የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ (ገላ. ፮፥፪)

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

የክርስቶስ ሕግ ፍጻሜ ፍቅር ነው። ፍቅር አንድ ሰው ከሌላው ጋር በየዕለቱ የሚያደርገው ግንኙነት፣ በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ልባዊ መዋደድና ጥልቅ መንፈሳዊ ጸጋ ነው።በሰዎች መካከል በሚኖረው መልካም ግንኙነት የተነሳ አንዱ ለሌላው የሚያደርገው መልካም ነገር ሁሉ ፍቅር ነው።

ለሌላው የምናደርገው ይህ መልካም የሆነ ፍቅር በልዑል እግዚአብሔር ዘንድ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ በዚህም በዕለት ተዕለት ግኑኝነት ለተራበ ማብላት፣ ለተጠማ ማጠጣት፣ ለተቸገረ መርዳት፣ ያዘነን ማጽናናት፤ ይህን የመሰለውን መልካም ምግባር ሁሉ ሰው ለሰው ካለው ፍቅር የተነሳ የሚያደርገው ነው።

በዚህ መሰል ተግባር ለሌሎች መልካም ያደረጉትን ሁሉ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ በሚመጣ ጊዜ “የአባቴ በሩካን ኑ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ከሁሉ የሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ያደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት” በማለት የከበረ ዋጋ እንደሚሰጠን በወንጌል ተናግሯል። (ማቴ.፳፭፥፭፤፴፭-፴፮)

ሰውን መውደድና መርዳት ፍቅር ነውና ከፍቅር አምላክ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰማያዊ ዋጋን ያስገኛል። ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ መልካም እናድርግ”  ያለው በፍቅር የሚደረግ መልካም ነገር ሁሉ የሚያስገኘውን መንፈሳዊ ዋጋ በሚገባ ስለተረዳ ነው። (ገላ. ፮፥፲)

ይህ ፍቅር የተባለው ለሰው መልካም መሥራት፣ የሰውን ድካሙን ሳይቀር በመሸፈን መገለጥ የሚገባው ተግባር ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ይህን በተመለከተ “ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም፤ እንዲህም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ”  ብሏል፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ ሕግ የተባለው ፍቅር ነው፤ ይህም በተግባር መገለጥ ያለበት አስተምህሮ ነው። (ገላ.፮፥፪)

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጽኑ ፍቅሩ የተነሳ የሰው ልጆችን ሸክም ተሸክሞ ሞት የማይስማማው ሲሆን መዋቲ ሥጋን ተዋሕዶ ሞትን ድል እንዳደረገልን ሁሉ የሰውን ጉድለት  በመታገስ ወደ ድኅነት የሰው ልጅ እንዲደርስ ማድረግ ፍቅርን በተግባር መግለጥ ነው።

ፍቅር በመላእክት ልሳን ከመናገር በላይ የከበረ ነው። ፍቅር ከዕውቀትና ከልግሥና ሁሉ ይበልጣልና። ቅዱስ ጳውሎስም በፍቅር ያልተቀመመ እና ያልጣፈጠ ሥራ (ገድል) ሁሉ የማይጠቅም መሆኑን ነግሮናል፤ “ፍቅር ይታገሳል፣ ፍቅር ያስተዛዝናል፣ ፍቅር አያስመካም፤ ፍቅር ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም፤ ፍቅር ክፉ ነገርን አያሳስብም፤ ፍቅር ከእውነት ጋር ሁሌ ደስ ይለዋል፤ ፍቅር ሁሉን ያምናል እንዲሁም ፍቅር ዘወትር አይወድቅም” በማለት አስተምሮናል። (፩ኛ ቆሮንቶስ ፲፫፥፩-፲)

በዚህ መሠረት ፍቅር ለሚወደውና ለሚያፈቅረው ቸርነትን ያደርጋል፤ ይታገሳልም። ስለዚህ የራሱን ሳይቀር ይተውለታል፤ ይሰጠዋልም። የሚወደውን ሰው እንዳያጣው በትሕትና፤ በየዋህነትና በትዕግስት ያፈቅረዋል። ሰው ሁሉ ለሚወደው ቸርና ርኅሩኅ ነው ካለው ሁሉ በልግስና ያካፍለዋል፤ በማንኛውም ነገር ቢሆን አይጨክንበትም። (ኤፌ. ፬፥፪፤፴፪)

በእግዚአብሔር የሚታመን ክርስቲያን ሁሉ በፍቅር መኖር ይጠበቅበታል። በመስቀል ላይ ለቤዛ ዓለም የተሰቀለው መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው ሰውን ሁሉ መውደድ እንደሚገባን ነው።

አማናዊው ክርስትና እምነትና ትምህርትም በዚህ ፍቅር መገለጥ አለበት። ቅዱስ ጳውሎስ “በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምም” ብሎ አስተምሮናል። ይህም እምነትን የሚያንቀሳቅሰውና በምግባር እንዲገለጥ ሥራም እንዲሰራ የሚያደርገው ዋናው ፍቅር ነው። (ገላ. ፭፥፮)

ከዚህ ሌላ ለመንፈሳዊ ነጻነት ከተጠራንበት የክርስትና እምነታችን በተለያዩ የሥጋ ፈቃድና ፈተናዎች እንዳንሰናከል እና ፍሬ አልባ እንዳንሆን ሲያስጠነቅቀን “ወንድሞች ሆይ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኃልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያት አይስጥ፤ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ” በማለት እንድንጠነቀቅ ነግሮናል። (ገላ. ፭፥፲፫)

ሃይማኖትን በምግባር ለመግለጥ ፍቅር እጅግ አስፈላጊ ነው። ይሁንና በመጽሐፍ ቅዱስ “ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ፤ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ’’ ተብሏል፡፡ ከዚህ በመነሳት ፍቅር የእምነት ተግባራዊ የሥራ መገለጫ መሆኑን እንረዳለን። (ገላ. ፬፥፲፬)

በእኛ መካከል ፍቅር አለ ማለት በመካከላችን ፍጹም የሆነ አንድነትና መግባባት አለ ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ሰዎች በአንድ ፍቅር ይኖራሉ፤ አንድ ነገር ያስባሉ፤ በአንድ መንገድ ይጓዛሉ፤ እንዲሁም አንድ ልብ ይሆናሉ። በአንድ ወንጌል ለአንድ ሰማያዊ አገልግሎት የተጠሩ መሆናቸውን ይረዳሉ፡፡ “በአንድ ልብ ሆነው ይተጉ ነበር” (የሐዋ. ሥራ ፩፥፲፬)

ቅዱስ ጴጥሮስ “በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፤ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፤ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፤” በማለት እንዳስተማረን እኛም ስለፍቅር ስንል የሚዋደዱትን ሰዎች በመምሰል የእግዚአብሔር ማደሪያ የእውነተኛ ፍቅር ምንጭ እንሁን፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ “በፍቅር ተመላለሱ፤ ፍቅርን ተከታተሉ” ያለን። ሽንገላ የሌለበት ፍጹም ፍቅር የኃጢአት ጠላትና እንቅፋት መሆኑን እንወቅ። ፍቅር በእኛ መካከል ያለውን ክፋት የሚያስወግድ መንፈሳዊ መሳሪያ ነውና። ዛሬ የምንኖረው ኑሮም በፍቅር ካልጣፈጠ ትርጉም አይነረውም፤ የፍቅር ሰው መሆን በፍቅርም መኖር ተገቢ ነው። (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፰፤ኤፌ. ፭፥፪)

ቅዱስ ዳዊት “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ ያማረ ነው” በማለት ቃል ከፍቅር የሚመነጭ መተሳሰብ፣ መረዳዳት፣ መተዛዘን በጠቅላላው የልብ አንድነት ሊኖር እንደሚገባ ነግሮናል። (መዝ. ፻፴፪፥፪)

እንዲሁም “ማንም እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው። ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል እግዚአብሔርን የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን?” እንደተባለው ይህ የእግዚአብሔር ትእዛዝ መሆኑን እንወቅ። (፩ኛ ዮሐንስ ፬፥፳-፳፩)

የእርስ በርሳችን መዋደድ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ስጦታ ነው። በጽኑ የክርስትና እምነት መሠረት ላይ የታነጽን ሁሉ በዚህ ፍጹም ፍቅር ልንዋደድ ይገባል። ፍቅር የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመፈጸም የፈጣሪ ታማኝ አገልጋይና ወዳጅ የመሆን ማረጋገጫ ነው።

ቅዱስ ጴጥሮስም ”ለእውነት እየታዘዛችሁ ግብዝነት የሌለበት ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ ተዋደዱ” በማለት አስተምሮናል። (፩ኛ ፩፥፳፪-፳፫)

ቅዱስ ጳውሎስ “አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ አንሰጥም። ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች (ግብዝነት በሌለው ፍቅር) ራሳችን እናማጥናለን” በማለት እውነተኛ ፍጹም ፍቅር ከግብዝነት የነጻ መሆኑን አስረድቶናል። (፪ኛ ቆሮንቶስ ፮፥፫)

በወንድሞች መካከል የሚኖረው የእርስ በርስ ፍቅር በተወሰነ ጊዜ ታይቶ የሚጠፋ በአንድ ወቅት ፈክቶ በሌላ ጊዜ እንደሚጠወልግ አበባ መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ በጽኑ እምነት ላይ በቅሎ በጊዜው ሁሉ እያበበ መንፈሳዊ በረከትንና ረድኤተ እግዚአብሔር እያፈራ የሚኖር ዘላቂ መሆን ይገባዋል። ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ”እኛ ደግሞ ለእናንተ እንደምንሆን ጌታ እርስ በርሳችሁ ያላችሁን ለሁሉም የሚሆን ፍቅራችሁን ያብዛ  ይጨምርም” በማለት የጸለየልን። (፩ኛ ተሰ. ፫፥፲፫)

አባቶቻችን እንዳደረጉት ሁሉ ፍቅር እንዲጸናና አድጎም ፍሬ እንዲያፈራ በጸሎት የታጠረና በጥንቃቄ የሚጠበቅ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ቅዱስ ጴጥሮሰ “ስለዚህም  ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ እግዚአብሔርን በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፣ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ” ብሏል፡፡ ፍጹም ሰማያዊ ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሊጓዝ የሚገባ የክርስትና ሕይወት ማጣፈጫ እንደሆነ በመረዳት ፍቅራችን ከግብዝነትና ከወረት ነጻ ሆኖ ሕግጋትን በመፈጸምና በማክበር በተግባር የሚገለጥ እንዲሆን መጸለይ አለብን። (፪ኛ ጴጥ. ፩፥፯)

የለመኑትን የማይነሣ የነገሩትን የማይረሳ ልዑል እግዚአብሔር ለቀደሙት አበው እንደተለመነ ሁሉ እኛን እንዲለመነን፣ የፍቅር ሰዎች እንዲያደርገን፣ በፍቅሩ በመጽናትም መንግሥቱን ለመውረስ እንዲያበቃን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡