች አይደሉም። በመነኮሳቱ ድርጊት የተበሳጩት ዓፄ ዐምደ ጽዮንም፣ ልጁ ሰይፈ አርዕድ፣ ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ አቡነ ተክለ ሐዋርያትን ያሰቃዩዋቸው እና ከገዳማቸው አስወጥተው ያሳደዷቸው ክርስቲያኖችን እንጂ ሌሎችን አይደለም። ይህ ደግሞ የመንግሥት ቀኝ እጅ መሆናቸውን ሳይሆን እንዲያውም ባጎረስኩኝ እጄን ተነከስኩኝ ይፈጸምባቸው እንደነበር ነው። ቤተ ክርስቲያን ለመንግሥት ቀኝ እጅ ከሆነች መንግሥታት ለምን መነኮሳቱን ሲያሰቃዩ ኖሩ ብሎ መጠየቅ ከስሕተት ያድናል (ገድለ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ፤ ገድለ አኖሬዎስ፤ ገድለ አሮን መንክራዊ፤ ገድለ አቡነ ተክለ ሐዋርያት፣ ተክለ ጻድቅ፣ 1966፣ 49-53) መመልከት ይቻላል።

አቡነ ኢየሱስ ሞዓ መጻሕፍትን ሲጽፉ ከኖሩበት ደብረዳሞ ገዳም ወደ ሐይቅ ሲመጡ በጣም ብዙ የብራና መጻሕፍትን ይዘው መጥተው የትምህርትም የምንኩስናም ማእከላቸውን  ሐይቅ  ላይ አድርገው ያስተማሯቸው ደቀ መዝሙሮቻቸው አቡነ ኂሩተ አምላክ ወደ ምዕራብ በመሔድ እስከ ቋራ አስተምረው ጣና ገዳማት ላይ ዐረፉ፤ አቡነ እንድርያስ ከኤርትራ ጀምረው እያስተማሩ እስከ ደቡብ  ጎንደር መጡ፤ አቡነ ዜና ማርቆስ  ዐባይን ተሻግረው ጎጃም አቸፈር ጣዖት አምላኪ የነበረውን  ገዢ አሳምነው ከዚያ ቤተሰብ  አባ ዓምደ ሥላሴን  አፍርተው ማኅበረ ሥላሴ ገዳም እንዲመሠርቱ አድርገው እስከ ሱዳን አስተማሩ። አባ በኪሞስ  ወይም ተከሥተ ብርሃን ዲማን እና አካባቢውን እስከ ይልማና ዴንሳ፣ ዑራ ኢየሱስ እና ናዳ ማርያም  ድረስ  አገውን ጭምር አስተማሩ። አባ ተጠመቀ መድኅን ከምዕራብ ሸዋ ተነሥተው ሙሉ መተከልን፣  አቡነ ዜና ማርቆስ  በምድረ ጉራጌ እስከ ምሁር ኢየሱስ፣ አቡነ አኖሬዎስ እስከ ባሌ፣ አቡነ ሳሙኤል እስከ ደብረ ወገግ እና የአሁኗ ጂቡቲ ሲያስተምሩ የትኛው ወታደር  አጅቧቸው እንዳጠቁ እና አስገድደው  የነባሩን ነዋሪ ርስት እንደወረሱ የሚያውቁት የሐሰት ትርክት ጽፈው እውነት የሚያስመስሉ የዚህ የታሪክ ጥራዝ ጸሓፊዎች ናቸው፡፡

በተደጋጋሚ  እስከ ወግዳ እየተስፋፋ እና እስከ ጀማ ወንዝ ድረስ እየሔደ የሸዋ ገዥዎችን እና ማእከላዊውን መንግሥት  ያስቸግር  የነበረውን  ሞቶሎሚን  ከድርጊቱ  እንዲታቀብ እና በጦርነት  ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለ እንዲረዳ ያደረጉት አቡነ ተክለሃይማኖት  አጥምቀው  ፍሰሐ ጽየን ካሉት በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በመቀጠልም አቡነ ተክለ ሃይማኖት  እስከ  ነጭ ዐባይ ድረስ ዞረው ሲስተምሩ  ወታደር ይቅርና ረድዕ እንኳ አብሯቸው አልነበረም።  እነዚህን እና ሌሎችንም አባቶች የየትኛው ንጉሥ ሠራዊት  እንዳጀባቸው፣  ማን በሚባለው ጳጳሳችን  የቤተ ክህነትን  ተልእኮ  እንደሰጣቸው አልነገሩንም። አሁን ታሪክ ተብሎ የቀረበልንን ዓፄ ምኒልክን ለማጣጣል እና ኢትዮጵውያንን  በማሸማቀቅ  የፈለግነውን  ለማድረግ  ይጠቅመናል ብለው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ሲቀሰቅሱበት የነበረ የፖለቲካ መርሐ ግብራቸው ነው። ይህን  አፈ ታሪክ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቀበለናል ብለው ማቅረባቸው ያስገርማል። እውነት ቢሆን እንኳ በመረጃ አስደግፈው ማቅረብ ነበረባቸው።

ለጥንቱ ሠራዊት ያለ ስሙ ስም መስጠት

በታሪክ ሰነድ እኛ ብቻ ሳንሆን የውጭ አገር ተጓዦች ጭምር ጽፈውት የምናነበው የዓፄ ምኒሊክ  ሠራዊት በራስ ወልደ ጊዮርጊስ እየተመራ እስከ ሩዶልፍ ሐይቅ ድረስ  እንደዘመተ ተዘግቧል። ከሠራዊቱ ጋር አብሮ የዘመተው ሩሲያዊ በዓይኑ ያየውን፣ በጆሮው የሰማውን በሦስት  መጻሕፍት አስነብቦናል።  ከዓፄ ምኒልክ ሠራዊት ጋርከእንጦጦ እስከ ባሮ እና በቅርብ ወደ አማርኛ በተተረጎመው የዓፄ ምኒልክ ሠራዊት ታሪክ የተረከበት መጻሕፍት የሠራዊቱን  ድካም ቢነግሩንም ማንንም አረማዊም ሆነ የሌላ እምነት ተከታይ አስገድደው ክርስቲያን እንዲሆኑ ማድረጋቸውን አልመዘገቡም። በመዋቅር ደረጃ ተልእኮ የተሰጠው  አንድም ቄስ አብሮ መጓዙን መጻሕፍቱ አይነግሩንም፡፡ የኢትዮጵያ  ሠራዊት በምርኮ ድል ያደረገውን ሕዝብ በግዳጅ ለማጥመቅ የቤተክርስቲያን ቀኝ እጅ ሆነ ተብሎ መልካም ባደረገ እና ሀገር ጠብቆ ባቆየ መተቸት አልነበረበትም። ወታደር በሔደበት  እንደሚወር፣ ተገዳዳሪውን እንደሚያውክ ቢታወቅም የራሳችንን ሀገር ሠራዊት ያለ ስሙ ስም መስጠት ተገቢ አይደለም ብለን እናምናለን።

ራስ ወልደ ጊዮርጊስ እስከ ሩዶልፍ ሐይቅ ሲዘምቱ እና የተበታተነውን መልሰው ሲሰበስቡ ታቦታ ይዘው አልዘመቱም። ነገሥታት ታቦት ይዘው የሚዘምቱት የውጭ ወራሪ ሲመጣባቸው እንጂ በሀገር ውስጥ አመጸኛ ሲነሣባቸው አለመሆኑን የታሪክ ድርሳናትን ማበላበጥ ከስሕተት ያድናል። ነገሥታት በሰላም ጊዜ የሚቀደስበት፣ በመከራ ጊዜ ካህናት ሱባኤ ይዘው መከራው እንዲርቅ የሚያደርጉበትን ታቦት ይዘው ቢዘምቱ ነውሩ ምኑ ላይ ነው? ነውር የሚሆነው ቤተ ክርስቲያን እና ምእመናን ሲፈጽሙት ነው እንዴ? ቤተ ክርስቲያን ከሠራዊታችን በየተዘዋወረበት አብራ እንደ ዘመተች ተደርጎ መጻፉ ሐሰት ነው፡፡ ራስ ወልደ ጊዮርጊስ  የአካባቢውን  ሰላም ካረጋገጡ  በኋላ የከፋ ገዥ ተደርገው ሲሾሙ የሚስቀድሱበት ቤተ ክርስቲያን ማሠራታቸው፣ በቤተ ክህነት ደረጃ ባይሆንም በግላቸው ቄስ ወስደው ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ ማድረጋቸው እውነት ነው። ኦርቶዶክስ በሰላማዊ መንገድ የሠራችው  እንደ ጥፋት ከተቈጠረ ከጀርመን  መጥቶ  በምዕራብ ወለጋ፣  በከፋ፣ በሲዳሞ፣ በጋሞ ጎፋ የፈጸመው ምን ሊባል ነው፡፡ እንደ Johann Ludwig Krapf ያሉ ጀርመናውያን ከ1837 እ.ኤ.አ. የኦሮሞን ሕዝብ ከግእዝ እና ከኢትዮጵያዊነት ለመነጠል የፈጸሟቸውን ጥፋቶች ተከትሎ በተከታታይ እስከ ዛሬ ምን እየተሠራ እንደሆነ ታሪክ ጸሐፊዎች ለመግለጥ አለመፈለጋቸው እውነትም ከታሪክ ጸሐፊነት ይልቅ አንድ የተደበቀ ርዕዮተ ዓለም የሚያራምዱ መሆናቸውን ይገልጣል፡፡ ከዐረብ የመጣው እስልምና ኢትዮጵያውንን ባርያ ብሎ እየፈነገለ ለዐረቦች ሲቸበችብ መኖሩን እነ አባ ጅፋር ሲፈጽሙት የኖሩትን የታሪክ መጻሕፍትን ማየት በቂ ማስረጃ ያስገኛል፡፡

ራስ ዳርጌ አርሲን ሲያስገብሩም ቤተ ክህነት አብራ አልዘመተችም። ምኒሊክ ሐረርን አስገብረው ከመሐል ሀገር ጋር ሲያስተሳስሩም ቤተ ክህነት አብራ አልነበረችም፡፡ ነበረች የሚል አካል ካለ መረጃውን ያቅርብ። የሆነው የሚያምኗቸውን የሐረርጌ ገዥ ለማድረግ ፈቃደኝነታቸውን ሲጠይቋቸው በማናውቀው ባሕል መካከል አንኖርም በማለታቸው ደጃዝማች መኮንን ወልደ ሚካኤልን ገዥ አደረጓቸው፡፡ ደጃዝማች መኮንንም በሐረርና አካባቢው ቤተ ክርስቲያን ያስፋፉት የአካባቢውን ሰው አሰገድደው ሃይማኖቱን በማስቀየር ሳይሆን ከሌላ አካባቢ ካህናትን በማምጣት ነው፡፡  አብሮ በመኖር አንዳንድ ክርስቲያኖች እስልምናን መቀበላቸው፣ አንዳንድ ሙስሊሞችም ክርስትናን መቀበላቸው ሊከሠት ይችላል። ጊዜ ያገኘ ሲመስለው ክርስቲያኑ ሙስሊሙን፣ ሙስሊሙም ክርስቲያኑን አሰቃይቶ ሊሆን ይችላል። አንድ ጊዜ  ከየመን፣ ሌላ ጊዜ ከቱርክ ፣ ሌላ ጊዜ ከግብፅ፣ በቅርብ ደግሞ ፋሽስት ኢጣሊያን ተገን አድርጎ ክርስቲያኖችን  ያሰቃየ እና ማዕተብ  ያስበጠሰ ማን እንደሆነ ይታወቃል። ሚዛናዊ የታሪክ ሊቃውንት ቢሆኑ ኖሮ ግራ ቀኙን መርምረው ሚዛናዊ ታሪክ ያቀርቡልን ነበር። የሠሩት ግን በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት እንደ ተባለው በመንግሥት በጀት እና በምርምር ስም የሚሠሩት ሌላ ነው፡፡

በአጠቃላይ የተዘጋጀው ጥራዝ ስሕተት የበዛበት በመሆኑ እንደገና ተስተካክሎ ሊቀርብ ይገባል። ለሀገርም ለትውልድም አሳቢ የሆኑ ምሁራን፣ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የሃይማኖት አባቶች ተወያይተውበት የጎደለው ሞልቶ፣ የተጣመመው ተስተካክሎ ተግባር ላይ መዋል እንዳለበት ማስገንዘብ እንፈልጋለን። ለወደ ፊትም ክፍተታችንን የሚሞላ እንጂ ይበልጥ እንድንለያይ እና በጥላቻ እንድንተያይ የሚያደርገንን ልቦለድ የታሪክ መጽሐፍ በማለት እንዳያቀርቡልን ምህራንን ማስገንዘብ እንፈልጋለን።