የትንሣኤ በዓል ትርጕሙና አከባበሩ

በሊቀ ትጉሃን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኘ

ሚያዝያ ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሰን!

«ትንሣኤ» የሚለው ቃል የግእዝ ቃል መገኛው ‹ተንሥአ = ተነሣ› የሚለው ግስ ሲኾን፣ ትርጕሙም መነሣት፣ አነሣሥ፣ አዲስ ሕይወትን ማግኘት ማለት ነው፡፡ ‹ትንሣኤ› በየመልኩ፣ በየዓይነቱ ሲተረጐም አምስት ክፍል አለው፤

የመጀመርያው ትንሣኤ ሕሊና ነው፤ ይህም ማለት ተዘክሮተ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን ማሰብ) ነው፡፡

ሁለተኛውም ትንሣኤ ልቡና ነው፤ የዚህም ምሥጢሩ ቃለ እግዘብሔርን መስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር ነው፡፡

ሦስተኛው ትንሣኤ ለጊዜው (በተአምራት) የሙታን በሥጋ መነሣት ነው፡፡ ነገር ግን በድጋሜ ሌላ ሞት ይከተለዋል፡፡

አራተኛው ትንሣኤ ክርስቶስ በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን ያመላክታል፡፡ የርእሰ ትምህርታችን መነሻም ይህ ነው፡፡

አምስተኛውና የመጨረሻው የትንሣኤ ደረጃ የባሕርይ አምላክ የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ መሠረት ያደረገ ትንሣኤ ዘጉባኤ ሲኾን፣ ይህም ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ዅሉ እንደየሥራው ለክብርና ለውርደት፣ ለጽድቅና ለኵነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ ነው፡፡

ወደ ርእሳችን ስንመለስ የትንሣኤ በዓል በምሥጢሩም፣ በይዘቱም ከኦሪቱ በዓለ ፋሲካ ጋር ስለሚመሳሰል ‹ፋሲካ› ተብሎ ይጠራል፡፡ ‹ፋሲካ› ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹ፌሳሕ›፤ በጽርዕ (በግሪክ) ‹ስኻ› ይባላል፡፡ ይህም ወደ እኛው ግእዝና አማርኛ ቋንቋችን ሲመለስ ፍሥሕ (ደስታ)፣ ዕድወት፣ ማዕዶት (መሻገር፣ መሸጋገር)፣ በዓለ ናእት (የቂጣ በዓል፣ እየተቸኮለ የሚበላ መሥዋዕት) ማለት ነው፡፡ የዚህም ታሪካዊ መነሻው በዘመነ ኦሪት ይከበር የነበረው በዓለ ፋሲካ ሲኾን፣ ይህም እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ የባርነት ቀንበር ወደ ነጻነት የተላለፉበት፤ ከከባድ ኀዘን ወደ ፍጹም ደስታ የተሸጋገሩበት በዓል ነው፡፡ በዚህ ኦሪታዊ (ምሳሌ) በዓል አሁን አማናዊው በዓል በዓለ ትንሣኤ ተተክቶበታል፡፡

ፋሲካ (በዓለ ትንሣኤ) በዘመነ ሐዲስ እስራኤል ዘነፍስ የኾንን ምእመናን የክርስቶስን ትንሣኤ የምናከብርበት ዕለት ነው፡፡ ይህ በዓል ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፤ ከውርደት ወደ ክብር፤ ከጠላት ሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነጻነት፤ ከአደፈ፣ ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ አዲስ ሕይወት የተሻገርንት ከበዓላት ዅሉ የበለጠ የነጻነት በዓል ነው፡፡ ስለዚህም ክርስቲያኖች በታላቅ ደስታና መንፈሳዊ ስሜት በዓሉን እናከብረዋለን፡፡

መድኃኒታችን ሞትን በሞቱ ድል ነስቶ፣ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ፣ በሥልጣኑ የተነሣው መጋቢት ፳፱ ቀን በ፴፬ ዓ.ም እንደ ኾነ ታሪከ ቤተ ከርስቲያን ያስረዳል፡፡ የትንሣኤ በዓል መከበር የጀመረው በቅዱሳን ሐዋርያትና በሰብዐ አርድእት፣ ኋላም በየጊዜው በተነሡ ሊቃውንትና ምእመናን ነው፡፡ ድምቀቱና የአከባበር ሥርዓቱ ይበዛ፣ ይቀነስ እንደ ኾነ እንጂ በዓሉ መከበሩ ተቋርጦ አያውቅም፡፡

በቅብብሎሽ ከዚህ በደረሰው ትውፊት መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሙነ ሕማማት ግብረ ሕማማቱን ስታነብ ሰንብታ ለትንሣኤ እሑድ አጥቢያ ማታ በ፪ ሰዓት «ለጸሎት ተሰብሰቡ» ስትል የደወል ድምፅ ታሰማለች፡፡ ካህናቱም በቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው ሥርዓቱን በጸሎት ይጀምራሉ፡፡ ሕዝቡም በቤተ ክርስቲያን ይሰባሰባል፡፡ ካህናቱ መዝሙረ ዳዊት፣ ነቢያት፣ ሰሎሞንና ውዳሴ ማርያም ከተደረሰ በኋላ «ተፈሥሒ ማርያም ለአዳም ፋሲካሁ» የሚለውን ግጥማዊ የደስታ መዝሙር ይዘምራሉ፡፡

ምንባቡ፣ ጸሎቱና ሌላውም ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ጸሎተ አኰቴት ተደርሶ ዲያቆኑ ነጭ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ፣ አክሊል ደፍቶ፣ መስቀል ይዞ፣ በጌታችን መቃብር በራስጌና በግርጌ በታዩት መላእክት ምሳሌ እንደ እርሱው ነጭ ልብሰ ተክህኖ በለበሱ፣ ድባብ ጃንጥላ በያዙ፣ መብራት በሚያበሩ ሁለት ዲያቆናት ታጅቦ በቅድስት ቆሞ፡- «ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም፣ ወከመ ኀያል ወኅዳገ ወይን፣ ወቀተለ ፀሮ በድኅሬሁ፤ እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤ የወይን ስካር እንደ ተወው ኃያል ሰውም ጠላቱን በኋላው ገደለ፤» የሚለውን የዳዊት መዝሙር በረጅም ያሬዳዊ ዜማ ይሰብካል (መዝ. ፸፯፥፷፭)፡፡

ካህናቱም ከበሮ እየመቱና በእርጋታ እያጨበጨቡ ተቀብለው ይዘምራሉ፡፡ ሕዝቡም በጭብጨባና በዕልልታ የደስታ ዝማሬው ተሳታፊ ይኾናል፡፡ ይህ ምስባክ በዲያቆኑና በመላው ካህናት ሁለት ሁለት ጊዜ፤ በዲያቆኑና በመላው ካህናት አንድ ጊዜ (በጋራ) ይዘመራል፡፡ ይህም በድምሩ አምስት መኾኑ አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም በጌታችን ሞትና ትንሣኤ ዓለም ለመዳኑ ምሳሌያዊ ማስረጃ ነው፡፡ በመቀጠል ካህኑ ትንሣኤውን የሚያበሥር ትምህርት ከማቴዎስ፣ ከማርቆስና ከሉቃስ ወንጌል አውጥቶ ያነባል፡፡ የዮሐንስ ወንጌል በቅዳሴ ጊዜ ይነበባል (ዮሐ. ፳፥፩-፱)፡፡

በማስከተል ከሊቃውንቱ መካከል ሥራው የሚመለከተው ወይም የተመደበው ባለሙያ (መዘምር) መስቀል ይዞ «ትንሣኤከ ለእለ አመነ» የሚለውን እስመ ለዓለም ከቃኘ በኋላ ለበዓሉ ተስማሚ የኾነው አርያም ተመርቶ በመቋሚያ ይዘመማል፡፡ ከዚያም «ዮም ፍሥሐ ኮነ በሰንበተ ክርስቲያን፣ እስመ ተንሥአ ክርስቶስ እሙታን = ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና በሰንበተ ክርስቲያን ዛሬ ደስታ ኾነ …፤» የሚለው አንገርጋሪ በመሪና በተመሪ ይመለጠናል፤ በግራ በቀኝ እየተነሣ ይዘመማል፤ ይጸፋል፡፡

በዚህ ጊዜ «በጨለማ የነበራችሁ ሕዝቦች የትንሣኤውን ብርሃን እዩ፤ ብርሃኑንም ወስዳችሁ የብርሃኑ ተካፋይ ኹኑ፤» እያለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጀችውን ጧፍ እያበራች ታድላቸዋለች፡፡ ወዲያውኑም ‹‹ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ = ለአመነው ለእኛ ብርሃንህን ላክልን፤›› የሚለውን እስመ ለዓለም እየዘመሩ፣ መብራት እያበሩ ካህናቱና ሕዝቡ ዑደት ያደርጋሉ (ቤተ ክርስቲያኑን ይዞራሉ)፡፡

መዘምራኑና ካህናቱ ከዑደት ሲመለሱ «ይእቲ ማርያም» የተባለው የኪዳን ሰላም ይጸፋና ኪዳን ተደርሶ ሲያበቃ እንደ ቦታው ደረጃ ፓትርያርክ ወይም ሊቀ ጳጳስ ወይም ቆሞስ ወይም ቄስ ዘለግ ባለ ድምፅ በንባብ «ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን = ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ» ሲሉ ካህናቱና መዘምራኑ ‹‹በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን = በታላቅ ኃይልና ሥልጣን» ብለው ይቀበላሉ፡፡ አሁንም ካህኑ «አሰሮ ለሰይጣን = ሰይጣንን አሰረው» ባለ ጊዜ መላው ካህናት «አግዐዞ ለአዳም = አዳምን አርነት ነጻ አወጣው» ይላሉ፡፡

በመቀጠል «ሰላም = ሰላም፣ አንድነት፣ ፍቅር» ሲሉ ዅሉም «እምይእዜሰ = ከዛሬ ጀምሮ» ብለው ይቀበላሉ፡፡ ካህኑም «ኮነ ፍሥሐ ወሰላም = ሰላምና ደስታ» ብለው ሦስት ጊዜ አውጀው «ነዋ መስቀለ ሰላም» እያሉ መስቀል ሲያሳልሙ ካህናቱና ሕዝቡም «ዘተሰቅለ ቦቱ መድኃኔ ዓለም» እያሉ ይሳለማሉ፡፡ ካህኑም «እግዚአብሔር ይፍታ» ይላሉ፡፡ ግብረ ሕማማት ሲነበብበት ከሰነበተው ጠበልም ይረጫል፡፡ የተረፈውንም ጠበል ሕዝቡ ለበረከት ወደየቤቱ ይወስደዋል፡፡

ከዚያም ልኡካኑ ለቅዳሴ እየተዘጋጁ መዘምራኑ ምስባክ መወድሱን ካዜሙ በኋላ በመቋሚያ ይዘሙታል፡፡ አያይዞም ይትፌሣሕ› የተባለውን መዝሙር ቃኝተው ከዘመሙ በኋላ «… ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ፤ ተኀፂባ በደመ ክርስቶስ = … ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካውን ታደርጋለች፤» እያሉ ይጸነጽላሉ፡፡ አያይዘውም የመዝሙሩን ሰላም ይጸፋሉ፡፡ መንፈቀ ሌሊት ሲኾንም ቅዳሴ ተቀድሶ ሥርዓተ ቍርባን ይፈጸማል፡፡ ከዚያም ሠርሖተ ሕዝብ = የሕዝብ ስንብት ከኾነ በኋላ ካህናቱም ሕዝቡ ወደየቤታቸው ሔደው እንደየባህላቸው ይፈስካሉ (ይገድፋሉ)፡፡

የመግደፊያ ዝግጅት ለሌላቸው ነዳያንም በየመንደሩ እየተዞረ «እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ» እየተባለ ከሥጋውም፣ ከአይቡም፣ ከቅቤውም ከመጣጣሙም፣ ከእርጐውም ይታደላል፡፡ ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤ ድረስ ሕዝበ ክርስቲያኑ «እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ» እየተባባለ በዚህ መልኩ አብሮ እየበላ፣ እየጠጣ፣ እየተደሰተ እግዚአብሔርን ሲያመሰግን ይሰነብታል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡