የቤተ ክርስቲያን አስፈላጊነት

‹‹…አቤቱ የሥርዓትህን መንገድ አስተምረኝ፤ ሁልጊዜም እፈልገዋለው….›› (መዝ.፻፲፰፥፴፫)

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ታኅሣሥ ፲፫ ቀን ፳፻፲፬ .

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለከበረው ጤንነታችሁ እንደምን አላችሁ? ነቢየ እግዚአብሔር ንገሥ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹…ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ፤ ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ….›› (መዝ.፳፪፥፲) በማለት እንደገለጸው ከእናታችን ሆድ ጀምሮ የጠበቀን አሁንም በቸርነቱ የሚጠብቀን እግዚአብሔር ይመስገን፤ አሜን!

እንዴት ሰነበታችሁ? ትምህርትስ እንዴት ነው? የመጀመሪያው የሩብ ዓመት የትምህርት ውጤታችሁ እንዴት ነው? መምህራን የሚሰጧችሁን ትምህርት በአግባቡ እየተከታተላችሁ ዕውቀታችሁን እያሳደጋችሁ ነውን? እንደዚያ ከሆነ መልካም በመሆኑ በርቱ! ታላላቆችን ማክበር እንዳትዘነጉ! መታዘዝ ታላቅ ያደርጋል!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ባለፈው በዚህ ዐቢይ ርዕስ ሥር ሥርዓተ ቤተ ክረስቲያን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ትርጉሙን ማየታችን ይታወሳል፤ ለዛሬ ደግሞ በሥርዓት መመራት ለምን ያስፈልጋል? የሚለውንና ሥርዓት አክብረው በሥርዓት ኑረው ክብርን ካገኙ አባቶቻችን አንዱን ታሪክ እንመለከታለን፤

ልጆች! በሥርዓት ስንመራ የምናገለግለው አገልግሎት የተሳካ፣ የሠመረ ይሆናል፣ ሥርዓት በማክበር የእኛም ሕይወታችን ይከብራል፤ ክፉ ነገርም አይገጥመንም፤ ስለዚህ በቤተ ክርስቲያንም ስንመላለስ በሥርዓት፣ በአግባቡ መሆን አለበት፡፡

መልካም ልጆች! ለአብነት የሚሆነን በቤተ መቅደስ ሲያገለግል በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በትሕትና፣ በታዛዥነት ያገለግል ስለነበረው ነቢዩ ሳሙኤል ታሪክ እንመልከት፤ ነቢዩ ሳሙኤል እናቱ ሐና አባቱ ደግሞ ሕልቃና ይባላሉ፤ እናቱ ለእግዚአብሔር ስዕለትን ተስላ ስለወለደችው ባደገ ጊዜ ወደ ቤተ መቅደስ ወስዳ ሰጠችው፤ ልጆች! ነቢዩ ሳሙኤል ቤተ መቅደስ ሲመጣ በወቅቱ በቤተ መቅደስ ካህኑ ዔሊ የሚባል ታላቅ አባት እና አፍኒንና ፊንሐስ የተባሉ ልጆቹ ነበሩ፡፡

ይገርማችኋል! የካህኑ ዔሊ ልጆች በቤተ መቅደሱ ሲያገለግሉ ሥርዓት እያበላሹ የማይገባ ሥራን ሲሠሩ ሕፃኑ ነቢዩ ሳሙኤል ግን በሥርዓት፣ በታዛዥነት ያገለግል ነበር፤ በጸሎት ይተጋል፤ ትእዛዝን ያከብራል፤ ከእነርሱ ጋር በመጥፎ ሥራቸው አይተባበርም ነበር፡፡ (፩ሳሙ.፫፥፩)

ውድ የእግዚአብሔር! ልጆች ነቢዩ ሕፃን ሳሙኤል ከአፍኒንና ፊንሐስ ክፉ ሥራ ጋር ሳይተባበር በመገኘቱና በመጽናቱ የሥርዓት ባለቤት አከበረው፤ ከፍ ከፍም አደረገው፤ በቤተ መቅደስ ተኝቶ ሳለ እግዚአብሔር ሌሊት በራእይ (በሕልም) ተገልጦ አናገረው፡፡ ሁለቱ ልጆች ሥርዓት በመተላለፋቸው እግዚአብሔር አዘነባቸው፤ እነርሱም ተቀጡ፤ እግዚአብሔር        ‹‹ …ያከበሩኝን አከብራለሁና፣ የናቁኝም ይናቃሉና ..›› በማለት እንደተናገረው ሁለቱ ልጆች ሥርዓትን በማፍለሳቸው፣ ባለማክበራቸው መከራ ችግር ገጠማቸው፤ ነቢዩ ሳሙኤል ግን እግዚአብሔር አከበረው፤ ነቢይ፣ መስፍን አድርጎ ሾመው፤ ተመርጦ ሕዝቡን ያስተምር ይመክር፣ ትንቢትን ይናገር ዘንድ ተመረጠ፡፡ሥርዓትን በማክበሩና በሥርዓት በመመላለሱ በእግዚአብሔር ዘንድ ክብርና ሞገስን ተሰጠው፡፡ (፩ሳሙ.፪፥፴)

ልጆች! ነቢዩ ሳሙኤል በዚህ መልካም ምግባሩ፣ ሥርዓት በማክበሩ የመጀመሪያውን የእስራኤልን ንጉሥ ሳኦልን እንዲሁም ንጉሥ ዳዊትን ቀብቶ ያነገሠ ታላቅ አባት ለመሆን በቃ፡፡

ልጆች! በሕይወታችን በየትኛውም ሥፍራ አጠገባችን ያሉ ባልንጀሮቻችንን አጠፉ በማለት እኛም እንደ እነርሱ ለማጥፋት መነሣት የለብንም፤ ሰዎች አላዩንም በማለት ብናጠፋ በሁሉ ቦታ ያለ ሁሉንም የሚያይ እግዚአብሔር ያየናልና በአግባቡ ልንመላለስ ይገባል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ ሥርዓትን ማክበር ምን ያህል ክብርን እንደሚያሰጥ በነቢዩ ሳሙኤል ታሪክ ተምረናል፡፡ ስለዚህ የምንሠራው ሥራ ሁሉ እንዲቀና አገልግሎታችንም እንዲሰምር እንዲሁም እንድንባረክ እግዚአብሔር ለታላቅ አገልግሎት እንዲመርጠን በሥነ መግባር የታነጽን ፣ሥርዓትን የምናከብር ልጆች መሆን አለብን፡፡

ለዛሬ ይህን ከተመለከትን በቀጣይ ደግሞ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስንመጣና ወደ ቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ እንዴት እንደሆነ ውስጥም ከገባን በኋላ እንዴት ባለ ሥርዓት መመላለስ እንዳለብን እንመለከታለን ለዛሬ ይብቃን፤ ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!