በሕይወት ሳልለው

ብፁዕ አቡነ ገሪማ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ ሚያዝያ ፳፯፤ ፳፻፲፩ ዓ.ም ከቀኑ አምስት ሰዓት ከሰላሣ ላይ ባልቻ ሆስፒታል ውስጥ ያረፉት ብፁዕ አቡነ ገሪማ፤ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት በተደረገ ትብብር ህክምና ቢደረግላቸውም በሕይወት መቆየት አለመቻላቸው ተገልጿል፡፡ ከፍተኛ የዓይን ሕመም ስለነበረባቸው አሜሪካን ድረስ በመሔድ መታከማቸውን የገለጹት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፤ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ አገልግሎታቸውን ማቋረጥ የማይፈልጉ አባት ነበሩ ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

«ታላቅ አባት ነበሩ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ትልቅ ጥላ አጥልቶብናል! እንደነዚህ አይነት አባት መተካት የማይቻልበት ዘመን ላይ ነው የደረስነው፤ አስተዋይ፤ ትዕግሥተኛና ሁሉንም ችለው ሥራቸውን ያከናውኑ ነበር፤» ሲሉም ኀዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

የብፁዕነታቸው  የቀብር ሥነ ሥራዓት ቅዱስ ሲኖዶሱ ሚያዝያ ፴፤፳፻፲፩ ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከቀኑ ፭ ሰዓት ላይ እንደሚፈጸም ወስኗል፡፡

ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ ዜማ፤ ቅኔና አቋቋምን ጨምሮ የመንፈሳዊ ትምህርት ከመማራቸው ባሻገር ዘመናዊ ትምህርታቸውን በሐረር የራስ መኰንን አዳሪ ትምህርት ቤት እና በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡በታሪክ ትምህርት የማስተርስ ዲግሪና በነገረ መለኮት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሰርተዋል፡፡

በአገልግሎት ዘመናቸውም የተለያዩ ኀላፊነት ያለባቸውን ሥራዎች ለማከናወን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር፤ የቅድስት ሥላሴ እና የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጆች ዲን በመሆን አገልግለዋል፡፡

በተጨማሪም በመንበረ ፓትርያርኩ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ቢሮ ዋና ጸሓፊ፤ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እንዲሁም የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊም ነበሩ፡፡