የእመቤታችን ኀዘን ስለ ጌታችን መከራ

መጋቢት ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

… ለእኔስ በተሰቀለው ላይ ልቅሶ አለኝ፤ ‹‹በመስቀል ላይ ሞትህን?›› እላለሁ፡፡ የመስቀልህ ጥላ ሙታንን ሲያስነሣም ዐውቃለሁ፤ በመስቀል ላይ ዘንበል ማለትህን አደንቃለሁ፡፡ የሲኦልን መታወክ፣ በውስጧ ያሉ ሰባት መቶ የብረት በሮች እንደ ተሰበሩ አስታውሳለሁ፡፡ በዚያ ታስረው የነበሩትንም ከአባታቸው ከአዳም ጋር አወጣሃቸው፡፡ በዚያች ዕለትም ወደ ርስታቸው ወደ ገነት አስገባሃቸው፡፡ ነፍስህ ከሥጋህ በተለየች ጊዜም አለቅስሁ፡፡ በቀኝ ተሰቅሎ ለነበረው ወንበዴ አምስት ሺሕ አምስት መቶ ሠላሳ ሦስት ዘመን ተዘግታ የኖረች ገነትን በከፈትህ ጊዜም ተደሰትሁ፡፡

በዕንጨት መስቀል በሰቀሉህ ጊዜ ላልቅስ? ወይስ ፀሐይ በጨለመ ጊዜ ልደንግጥ? በመስቀል ላይ ራቁትህን ኾነህ በተመለከትሁህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ቀኑ ሌሊት በኾነ ጊዜ ልደነቅ? ‹‹ክርስቶስ ሆይ! ማን መታህ? ንገረን!›› እያሉ በመቱህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት፤ በመስቀል የተሰቀለ›› እያሉ ለማመስገን እልፍ አእላፍ ፍጥረታት ሲወድቁልህ ልደሰት? መጣጣዉን ከሐሞት ጋር ቀላቅለው ባጠጡህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ አምላካዊ የኾነች ደም፣ ከመስቀሉ ታችም ንጹሕ ውኃ በፈሰሰ ጊዜ?

የመለኮት ደም ዐለቱን ሰንጥቆ የአባታችን የአዳምን መቃብር አልፎ በአዳም አፍ ስለ መግባቱ ስለ ማዳኑም አደንቃለሁ፡፡ ስለዚህም ወንጌላዊው ‹‹ዐለቱ ተሰነጠቀ፤ የጻድቃን በድኖች ተነሡ፤›› አለ (ማቴ. ፳፯፥፶፩-፶፬)፡፡ በፊትህ ምራቅ በተፉብህ ጊዜ ላልቅስ? ወይስ ዕውር ኾኖ የተወለደዉን በማዳንህ ልደሰት? በአንገትህ ሐብል ባደረጉብህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ሰይጣን ያሰራቸዉን ስትፈታቸው ላመስግንህ? ታስረህ በጲላጦስ ፊት ሲያቆሙህ ላልቅስን? ወይስ በባሕሩ እንደ የብስ ሔደህ ነፋሳትን እንደ ሎሌ በመገሠፅህ ላድንቅ? ወይስ ነቢያት አንተን ለማየት በመመኘታቸው ልደሰት?

ዛሬ በሁለት ወንበዴዎች መካከል ባየሁህ ጊዜ ላልቅስን? ከሌቦች፣ ከወንበዴዎች፣ ዓለሙን ዂሉ ካስለቀሱት ጋር በመስቀል በሰቀሉህ፣ በቸነከሩህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ በሙሴና በኤልያስ መካከል የመንግሥትህ ግርማ በታወቀ፤ የመለኮትህ ብርሃን ባንጸባረቀ ጊዜ ልደሰት? በቀራንዮ መስቀልን በተሸከምህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ መጻጕዕን ‹‹ኀጢአትህ ተሰረየልህ፤ ተነሥና አልጋህን ተሸከም፤ ሔደህም ወደ ቤት ግባ፤›› (ዮሐ. ፭፥፰) በማለትህ ልደሰት? ሐና እና ቀያፋ ‹‹ደሙ በእኛና በልጆቻችን ይኹን›› ባሉህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረችዉን ሴት በልብስህ ጫፍ በማዳንህ ልደሰት? በይሁዳ አማካይነት በሠላሳ ብር በመሸጥህ ላልቅስን? ወይስ ከዓሣ ሆድ ዲናር ያወጣ ዘንድ፣ በአንተ እንዳያጕረመርሙም ለቄሣር ግብር ይሰጥ ዘንድ ጴጥሮስን ባዘዝኸው ጊዜ ልደሰት?

በመስቀል ላይ ሳለህ ‹‹ተጠማሁ›› (ዮሐ. ፲፱፥፳፰) ስትል ላልቅስን? ወይስ በቃና ዘገሊላ ውኃዉን ወይን በማድረግህ ልደሰት? እናትህ እኔ በጉባኤው መካከል የፊቴን መሸፈኛ ገልጬ ስመለከት፣ ዮሐንስ ‹‹ልጅሽ ሞተ›› ባለኝ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ገብርኤል ‹‹ከአንቺ የሚወለደው የእግዚአብሔር ቃል በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም፤›› (ሉቃ. ፩፥፴-፴፫) እያለ በነገረኝ ጊዜ ልደሰት? ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ሥጋህን ለመገነዝ ሽቱ ሲገዙ ባየኋቸው ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ምድራዊ ሳሙና እንደዚያ አድርጎ ማጽዳት የማይቻለው ፀዓዳ የኾነ የመንግሥት ልብስህን ባየሁ ጊዜ ልደሰት?

ሥጋህን ለመቅበር አዲስ መቃብር በፈለጉ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ከአራት ቀናት በኋላ አልዓዛርን ከመቃብር ባስነሣኸው ጊዜ (ዮሐ. ፲፩፥፵፫-፵፬) ልደሰት? በአፍህ መራራ ሐሞትን በጨመሩብህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ከሴቶችና ከሕፃናቱ ሌላ በአምስት እንጀራ ለአምስት ሺሕ ሕዝብ በማጥግብህ፣ ተርፎም ዐሥራ ሁለት ቅርጫት በመነሣቱ (ማቴ. ፲፭፥፲፯-፳፩) ልደሰት? በመቃብርህ ላይ ድንጋይ በገጠሙበት ጊዜ ላልቅስን? ወይስ በአህያና ላም ባሟሟቁህ ጊዜ ላድንቅ? በሙታን መካከል በተኛህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ በጦር የወጋህን ሰው የታወረ ዓይኑን በመዳሰስ ባዳንኸው ጊዜ ልደሰት?

በመስቀል በምትጨነቅበት ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ወንበዴዉን ‹‹ዛሬ እውነት እልሃለሁ፤ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ፡፡ ፈጽመህ እመን፤›› (ሉቃ. ፳፫፥፵፫) ባልኸው ጊዜ ልደሰት? የተረገሙ አይሁድን ምን እንላቸዋለን? በዮርዳኖስ ውኃ ዓለሙን የሸፈነዉን ራቀቱን ሰቅለውታልና፡፡ ዓለምን ከኀጢአት ሞት ያዳነ እርሱን ገድለውታልና፡፡

ምንጭ፡- ርቱዐ ሃይማኖት፣ መ/ር ተስፋ ሚካኤል ታከለ፤ ፳፻፬ ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፤ ገጽ 211-214)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡