የበረዶ ናዳ በገዳመ ናዳ

ፈለገ ብርሃን ናዳ ቅድስት ማርያም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ፈለገ ብርሃን ናዳ ቅድስት ማርያም ገዳም በምዕራብ ጐጃም ሀገረ ስብከት ሜጫ ወረዳ ቤተ ክህነት በጉታ ቀበሌ ልዩ ስሙ ናዳ በሚባል ቦታ ይገኛል፡፡ ገዳሙ በዐሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተመሠረተ ሲኾን፣ ታቦተ ሕጉም ከጣና ቂርቆስ ገዳም እንደ መጣ ይነገራል፡፡ ለብዙ ዓመታት ‹እንቍርቍሪት ጽዮን› እየተባለ ሲጠራ የቆየው ገዳሙ፣ ከዓመታት በኋላ ‹ናዳ ማርያም› ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ናዳ የተባለበት ምክንያትም የሚከተለው ታሪክ ነው፤ በአካባቢው ዋናው ገዳም የሚባል ሌላ ጥንታዊ ገዳም ነበረ፡፡ በዚህ ገዳምም አባ ናዳ የሚባሉ አባት ይጸልዩበት ነበር፡፡ በዙርያውም በርካታ መነኮሳት ነበሩ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አባ ናዳ በመሰላል ወጥተው የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ጣርያ ሲከድኑ መሰላሉ አንሸራቷቸው ወደቁ፡፡ በዚህ ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጻ በደኅና ካነሣቻቸው በኋላ ‹‹ወዳጄ አባ ናዳ ሆይ! ለዘለዓለም ስምህ በዚህ ቦታ ይጠራ›› በማለት ቃል ኪዳን ሰጠቻቸው፡፡ አባ ናዳም ገዳሙን አሁን ባለበት አኳኋን እንዲጸና አደረጉ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ‹እንቍርቍሪት› የሚለው ስያሜ ተለውጦ ‹ናዳ ማርያም› ወይም ‹ናዳ ጽዮን› ተብሎ መጠራት ጀመረ፡፡

በአዲስ መልክ እየተገነባ የሚገኘው የክብረ ደናግል ናዳ ቅዱስ ላልይበላ ሕንጻ

ፈለገ ብርሃን ናዳ ማርያም ገዳም በየጊዜው የመጥፋት ፈተና ቢያጋጥመውም በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደ ገና እየተመለሰ እስካሁን ድረስ ክብሩ እንደ ተጠበቀ፤ ወሰኑ እንደ ተከበረ፤ ልማቱም እንደ ቀጠለ ነው፡፡ ገዳሙ የአብነት ትምህርት ማእከል በመኾኑና ዙርያው በምንጭ በመከበቡ የተነሣ ከ፲፱፻፹፮ ዓ.ም ጀምሮ በጊዜው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በነበሩት ብፁዕ አቡነ በርናባስ ፈቃድ ‹ፈለገ ብርሃን› ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ገዳሙ በዚህ መልኩ እየሰፋ መጥቶ በአሁኑ ሰዓት አገልግሎቱም ጉባኤ ቤቱም በአግባቡ እየተከናወነ ነው፡፡ ከፈለገ ብርሃን ናዳ ማርያም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በተጨማሪ የክብረ ደናግል ናዳ ቅዱስ ላልይበላ እና የጋፈራ ደብር ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ሕንጻ አብያተ ክርስቲያናት ለመነኮሳቱ እና ለአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓትም የክብረ ደናግል ቅዱስ ላሊበላ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በዘመናዊ ጥበብ በአዲስ መልክ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

(ምንጭ፡- ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ፤ ገዳሙ ያሳተመው ብሮሸር)

ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ

ምንኵስናን ከሊቅነት፣ አባትነትን ከሥራ ጋር አስተባብረው በያዙት በሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ አማካይነት ከ፲፱፻፸፱ ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ በገዳሙ የትርጓሜ መጻሕፍት እና የቅኔ ትምህርት በመሰጠት ላይ ነው፡፡ ከሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ይባቤ ጉባኤ ቤት ተምረው በልዩ ልዩ የአገልግሎት ዘርፍ ተሰማርተው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ ካህናትና መምህራንም እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ የገዳሙ ዋና አስተዳዳሪ፣ የትርጓሜ መጻሕፍትና የቅኔ መምህሩ ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ይባቤ እንደ ገለጹልን ገዳሙ ከሚታወቅባቸውና ከሚደነቅባቸው ተግባራት አንደኛው የልማት ሥራ ሲኾን፣ ልማቱ በስፋት የተጀመረውም በ፲፱፻፹ ዓ.ም ነው፡፡ በገዳሙ አካባቢ የሚገኘውን በጎርፍ የተሸረሸረ ሸለቆ በመከባከብ የተጀመረው የልማት ሥራ ውጤታማ ኾኖ ገዳሙን በፌዴራል ሁለተኛ፤ በክልል ደግሞ አንደኛ ደረጃ እንዲያገኝና የክብር ሜዳልያ እንዲሸለም አድርጎታል፡፡

የገዳሙ አትክልት በከፊል

የገዳሙ መነኮሳት ከመንፈሳዊው አገልግሎታቸው ጎን ለጎን በጕልበታቸው ያለሙት የአትክልት እና የደን ይዞታ የተመልካች ቀልብን ይስባል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በዘንድሮው ዓመት (፳፻፱ ዓ.ም) በወርኃ ሰኔ በአካባቢው አንድ አዲስ ነገር ተከሠተ፡፡ ነገሩም እንዲህ ነው፤

ዘመነ ጸደይ (በልግ) ተፈጽሞ ዘመነ ክረምት ሊገባ ቀናት ብቻ ቀርተዋል፡፡ ክረምቱ በይፋ ባይገባም በገዳሙ ማኅበረ መነኮሳት እና በአካባቢው አርሶ አደሮች የክረምቱ ተግባር መከናወን ከጀመረ ቆየት ብሏል፡፡ ‹‹ሰኔ እና ሰኞ›› እንደሚባለው ወርኃ ሰኔ ልዩ የሥራ ወቅት ናትና ማኅበረ መነኮሳቱ እና የአካባቢው አርሶ አደሮች ለሥራ በመሯሯጥ ላይ ናቸው፡፡ ከላይ በሚወርደው ዝናም የራሰው፤ ከምድር በእርሻ ብዛት የለመለመው የፈለገ ብርሃን ናዳ ማርያም ገዳም እና የአካባቢው መሬትም የተዘራበትን አብቅሎ አርሶ አደሮቹንና መነኮሳቱን አስደስቷል፡፡ በማጭድ ከሚታጨዱ ሰብሎች መካከል በቆሎን የመሰሉ አዝርዕት እየፋፉ ናቸው፤ በእጅ ከሚለቀሙት መካከል ደግሞ በተለይ ገዳሙን የልማት ማእከል ያደረጉት፤ በልዩ ልዩ ጊዜ ለሽልማት ያበቁት እና ስሙ ከፍ ከፍ እንዲል፣ በመንግሥት ዘንድም ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ያስቻሉት፤ ለበርካታ ዓመታት የተለፋባቸው የአቦካዶ፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ ብርቱካን፣ ፓፓዬ፣ ትርንጎ፣ ሎሚ እና የመሳሰሉ ጣፋጭ ተክሎች ፍሬያቸው ተንዠርግጎ አላፊ አግዳሚውን ያስጎመዣል፡፡ መነኮሳቱም የድካማቸውን ዋጋ በፍሬ አይተዋልና እየተደሰቱ ፍሬውን ለቅመው አንድም ለምግብ፣ አንድም ለሽያጭ ለማቅረብ ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

ማኅበረ መነኮሳቱ በሥራ ላይ

በ፳፻፱ ዓ.ም፣ ወርኃ ሰኔ በገባ በሃያ ሁለተኛው ቀን ከሰዓት በኋላ እንዲህ ኾነ፤ የገዳሙ መነኮሳት እና የአካባቢው አርሶ አደር ከፊሉ በአረም፣ ከፊሉም እንስሳትን በመጠበቅ ላይ ናቸው፡፡ ወቅቱ የዘመነ ክረምት ዋይዜማ ነውና ሰማይ በመባርቅቱ ድምፅ አጅቦ ዝናም ስጦታውን ወደ ምድር ሊልክ ተቻኩሏል፡፡ የሰማይ መልእክተኛ ደመናም ከውቅያኖሶች የቀዳውን ዝናም ተሸክሞ ወደ ምድር ሊያደርስ ተዘጋጅቷል፡፡ የዝናም መጓጓዣ ነፋስም ዝናሙን በመግፋት ደመናን እየተራዳው ነው፡፡ ምድር የሚወርደውን ዝናም ትጠጣ ዘንድ ሳስታ አፏን ከፍታ በመጠበቅ ላይ ናት፡፡ አዝርዕቱም ተዘርተው ያልበቀሉት በፍጥነት ለመብቀል፤ የበቀሉት ደግሞ ፍሬ ለመስጠት በአጠቃላይ በልምላሜ ለመረስረስ ወደ ላይ አሰፍስፈው ዝናሙን ይጠባበቃሉ፡፡ የመብረቁ ድምፅ፣ ብልጭታው፣ ጉርምርምታው እና የደመናው ጥቁረት ከወትሮው ጊዜ የተለየ ነው፡፡

ጥቁር ደመና በናዳ ሰማይ

ከቆይታ በኋላ በአንዲት ቅጽበት ማንም ያልጠበቀው ልዩ አጋጣሚ ተከሠተ፡፡ ለትምህርት ይኹን ለተግሣፅ፣ ለመዓትም ይኹን ለመቅሠፍት ብቻ ከእግዚአብሔር በቀር እኛ በማናውቀው ምክንያት በቀበሌው እና በገዳሙ ዙርያ ዝናምና ማዕበል የተቀላቀለበት ከባድ የበረዶ ናዳ ወረደ፡፡ በበረዶውም ከታላላቆቹ ጀምሮ እስከ ታናናሾቹ ድረስ ዕፀዋቱ በእሳት እንደ ተቃጠሉ ኩምሽሽ፣ እርር አሉ፡፡ ፍሬ ያፈሩ ተክሎችም ረገፉ፡፡ ገና ያልበቀሉትም በማዕበል ተወሰዱ፡፡ በፈለገ ብርሃን ናዳ ማርያም መነኮሳት ክንድ የተተከሉ የአቦካዶ፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ ብርቱካን፣ ፓፓዬ፣ ትርንጎ፣ ሎሚ እና የመሳሰሉ ጣፋጭ ተክሎች ፍሬያቸው ሙሉ በሙሉ ረገፈ፡፡ ያፈሉት ችግኝ ተጨፈጨፈ፡፡ የገበሬው፣ የመነኮሳቱ እና የእንስሳቱ መኖርያ ቤቶችም በበረዶ ፈራረሱ፡፡ የጠበል መጠመቂያ ቦታዎች ተናወጡ፡፡ የገዳሙ ንቦችም ከቀፎዎቻቸው ተሰደዱ፡፡ በዚህ የተነሣም በናዳ ማርያም ገዳም እና በአካባቢው ጸጥታ ነገሠ፡፡ ፍርኃትም ሰፈነ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደ ነገሩን የበረዶ ናዳው ሰኔ ሃያ ሦስት ቀንም ቀጥሎ ነበር፡፡ ጥፋቱ እንደ ገና ተደገመ፡፡ በአጠቃላይ ከሰባ ሄክታር በላይ የሚገመት ሰብል በበረዶው ናዳ ወደመ፡፡

ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ በበረዶ የተጎዳውን አትክልት ሲያስጐበኙ

ከጉዳቱ በኋላ የገዳሙ ዋና አስተዳዳሪ ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ ደቀ መዛሙርታቸውን እና ማኅበረ መነኮሳቱን ይዘው ጸሎተ ምሕላ ያዙ፡፡ የደረሰው ጥፋት እንዳይደገም፤ የወደመው ሰብልም እንዲመለስ፤ መነኮሳቱ፣ የአብነት ተማሪዎች እና ምእመናኑ ተስፋ ቈርጠው እንዳይበተኑ እግዚአብሔርን በጸሎት ይማጸኑት ጀመር፡፡ ዋና አስተዳዳሪው የጠፋውን ሰብል እና በአካባቢው የደረሰውን ጉዳት ላለማየት ከበዓታቸው አልወጣም ብለው ነበር፡፡ ከዕለታት በኋላ ግን የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ከራሱ ይልቅ የገዳሙን ጉዳይ አስቀድሞ በጉልበት፣ በእርሻ ሥራ እና ዘር በድጋሜ በመዝራት መነኮሳቱን ለማገዝ መምጣቱን ሲሰሙ ምእመናኑን ለማበረታታት ከበዓታቸው ወጡ፡፡ እኛም አባን ያገኘናቸው በዚህ ወቅት ነበር፡፡ ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ይባቤ ያዩት ነገር አዲስ ኾኖባቸዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ገዳም ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ እንደዚህ ዓይነት መዓት ደርሶ አያውቅም›› ይላሉ ሊቀ ብርሃናት የደረሰውን ጉዳት ከፍተኛነት ሲገልጹ፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ ከየአቅጣጫው ስልክ ሲደውልላቸውም ‹‹ደኅና ነን፤ አልተጎዳንም›› ይላሉ፡፡ ይህ ዅሉ ጉዳት ደርሶ እንዴት ለሰዎቹ ‹‹ደኅና ነን›› ይላሉ ብለን ስንጠይቃቸው ሊቀ ብርሃናት የሰጡን ምላሽ ‹‹እናትህ ሞተች ተብሎ አይነገርም›› የሚል ነበር፡፡ በእርግጥ እርሳቸው እንደ ነገሩን በሰው እና በእንስሳት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩ ማኅበረ መነኮሳቱን አስደስቷቸዋል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን የደከሙበት ሰብል እና አትክልት ከጥቅም ውጪ ኾኗል፡፡

በበረዶው ናዳ የረገፈው ፍራፍሬ በከፊል

የገዳሙ ደን እና ፍራፍሬ በበረዶ ናዳ ቢወድምም ዋና አስተዳዳሪው እና ማኅበረ መነኮሳቱ ብሩህ ፊታቸው አልቀዘቀዘም፡፡ ጉባኤ ቤቱም አልተፈታም፡፡ ገዳማውያኑ በተለመደው መንፈሳዊ ቋንቋ ‹‹እግዚአብሔር ይመስገን! ደኅና ነን … በአትክልት ላይ እንጂ በሰውና በእንስሳት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም … ዅሉም ነገር ለበጎ ነው … ከዚህ የባሰ አያምጣ …›› እያሉ እነርሱን ለመጠየቅና ጉዳን ለማየት የሚመጡ ምእመናንን ያረጋጋሉ፡፡ ገዳማውያን እንዲህ ናቸው፤ ተበድለው እንዳልተበደሉ፤ ተጎድተው እንዳልተጎዱ፤ ተቸግረው እንዳልተቸገሩ በማመን በኾነው ነገር ዅሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፡፡ በዚህ ዓመት በፈለገ ብርሃን ናዳ ማርያም ገዳም እና በአካባቢው በወርኃ ሰኔ የደረሰው ጉዳት እግዚአብሔርን ወደማማረር የሚገፋፋ ከባድ ፈተና ቢኾንም የገዳሙ አባቶች እና እናቶች ግን እግዚአብሔርን ማመስገናቸውን ለቅጽበት አላቋረጡም ነበር፡፡ በስበብ አስባቡ እግዚአብሔርን ና ውረድ የምንል ምእመናን ከእነርሱ ትምህርት ልንወስድ ይገባል፡፡

ከበረዶው ናዳ በኋላ የአካባቢው ምእመናን የገዳሙን መነኮሳት በጕልበት ሥራ ሲደግፉ

የገዳሙ መነኮሳትና የአብነት ተማሪዎች የወደፊት ኑሯቸው አሳሳቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን›› እያሉ እየጸለዩ ለምግብ እና ለአካባቢ ጥበቃ ይጠቅም ዘንድ በጉልበታቸው ወጥተው ወርደው ያበቀሉት ሰብል፣ ያለሙት አትክልት፣ ያፈሉት ችግኝ አሁን የለምና፡፡ የያዙት አማራጭ የተጎዳውን ሰብል እየገለበጡ እንደ ገና ዘር መዝራት ነው፡፡ ይህ መፍትሔ ግን በበቆሎ ፋንታ ዳጉሳንና የመሳሰሉ አዝርዕትን ለመተካት እንጂ ሙዙን፣ አቦካዶውን፣ ፓፓዬውን፣ ማንጎውን፣ ወዘተ የመሳሰሉ አትክልቶችን ለመተካት አያስችልም፡፡ እነዚህን ተክሎች ወደ ነበሩበት ለመመለስ የዓመታት ጥረትን ይጠይቃልና፡፡ ስለኾነም መላው ሕዝበ ክርስቲያን በገዳሙ እና በአካባቢው የደረሰውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት በሚቻለን አቅም ዅሉ አስቸኳይ ርዳታ ልናደርግላቸው ያስፈልጋል፡፡

የ አብነት ተማሪዎች በከፊል

በእርግጥ ማኅበረ ቅዱሳን ከገዳሙ ድረስ ልዑካንን በመላክ ለመነኮሳቱ የዘር መግዣ ይኾናቸው ዘንድ ለጊዜው የሃያ ሺሕ ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል በደረሰን መረጃ ማኅበሩ ካሁን በፊት ለገዳሙ ካበረከተው ትራክተር (የእርሻና የዕቃ ማጓጓዣ መሣርያ) በተጨማሪ ለወደፊትም በቋሚነት ገዳሙን ለመደገፍ አቅዷል፡፡ በቦታው ተገኝተን ዋና አስተዳዳሪውን ባነጋገርንበት ወቅት ላደረገው የገንዘብ ድጋፍ ማኅበረ ቅዱሳንን፤ በጉልበት ሥራ በመራዳታቸው ደግሞ የአካባቢውን ሕዝበ ክርስቲያን አመስግነዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ለገዳሙ ያበረከተው የእርሻና የዕቃ ማጓጓዣ መሣርያ

ኾኖም ግን ይህ ድጋፍ በቂ አይደለምና ሌሎች በጎ አድራጊ ምእመናንም ቀለብ በመስጠት፣ ዘር በመግዛት፣ ልብስ በመለገስ እና ከፍ ሲል ደግሞ መኖርያ ቤት በማደስ በአጠቃላይ በሚቻላቸው ዅሉ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ዋና አስተዳዳሪው ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ በገዳሙ ስም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ዝግጅት ክፍላችንም የገዳሙን መነኮሳት ከስደት፣ ጉባኤ ቤቱንም ከመዘጋት ለመታደግ፤ እንደዚሁም የልማት ቦታውን ወደ ጥንት ይዘቱ ለመመለስ ይቻል ዘንድ በተቻላችሁ አቅም ዅሉ ድጋፍ በማድረግ ከበረከቱ እንድትሳተፉ ይኹን ሲል መንፈሳዊ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡ በመጨረሻም የአባቶቻችን አምላክ ገዳሞቻችንን ከድንገተኛ አደጋ እና ከጥፋት፤ መነኮሳቱንና የአብነት ተማሪዎችንም ከስደት ይጠብቅልን እያልን ጽሑፋችንን አጠቃለልን፡፡

ማሳሰቢያ

ገዳሙን በገንዘብ ለመደገፍ የምትፈልጉ ምእመናን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መርዓዊ ቅርንጫፍ ሒሳብ ቍጥር፡- 10000 6261 1786 ገቢ ማድረግ የምትችሉ መኾኑን የገዳሙ ጽ/ቤት ያሳስባል፡፡ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘትም በስልክ ቍጥር፡- 09 18 70 81 36 በመደወል የገዳሙን ዋና አስተዳዳሪ ማነጋገር ይቻላል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡