የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን የሃይማኖት ነጻነት የሚጋፋ መመሪያ ማውጣቱ ተገለጸ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሃይማኖታዊ ነጻነታቸውን የሚጋፋ መመሪያ መውጣቱን ገለጹ፡፡ ዮኒቨርስቲው በ፳፻፲፯ ዓ.ም ያወጣውን የሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን መመሪያ ተከትሎ ይህንን መመሪያ ማውጣቱን ተማሪዎቹ አክለው ገልጸዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤ ማስተባበሪያ ኀላፊ የሆኑት አቶ አበበ በዳዳ ለቴሌቭዝን አገልግሎት ክፍል እንደገለጹት ከሆነ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች በመመገቢያ አዳራሽ በሚገኙበት ጊዜ ነጠላ መልበስና መብልን አውጥተው መመገብ የማይችሉ ሲሆን ይህ ሃይማኖታዊ መብታቸውን የሚጋፋ የሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን መመሪያ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አቶ አበበ በዳዳ “ጠቅላይ ቤተ ክህነት ኦርቶዶክሳውያን የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች ሃይማኖታዊ የመብት ጥሰት እንዳይፈጸምባቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መወያየት ይገባል” በማለት አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲው በ፳፻፲፯ ዓ.ም ባወጣው የሥነ ምግባር ዲስፕሊን መመሪያ “የተለያዩ እምነት ተከታይ ተማሪዎች በግቢው ስለሚያስተናገዱ ከሃይማኖትና ከበዓላት ጋር የተያያዙ የአለባበስ ሥርዓቶች የማንነትና የእምነት መገለጫዎች በመሆናቸው ሊከበሩ ይገባቸዋል” እንደሚል ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን ተማሪዎቹ “የኒቨርሲቲው ሃይማኖታዊ ነጻነታችንን የሚጋፋ መመሪያ አውጥቷል” በማለት ገልጸዋል፡፡
ይህ ብቻም ሳይሆን እነዚህ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎቹ “በምግብ ሰዓት የሕሊና ጸሎት ካልሆነ በቀር ጸሎት እንዳናደርግና ከዳቦ ውጭ ምግብ እንዳናወራ እንዲሁም በመመግቢያ አዳራሽ ውስጥ ነጠላ እንዳንለብስ መመሪያ ወጥቷል” ሲሉ መናገራቸው ታውቋል፡፡
አስከትለውም “የወጣውን መመሪያ ምክንያት በማድረግ በአንዳንድ የጥበቃ አካላትና ግለሰቦች ጫና እየተደረገብን ነው፤ ምግባችንን አውጥተን ለነዳያን መስጠትና መንፈሳዊ ጉዞ በምናከናውንበት ወቅት አውጥተን መጠቀም እንዳንችል ተደርጓልም” ብለዋል፡፡
የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኀላፊ አቶ አበበ በዳዳ ይህንን አስመልክቶ “ዩንቨርሲቲው በመጀመሪያው ረቂቅ መመሪያ ያወጣቸው ሕጎች ለኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች በጣም አስቸጋሪ ነበሩም” በማለት የገለጹ ሲሆን በተማሪዎች በተቋቋመ ኮሚቴ በመመሪያው አንዳንድ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ በቀረበው አስተያየት መሠረት ከበፊቱ የተሻለ ቢሆንም አሁንም ግን የተማሪዎችን ሃይማኖታዊ መብት የሚጋፋ መመሪያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
“በተለይም ነጠላን አላስፈላጊ ልብስ በማለት የተገለጸው መመሪያ አግባብነት የሌለው ነው” በማለት የተናገሩት አቶ አበበ በዳዳ ይህ አካሄድ ሀገርን የማይጠቅም በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ አሳስበው ዩንቨርሲቲው አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ ሰዎች በልዩ ሁኔታ ሃይማኖቱ የሚፈቅደውን አለባበስ መልበስ ይችላሉ የሚል መመሪያ ስላለው የሚመለከታቸው አካላት ውይይትና ምክክር እንዲያደርጉ መልእክት ማስተላለፋቸው ታውቋል፡