የአምላክ እናት መገለጥ!

ግንቦት ፲፱፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ‹‹በዓለ ደብረ ምጥማቅ›› አደረሳችሁ!

አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በደብረ ምጥማቅ በስሟ በተሠራች ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ በብርሃን መርከብ ተቀምጣ ፊቷ በግልጥ ስለ መታየቱ የክርስቲያን ወገኖች ሁላችንም ታላቅ በዓልን እናደርጋለን።

እርሷም በልጅዋ የመለኮት ብርሃን የተጐናጸፈች ናት፤ በዙሪያዋም የመላእክት ሠራዊት የመላእክት አለቆችም በየማዕረጋቸው ክንፋቸውን ዘርግተው ይቆሙ ነበር፤ ይጋርዷታልም። ሱራፌልም ማዕጠንታቸውን ይዘው ለንግሥዋ ገናናነት ይሰግዳሉ፤ በየስግደታቸውም እንዲህ እያሉ ያመሰግኗታልኳ ‹‹አብ በሰማይ ሁኖ ተመለከተ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም፤ አንድ ልጁንም ልኮ ከአንቺ ሰው ሆነ።››

ሁለተኛ ሰማዕታትም በየማዕርጋቸው ረቂቃን በሆኑ ፈረሶቻቸው ተቀምጠው እየመጡ መጀመሪያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምባላይ ፈረሱ ወርዶ ይሰግድላታል፤ እንዲሁም ባልንጀሮቹ ሰማዕታት መጥተው ይሰግዱላታል።

ከእርሱ በኋላ የሚመጣው በዱሪ ፈረስ የሚቀመጥ ይህ መርቆሬዎስ ነው። ከዚህም በኋላ ሰማዕታት ሁሉ በመከታተል መጥተው ይሰግዱላታል፤ ምስጋናም ያቀርቡላታል። ሁለተኛም ደግሞ የጻድቃን አንድነታቸው መጥተው በፊቷ ሰግደው ይመላለሳሉ።

ሄሮድስ የገደላቸው ሕፃናትም መጥተው ይሰግዱላታል፤ በፊቷም እየዘለሉ አንዱ በአንዱ ላይ እየዘለለ በመተቃቀፍም ይጫወታሉ፤ የተሰበሰቡትም በአዩ ጊዜ ደስታ ይመላባቸዋል፤ በሰማይም ያሉ ይመስላቸው ነበር።

እናትና አባቱም የሞቱበት ቢኖር ወይም ከዘመዶቹ ወይም ባልንጀራው ‹‹ቅድስት ድንግል እመቤቴ ሆይ ዕገሌን አሳዪኝ›› ብሎ በሚለምናት ጊዜ ቀድሞ በነበረበት መልኩ ያን ጊዜ ታመጣዋለች። ደግሞ መሀረባቸውን ወደ ላይ ይወረውሩላታል፤ የወደደችውንም በእጇ ተቀብላ መልሳ ትጥልላቸዋለች፤ ለበረከትም በየጥቂቱ ይካፈሉታል።

እንዲህም አምስት ቀን ሁሉ ክርስቲያንም፣ እስላሞችም፣ አረማውያንም ያይዋታል። ወደ ቤታቸውም ለመሔድ ሲሹ በፊቷ ሰግደው ይሰናበቷታል፤ እርሷም ትባርካቸውና ይመለሳሉ።

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጀነት፣ ተረዳኢነትና በረከት አይለየን፤ አሜን!

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ግንቦት ሃያ አንድ ቀን