የተቀደሰ ውኃ
ቀሲስ ኃይሉ ብርሃኑ
ሰኔ ፱፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ውኃ በመጀመሪያ ቀን ከተፈጠሩት ፍጥረት የሚመደብ ሲሆን “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።” (ዘፍ.፩፥፩-፪)
በምልአት የነበረን ውኃ እግዚአብሔር በሦስት ከፈለው፡፡ ከምድር በታች “ምድርን በውኃ ላይ ያጸና፤ ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና”*እንዳለ ነቢዩ ዳዊት፡፡ (መዝ. ፻፴፮፥፮) በምድር ገጽ ላይ “እግዚአብሔርም የብሱን ምድር ብሎ ጠራው፤ የውኃ መከማቻውንም” ስሙም ውቅያኖስ ተባለ። (ዘፍጥረት ፩፥፲)
ከምድር በላይ ባለው ቀላያት ላይ ጠፈር እንዲሆን ሰቀለው። ጠፈር ማለት “ኀይል፣ ጽንዕ” ማለት ነው። አንድም “ቤት” ማለት ነው፤ በውስጡ ሰው አራዊት እንስሳት ይኖሩባታልና (ኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ) “እግዚአብሔርም በውኆች መካከል ጠፈር ይሁን፥ በውኃና በውኃ መካከልም ይክፈል አለ” እንዲል፡፡ (ዘፍ. ፩፥፮) ከጠፈር በላይም ያለውን ውኃ ለይቶ ሐኖስ ብሎታል። “እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፥ ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉትንም ውኆች ለየ፤ እንዲሁም ሆነ።” (ዘፍ. ፩፥፯)
በተለየ መልኩ ስናየው ውኃ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ማየ ሕይወት ነው፤ ሕይወት የሚገኝበት የሕይወት መገኛ ነው። “የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር” እንደተባለው (ዘፍ.፩፥፪) ለማያት ሕይወት የሚሆናቸው፣ የሚያጠራቸው መንፈስ ቅዱስ ነው። ይህም በኋላ በጥምቀት የሚሰጥ የሀብተ መንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው። እግዚአብሔር ውኃን በራሱ ግብር ፈጥሮታል፤ እንዴት ቢሉ ውኃ መንጽሒ (የሚያነጻ) የሚያጠራ ነው፤ ሁሉን ያነጻልና፤ ጌታም መንጽሔ ሥጋ ወነፍስ ነውና እንዲህ አድርጎ ፈጥሮታል። አንድም የውኃ ግብሩ (ጠባዩ)፡- ብሩህነት፣ ርጥብነት፣ ቀዝቃዛነት ነው፤ ይህም የሥላሴን ሦስትነት አንድነት ያመለክታል፤ በመለኮት አንድ ሲሆን ሦስት ግብራት አሉትና ነው፡፡ (መጽሐፈ አክሲማሮስ) “ለተጠማ ከሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ” እንዳለ፡፡ (ራእይ ፳፩፥፮)
ይህ የሕይወት ውኃ የመንፈስ ቅዱስ ዘለዓለማዊ ጸጋ በልዩ ልዩ ቦታዎች የሚሰጥ መሆኑን በሕይወት ውኃ ተመስሏል። በዚህም ውኃ ሕይወት ላላቸው በሙሉ የሕይወት ምንጭና ሕይወት ሰጪ መሆኑን መናገር ይቻላል። “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” ያለውም ለዚህ ነው። (ዮሐ.፫፥፭) በዚህ አገላለጽ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊ ልደት እንደምን ወለደ ነገረን። (ዮሐንስ ወንጌል ትርጓሜ)
ቤተ ክርስቲያናችን ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ የነበረውን ሥርዓተ አምልኮ ስታከናውን የነበረች ከመሆኑ አንጻር፣ በበሉይ ኪዳን ውኃ ለቤተ መቅደስ አገልግሎትና ለእስራኤል ዘሥጋ ለመንጻት አገልግሎት ይውል ነበር።
“እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። ‘የመታጠቢያ ሰንና መቀመጫውን ከናስ ሥራ፤ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል እርሱን አድርገህ ውኃን ትጨምርበታለህ። አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡበታል።” (ዘጸ. ፴፥፲፯-፲፱) የረከሱት ንዋያትም በውኃ ያጠሩ ነበር። ከደዌም ይነጹበት ነበር፡፡ (ዘሌ.፲፩፥፴፫) “ንዕማንም በፈረሱና በሠረገላው መጣ፥ በኤልሳዕም ቤት ደጃፍ ውጭ ቆመ። ኤልሳዕም ሂድ፥ በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ታጠብ፤ ሥጋህም ይፈወሳል፥ አንተም ንጹሕ ትሆናለህ…… ወረደም፥ የእግዚአብሔርም ሰው እንደ ተናገረው በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ፤ ሥጋውም እንደ ገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ሆኖ ተመለሰ፥ ንጹሕም ሆነ” ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ (፪ኛ ነገ. ፭፥፩-፲፱) በአጠቃላይ በብሉይ ኪዳን ውኃ ለድኅነተ ሥጋና ለደዌ ፈውስ እንዲሁም ለንዋያተ ቅዱሳት መንጻት እንጂ ለድኅነተ ነፍስ አያገለግልም ነበር።
የውኃ አገልግሎት በአዲስ ኪዳን ከፍ ብሎ ለነፍስ ድኅነትና የዘለዓላማዊ ሕይወት ማግኛ ሆኗል። “የእግዚአብሔር ስጦታ፥ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ፤ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር፡፡” (ዮሐ.፬፥፱)
፩. የሕይወት ውኃ የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንበት ጸጋ መንፈስ ቅዱስ /ልጅነት/ ነው፤ «እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውኃ ኑ፡፡» (ኢሳ.፶፭፥፩) «ጥሩውን ውኃንም እረጭባችኋለሁ፤ እናንተም ትጠራላችሁ፤ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ» (ሕዝ፣ ፴፮፥፳፭)፣ «ለተጠማ ከሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጠዋለሁ» እንዲል። (ራእይ ፳፩፥፮)
፪. የሕይወት ውኃ በዕለተ ዐርብ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጎን የፈሰሰ ውኃ ነው፡፡ (ዮሐ.፲፱፥፴፬)
፫. የሕይወት ውኃ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ «ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል» (ኤር.፪፥፲፫)። «አቤቱ የእስራኤል ተስፋ ሆይ የሚተውህ ሁሉ ያፍራል፤ ከአንተም የሚለዩ የሕይወትን ውኃ ምንጭ እግዚአብሔርን ትተዋልና በምድር ላይ ይጻፋለ» እንዲል። (ዮሐንስ ወንጌል ትርጕም)
ከዚህ በመነሣት በቤተ ክርስቲያን በኃው የተለያዩ አገልግሎቶች ይፈጸማሉ። ለዚህም እንደ አብነት አድርገን ከምናከብራቸው በዓላት፦ በስንክሳር ሰኔ ስምንት በሚነበበውና ከእመቤታችን ከሠላሳ ሦስት በዓላት አንዱ የሆነውን ለሕሙማን ድኅነት ሊሆን ልጅዋ ውኃን ከዐለት ላይ ያፈለቀበት በዓል ነው። በዚህ ዕለት የእመቤታችን ማርያም የታወቀች በውኃ ምንጭ ዘንድ ያለች ቤተ ክርስቲያንዋ ቅዳሴ ነው። እርሱም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሷ ጋር በግብጽ አገር ተሰዶ ሲመለስ ያፈለቀው የተባረከ መታጠቢያ ነው። (ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ ፰) በዚህ መነሻነት ቤተ ክርስቲያናችን ለክርስቲያኖች በተባረከ ውኃ ለሥጋ ደዌ ፈውስና የመገልገያ ነገሮች ለመባረክ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ የተለመደውን በሐዲስ ኪዳንም ቀጥላ በየዓመቱ ታከብራለች።
ይህንንም ለመመልከት በቤተ ክርስቲያናችን ለድኅነት ሥጋና ነፍስ የምንጠቀምበት በውኃ የሚፈጸሙ ሥርዓቶችን በዝርዝር እንመለከታለን፦
*ማየ ገቦ*
የጥምቀት ውኃን ወደ ማየ ገቦነት የሚለወጥ (ምሥጢረ ጥምቀት ይባላል)
ማየ ገቦ “የጎን ውኃ” ማለት ሲሆን ምእመናን ከሥላሴ ልጅነትን የሚያገኙበት ውሉደ እግዚአብሔር የሚባሉበት ‹‹ማየ ገቦ›› ይባላል፡፡ ጌታ በዕለተ ዓርብ ተሰቅሎ ሳለ ለንጊኖስ የሚባል ሐራዊ ጎኑን በጦር በወጋው ጊዜ ከጎኑ ደምና ውኃ ወጥቷል፡፡ (ዮሐ.፲፱፥፴፬)
ይህም ውኃ (ማየ ገቦ) በጥምቀት ከእርሱ የምንወለድበት ሲሆን ደሙ ደግሞ ጽምዓ ነፍሳችንን የምናረካበት ነው፡፡ እናም ቤተ ክርስቲያን ጌታ ‹‹ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል›› ሲል በተናገረው አምላካዊ ቃል መሠረት ወንዶችን በአርባ፣ ሴቶችን በሰማንያ ቀን በዚህ ማየ ገቦ ታጠምቃለች፡፡ (ማር.፲፮፥፲፮) ሊቃውንትም ‹‹ጥምቀትስ ለወንዶችም ለሴቶችም ለትልቆችም ለትንሾችም የታዘዘ ነው፤ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን በወንጌል ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያያትም ስላለ” በማለት ያስተምራሉ፡፡ (ዮሐ.፫÷፭) ለደቀ መዛሙርቱም ሂዱና አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው ስላላቸው (ማቴ.፳፰÷፲፱)፡፡›› (ፍትሕ መን. አን. ፫፥፳) በእነዚህ ሥርዓት ተሠርቷል።
ማየ መቍረር
‹‹ማቍረሪያ፣ ማብረጃ፣ማቀዝቀዣ፣ የሰን ውኃ፣ የቅዳሴ ጠበል›› ማለት ነው፡፡ የሚያቀዘቅዝ ውኃ እንደ ማለት ሲሆን ሥጋውን ደሙን ለተቀበሉ ምእመናን የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ ምእመናን አስቀድሰው ሥጋውን ደሙን ከተቀበሉ በኋላ እህል ከመቅመሳቸው በፊት የሚሰጣቸው ነው፡፡ ‹‹አንዱስ እንኳን ከሠርሖተ ሕዝብ አስቀድሞ ሥጋውን ደሙን በሌላ ኅብስት አያድፈው፤ ማየ መቍረሩም ከአፉ ምንም ጠብ አይበል›› እንዲል፡፡ (ፍት. መን. አን. ፲፫፥፭፻፳፯)
ማየ ጸሎት(ጠበል)፣በጸሎት የተባረከ ማየ በረከት የበረከት ውኃ ማየ ፈውስ ማለትም ነው።
ጠበል በቁሙ ‹‹የጥምቀት ውኃ፣ የተጸለየበት ወይም በተአምራት የፈለቀ፣ ከደዌ የሚያድን፣የሚፈውስ›› ማለት ሲሆን ‹‹ጸበል ደግሞ ብናኝ፣ትቢያ፣አቧራ፣ደቃቅ አፈር›› ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በልማድ ‹‹ጸበል›› ይባላል፡፡ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት) በአጠቃላይ ጠበል የተጸለየበት፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያረፈበት ውኃ ማለት ነው፡፡ ጠበል በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ሕሙማን የሚፈወሱበት ተአምራት የሚደረግበት ቅዱስ ውኃ ነው:: ‹‹የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃው ላይ ይሰፍፍ ነበረ›› እንዲል፡፡ (ዘፍ. ፩፥፪) ኢዮብም እንዲሁ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ነጽቷል፡፡ (ኢዮ. ፵፪፥፲)
በኢየሩሳሌምም ሕሙማን ተጠምቀው የሚድኑባት መጠመቂያ ነበረች፡፡ ‹‹በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ መጠመቂያ ነበረች…..በዚያም ዕውሮችና አንካሶች ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ድውያን ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቁ ነበሩ፤ የእግዚአብሔር መልአክ..ውኃውን በሚያናውጠው ጊዜ ከውኃው መናወጥ በኋላ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበርና፡፡›› (ዮሐ.፭፥፩-፭) ‹‹እንዲህም አለው፤ ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ ትርጓሜውም የተላከ ማለት ነው፤ ሄዶም ታጠበና እያየ ተመለሰ፤ ኢየሱስ የሚባለው ሰው በምራቁ ጭቃ አድርጎ ዐይኖቼን ቀባኝና ሄደህ በሰሊሆም ውኃ ታጠብ አለኝ፤ ሄጄም ታጠብሁና አየሁ አላቸው፡፡›› (ዮሐ.፱÷፯፣፲፩፥፲፭)
የወንዝና የኩሬ ውኃ በሌለበት ቦታ ደግሞ ካህናት የጸለዩበት ውኃ እና ዘይት እንደ ሚፈውስ ተነግሮአል፡፡ (ያዕ.፥፲፬፣ ማቴ.፲፰፥፲፰) ነገር ግን ካህናት ያልጸለዩበት (ያልተባረከ)፣ ቤተ ክርስቲያን ያልታነጸበት፣ ታቦት፣መሥዋዕት፣ ዕጣን እነዚህን የመሰሉ ነገሮች የሌሉበት ከሆነ አጋንንት በምትሐት ሰውን ሊያስቱበት ይችላሉና ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም አሁን አሁን በአጋንንት አሠራር ተአምራት እያደረጉ ሕዝብ የሚያደናግሩ ብዙዎች ናቸውና፡፡ ነገር ግን ማስተዋል ያለብን ተአምራት ማድረግ ብቻ የጻድቅነት መለኪያ አለመሆኑን ነው፡፡ ተአምራት ያደረገው ሁሉ የበቃ አይደለምና፡፡ በለዓም ከእግዚአብሔር ሳይላክ ተአምራት ያደርግ ነበር፡፡ ይህም ማለት ረግሞ ያጠፋ፣ መርቆ ያከብር ነበር፡፡
‹‹እነሆ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ አለ፤ እነሆ የምድሩን ሁሉ ፊት ሸፈነ፤ በአቅራቢያችንም ተቀምጦአል፤ አሁንም ይህ ሕዝብ ከእኔ ይበልጣልና ልወጋቸውና ከምድሪቱ ላሳድዳቸው እችል እንደሆነ ና ርገምልኝ አንተ የመረቅኸው ምሩቅ የረገምኸውም ርጉም እንደሆነ አውቃለሁና፡፡›› (ዘኍ.፳፪፥፮) ይህንንም ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹ወቀዳሚት ኮነት ኃይለ ጸጋ ዘትትገበር በእደዊሆሙ እንዘ ኢይደልዎሙ በከመ ተገብረት በላዕለ በለዓም፦አስቀድሞ ግን በእጃቸው ዳሰው፣ በቃላቸው ተናግረው ተአምራት ያደርጉ ነበር፡፡›› በለዓም ሳይበቃ በእጁ ዳሶ በቃሉ ተናግሮ ያደርግ እንደ ነበር፡፡ እንደዚሁ ሁሉ እነዚህም በክፋት ሳሉ ሳይበቁ በቃላቸው ተአምራት ትደረግ ነበረች፤ በስሙ እምነው ይድኑ ዘንድ ስለ መጡ ሰዎች ሃይማኖት (የሚደረግ ተአምራት አለና)›› (ተግሣጽ ገጽ ፪፻፷፭)
የአይሁዳዊው ልጆች ደቂቀ አስቄዋም በክርስቶስ ስም ተአምራት ያደርጉ ነበር፡፡ ‹‹ከአይሁድም አስማት እያደረጉ የሚዞሩ ሰዎች ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ ጳውሎስ በሚያስተምርበት በኢየሱስ ስም እናምላችኋለን እያሉ የጌታችን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ነበር እኒህ እንዲህ ያደርጉ የነበሩትም የካህናቱ አለቃ የአይሁዳዊው የአስቂዋ ልጆች ናቸው፤ እነርሱም ሰባት ነበሩ ያም ክፉ መንፈስ በኢየሱስ አምናለሁ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ እንግዲህ እናንተ እነማን ናችሁ? ብሎ መለሰላቸው ያም ክፉ መንፈስ የያዘው ሰው ተነሣባቸው አየለባቸውም፤ አሸነፋቸውም አቍስሎም ከዚያ ቤት አስወጥቶ አባረራቸው፡፡›› (ሐዋ.፲፱፥፲፫-፲፮)
ይህንንም ተአምራት የሚያደርጉ ሰዎች የበቁ አለመሆናቸው የሚታወቀው በጌታ የፍርድ ዙፋን ፊት በቀረቡ ጊዜ የሚመለስላቸው መልስ ነው፡፡ ‹‹በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ ከሚያደርግ በቀር አቤቱ! አቤቱ! የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፤ በዚያች ቀን ብዙዎች አቤቱ! አቤቱ! በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል ያን ጊዜ ከቶ አላውቃችሁም ዐመፅን የምታደርጉ ሁላችሁ ከእኔ ራቁ እላቸዋለሁ፡፡›› (ማቴ. ፯፥፳፩-፳፫) ዮሐንስ አፈወርቅም ‹‹ወገቢረ ተአምራት ወመንክራት ኢይክል ያድኅን እምሥቃየ ኵነኔ፦ተአምራት ማድረግም ከገሃነም አያድንም›› ብሏል፡፡ (ተግ.ገጽ ፪፻፷፭)
ስለዚህም ዛሬ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እንደሚታየው ዮሐንስ መጥምቅን በተግባር ሳይሆን በአፍአዊ ግብር ለመምሰል የሚታትሩ ራሳቸውን ናዝራውያን ያሰኙ ስመ እኩይ ግብረ ስንኩል የሆኑ አንዳንድ ሥራ ፈት ሰዎች በሌሎች የመናፍቃን አዳራሽ የምናየውን ምትሐታዊ ድርጊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይህን ድርጊት እንደ ምትደግፍ አስመስለው እያደናገሩ እና እያጭበረበሩ እንደ ገንዘብ ምንጭነት እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ ይህም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
አሁን አሁን በየጠበል ቦታው “በሐሰተኛ አጥማቂዎች ስም በአባ እግሌ ካልሆነ አልወጣም፤” የሚል ሰይጣን እንዳለ ይሰማል፡፡ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ በጌታችን ስም ውጣ ሲባል፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስምን ስንጠራበት የማይወጣ ሰይጣን የቅዱሳን ስም ሲጠራ “እወጣለው” ይላል፤ ይህ የሰይጣን ማታለል ነው። የባሕርይ አምላክ በሆነው በጌታችን ስም ያልወጣ በማን ስም ሊወጣ ነው? ይህ ታዲያ የሰይጣን የማታለል ሥራ ስለሆነ ጥንቃቄ ቢደረግ ምእመኑም በማስተውል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ቢሆን መልካም ነው።
ታዲያ ጠበሎች ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠራት ሲኖርባቸው ለምን የማርያም ጠበል፣ የሚካኤል ጠበል፣ የጊዮርጊስ ጠበል ይባላል? ተብሎ ለሚነሣ ጥያቄ ይኸውም በጠበሉ ቅዱሳን እንዲታሰቡበት ነው፡፡
“እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና።በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ።” (ኢሳ.፶፮፥፬-፭)
እንዲሁም “የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው” (ምሳ.፲፥፯) በሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ መሠረት በጠበሉ ቅዱሳኑ መጠራታቸው መታሰቢያቸው እንዲሆን ነው፡፡ ጠበሉን የፈጠረው መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን እና በጠበሉም አድሮ ሕሙማንን የሚፈውሰው እና ተአምራትን የሚያደርገው የእግዚአብሔር ኃይል መሆኑን በደንብ እናውቃለን፡፡
እምነት (ጸበል)
ጸበል ብናኝ፣ ትቢያ፣ ዐቧራ፣ ደቃቅ፣ አፈር
“አፈር፤ መሬት፣ትቢያ” ማለት ነው፡፡ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት) ነገር ግን እምነት የሚለው ሃይማኖት፣ማመን፣መታመን፣ማሳመን ማለት ስለሆነ በግብሩ ወይም በልማድ የተሰጠ ስም ነው፡፡ ትክክለኛ ስሙ ‹‹ጸበል›› የሚለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የቅዱሳን ዐፅም ያረፈበት ልዩ ልዩ ተአምራት በተደረገበት ቦታ ላይ የሚገኝ ሲሆን በእምነት ላደረገው ሁሉ የሚፈውስ ነው፡፡ ‹‹ሁለት የበቅሎ ጭነት አፈር ለአገልጋይህ ይስጡት፤ እግዚአብሔርም የእኔን የአገልጋይህን ኃጢአት በዚህ ነገር ብቻ ይቅር ይበለኝ፡፡›› (፪ኛ ነገ. ፭፥፲፯) ‹‹ይህንም ብሎ በምድር ላይ ምራቁን እንትፍ አለ፤ በምራቁም ጭቃ አድርጎ የዕዉሩን ዐይኖች ቀባው፡፡›› (ዮሐ.፱፥፮-፲፩)
‹‹ነገሥታትም አሳዳጊዎች አባቶችሽ ይሆናሉ፤ እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ ግንባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፤ እኔንም በመተማመን የሚጠባበቁ አያፍሩም›› (ኢሳ. ፵፱፥፳፫) ክርስቲያኖችም ከጌታ መቃብር ላይ እና እመቤታችን ተቀብራበት ከነበረው መቃብር ላይ እምነቱን (ጸበሉን) እየተቀቡ ይድኑ እንደነበር ‹‹እነሆ እስከ ዛሬ ድረስ ከመቃብሩ ላይ ተአምራት ይደረጋልና ክርስቲያኖች ከእምነቱ(ከትቢያው) ተቀብተው ከበሽታቸው ይፈወሳሉና›› ይላል፡፡ (ርቱ.ሃይ.ገጽ ፫፻፳)
በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በቤት ውስጥ አባቶች ካህናት ውኃ ላይ በመጸለይ በሥጋችን ከደዌ ሕማም (በሥጋ በሽታ) ከሚመጡ ነገሮች እንድናለን፤ ከጭንቀት፣ ከአጋንንት እስራት ሁሉ ነጻ እንሆናለን፡፡ እንዲሁም በአርባና በሰማንያ ቀን ደግሞ ጌታችን እንዳስተማረው ካህናት በተለየ ጸሎት ከውኃ እንወለዳለን።
በቅዱሳን ጠበል ተጠምቀን፣ ውኃን ጠጥተን፣ ተቀባብተን፣ ተሻሽተን እንድናለን፤ በእግዚአብሔር ስም ካለብን ችግር ነጻ እንሆናለን። ለዚህ ደግሞ ከሐሰተኞች አጥማቂዎች፣ በየጠበል ቦታው ከማጭበርበሩ ሰዎች፣ ሥርዓት ከጎደለው የሥርዓተ ጥምቀት፣ የመንፈስ ቅዱስን ሥራ የገንዘብና ምንጭ አድርገው ከቤተ ክርስቲያን ፈቃድና ዕውቅና ውጪ ከሚንቀሳቀሱ ሕገ ወጥ ሥርዓት መጠበቅ አስፈላጊ ነው። የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና እና ትውፊት በጠበቀ ሥርዓት ማገልገልና መገልገል ይገባል።
ስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!