addis ab 03

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር ረቂቅ መመሪያ ርክክብ ተካሔደ

የካቲት 6 ቀን 2006 ዓ.ም.

በመምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

addis ab 03ዐሥራ ሦስት የመመሪያ ረቂቅ ሰነዶችን ከ12/11/2005 ዓ.ም ጀምሮ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሲያጠናና ሲያወያይ የነበረው 18 አባላት ያሉት አጥኚ ኮሚቴ ዛሬ የካቲት 6 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተደረገው የመረካከቢያ መርሐ ግብር ረቂቅ ሰነዶችን ለብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ረዳትና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አስረከቡ፡፡

በርክክቡ ወቅት ንግግር ያደረጉት የአጥኚው ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ አሠፋ እንደገለጹት “ቡድኑ የልጅነት ድርሻውን ይወጣ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊነት ስትሰጠው ወደ ዋና ጥናቱ ከመግባቱ በፊት ሥራው የተቃና ይሆን ዘንድ በአባቶች ጸሎት እንዲታሰብ መብዓ አሰባስቦ መላኩ ለጥናት ቡድኑ ብርታት እንዲሁም ሥራ መጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጐለታል፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት የቅዱሳን ጸሎት አልተለየንም” ብለዋል፡፡

በመቀጠልም “ጥናቱን እያጠናን ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ አጥቢያ ምእመናን ድረስ በማወያየት 96 በመቶ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን በውይይቱ ወቅት እንዲካተቱ የተነሡ ነጥቦች ተካተውና ተሻሽለው ለዚህ ቀን ደርሰናል፡፡ ጥናቶቹም፡-

 1. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመዋቅር የአደረጃጀት ጥናትና መመሪያ 119 አንቀጽ

 2. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአብያተ ክርስቲያናት የደረጃ መስፈርት መመሪያ 23 ገጽ

 3. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአገልግሎት መደቦች የሥራ ዝርዝር መመሪያ 120 ገጽ

 4. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰው ኃይል ትመናና የተፈላጊ ችሎታ መስፈርት መመሪያ 53 ገጽ

 5. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደመወዝ ስኬል ጥናት 99 ገጽ

 6. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአገልግሎጋዮች ማስተዳደሪያ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ 125 ገጽ

 7. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥልጠናና የሰው ሃብት ልማት ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ 30 ገጽ

 8. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፋይናንስ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ 107 አንቀጽ

 9. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የግዢ፣ ሽያጭና ንብረት አስተዳደር መመሪያ 26 ገጽ

 10. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የልማት ሥራዎች ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ 16 ገጽ

 11. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዕቅድና ሪፖርት ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ መመሪያ 31 ገጽ

 12. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የኦዲትና ኢንስፔክሽን ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ 57 ገጽ

 13. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥልጠና ማእከል፣ ወላጅ አልባ ሕፃናትና የአረጋውያን መርጃ ማእከል ፕሮጀክት ጥናት ሰነድ /የተሠጠ/

ሲሆኑ የዚህ ጥናት ትግበራ ስልትና የእያንዳንዱ መመሪያና ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ብዛት ያላቸው ቅጾች ለትግበራ ስለሚያስፈልጉ ወደፊት ተጠናቀው ይቅርባሉ”addis ab 02 በማለት ገልጸው ሰብሳቢው የአጥኚው ቡድን አባላት ለብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጥናት ሰነዱን እንዲያስረክቡ ካደረጉ በኋላ “በዚህ ጥናቱን በሚመለከት ማብራሪያ ለሚጠይቀን አካል ሁሉ ምላሽ ለመስጠትና ለመወያየት ዝግጁ ነን” በማለት ገልጸዋል፡፡

ከአጥኚ ኮሚቴው በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ በላይ መኰንን “እንደገለጹት ለቤተ ክርስቲያን ብላችሁ ጊዜያችሁን ገንዘባችሁን ሁሉን ነገር አውጥታችሁ የሠራችሁትን እግዚአብሔር ዋጋችሁን ይክፈላችሁ፡፡

እግዚአብሔር ለሥራ ጊዜ አለው፡፡ ሁሉም ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ነው፡፡ ቅዱስ አባታችንም ጥናቱ ለምን ቆየ? ከምን ደረሰ? እያሉ እየጠየቁ ነው፡፡ የተቃውሞ ጥያቄ የሚያነሱትም ነፃ አስተሳሰብ ነውና ሊመሰገኑ ይገባል” ብለዋል፡፡

ጥናቱን የተረኩበት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ባደረጉት ንግግር “መነሻ የሚሆን ነገር እንድናቀርብ በመጠየቃችን እናንተም ይህን በመሥራታችሁ እግዚአብሔር በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ ያድላችሁ፡፡

በእግዚአብሔር የምንጠየቀው የሚጠብቅብንን ሳንሠራ ስንቀር ነው፤ የታዘዛችሁትን አዘጋጅታችሁ አቀርባችኋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ተግባራዊ ያደርገዋል፡፡ ሆን ብሎ ለጥፋት የሚሰለፍ የለም አስተሳሰባችን በመለያየቱ እንጂ፡፡ ከዚህ በተመሳሳይ ቃለ ዓዋዲው መጀመሪያ ሲረቀቅ ብዙ ተቃውሞ ቀርቦበት ነበር፤ ግን ተግባራዊ ሆነ፡፡ ከዚህ በኋላ የሚያስፈልገው ሁላችንም ወደ አንድ መጥተን ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅመውን ማድረግ ነው” በማለት አባታዊ ምክር ሰጠተዋል፡፡ በመጨረሻም በርክክቡ መርሐ ግብር ላይ ለተገኙት ተሳታፊዎች የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ የምሳ ግብዣ አድርገዋል፡፡