sewa sewe brhan 3

የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀመዛሙርትን አስመረቀ

 ሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

sewa sewe brhan 3በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመደበኛና በማታ መርሐ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ 212 ደቀመዛሙርትን በዲፕሎማ አስመረቀ፡፡

ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተካሔደው የምረቃ መርሐ ግብር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዲፕሎማና በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ደቀመዛሙርት የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት ቃለ ምእዳን “ቤተ ክርስቲያን ከአጽናፈ ዓለም አሰባስባ፤ አስተምራ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ልታሰማራችሁ በዝግጅት ላይ ቆይታችኋል፡፡ ይህ ለቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ሐብት በመሆኑ ያገኛችሁትን እውቀት ለወገኖቻችሁ እንድታካፍሉና ቤተ ክርስቲያን የጣለችባችሁን ሓላፊነት እንድትወጡ አደራ እላለሁ” ብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ያሬድ የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ፤ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ፤ የሶማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ደቀመዛሙርቱ መንፈሳዊ ትምህርት ሲከታተሉ ቆይተው ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል የሚዘጋጁበት ወቅት እንደሆነ አስታውሰው፤ በአባቶች ቡራኬ ለመመረቅ በመብቃታቸው እንኳን አደረሳችሁ በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኮሌጁ ዲን መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወልደ ሃና ባቀረቡት ሪፖርት በመማር ማስተማሩ ሂደት ያጋጠሟቸውን ችግሮች ላይ ትኩረት በማድረግ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት መምህራን ሲለቁ በቦታቸው ቶሎ ተተኪ ያለመመደብ፤ የሚመሩ ደብዳቤዎች ባልታወቀ ሁኔታ መጥፋት፤ ኮሌጁ ለሚጽፋቸው ደብዳቤዎች ምላሽ ያለማግኘት፤ የሥራ ጣልቃ ገብነት ጎልተው ከሚታዩት ችግሮች ውስጥ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡

ኮሌጁ ምሁራንን እያፈራ የሚገኝ ቢሆንም ዘመኑን ባልተከተለ አሠራር እየተጓዘ ከአባቶች እንደተረከብነው ለተተኪ ትውልድ ማስተላለፍ እንችላለን ወይ? በሚል ጥያቄ ውስጥ እንደሚገኙም መጋቤ ጥበብ ምናሴ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኮሌጁ በየዓመቱ የሚቀበላቸው ደቀመዛሙርት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱም እንደማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

sewa sewe brhan 2ከተመራቂ ደቀ መዛሙርቱ መካከል አባ ኪሮስ ወልደ አብ የትምህርት ቆይታቸውን አስመልክቶ የተሰማቸው ስሜት ሲገለጡ “ትምህርት ጀመርኩ እንጂ አልጨረስኩትም፤ የበለጠ እንድማር አነሳሥቶኛልና እቀጥልበታለሁ፡፡ በኮሌጁ ቆይታዬም በእቅድ መመራት በመቻሌ በጥሩ ሁኔታ ተምሬ በማዕረግ ለመመረቅ ችያለሁ” ብለዋል፡፡

 

ተመራቂ ደቀመዛሙርት ያወጡትን የጋራ መግለጫ በተወካያቸው አማካይነት ያቀረቡ ሲሆን፤ በኮሌጁ ውስጥ አንዳንድ መልካም ሥራዎች ቢኖሩም በኮሌጁ ቆይታቸው በስፋት ይታያሉ ያሏቸውን ችግሮች ዳስሰዋል፡፡ የትምህርት አሠጣጡ ዘመኑን የዋጀsewa sewe brhan 1 ያለመሆን፤ ለመምህራን በቂ ደሞዝ ያለመከፈል፤ ከሌሎች መሰል የቤተ ክርስቲያኒቱ ኮሌጆች ጋር የልምድ ልውውጥ ያለማድረግ፤ በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ የሚገኙ መጻሕፍት በቂ ያለመሆናቸው፤ የመደበኛ ተማሪዎች ቁጥር መቀነስ እንደ ችግር ከጠቀሷቸው ውስጥ ይገኙበታል፡፡

ደቀመዛሙርቱ እንደመፍትሔ ካቀረቧቸው ውስጥ፤ የትምህርት አሰጣጡ በሚመጥን መልኩ ቢቀረጽ፤ ተቋማዊ አቅሙን ወደ ዩኒቨርስቲነት ቢያሳድግ፤ በከፍተኛ ውጤት ለሚመረቁ ደቀመዛሙርት የነጻ ትምህርት እድል ቢመቻች የሚሉት ሐሳቦች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ከ212 ተመራቂ ደቀ መዛሙርት መካከል 12ቱ በመደበኛነት ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አንድ በብሉያት፤ አንድ በሐዲሳት ትርጓሜ የተመረቁ ናቸው፡፡ 200 ደቀመዛሙርት ደግሞ በማታው የትምህርት መርሐ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የኮሌጁ መምህራንና የተመራቂ ደቀመዛሙርት ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡