በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡

በፍትሕ መንፈሳዊ አቀንቀጽ 5 ተራ ቁጥር 164 ድንጋጌ መሠረት፣ ከግንቦት 4 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የተካሔደውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን አስመልክቶ ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

1. በዓለማችንና በአገራችን ኢትዮጵያ ጭምር ከቅርብ ወራት ወዲህ የተከሠተው የኮረና ቫይረስ/ኮቪድ-19/ ወረርሺኝ እስከ አኹን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በመያዙ እና ከመቶ ሺሕዎች ላላነሱ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያተ በመኾኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን በእጅጉ ያሳዘነ ሲኾን፣ ጉባኤው፣ በቫይረሱ የተጠቁትን ምሕረት እንዲሰጥልን እስከ አኹን በቫይረሱ ያልተጠቁትንም እንዲጠብቅልን ተማኅፅኖውን ለእግዚአብሔር አቅርቧል፡፡

2. ይኸው ተላላፊ እና የሰው ልጆችን በሞት እየነጠቀ ያለውን ቫይረስ፣ እግዚአብሔር አምላክ በምሕረቱ እንዲያጠፋልን፣ ምእመናን፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ እና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመኾን እንዲጸልዩ፤ ተይዞ የነበረውን የሱባኤ ጊዜ በአግባቡ መከናወኑን ጉባኤው ተገንዝቦ ለወደፊቱም ካህናትም ኾኑ ምእመናን ወደ እግዚአብሔር የሚያደርጉትን ጸሎት በቤተ ክርስቲያንም ኾነ በቤታቸው አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጉባኤው አበክሮ አሳስቧል፡፡

3. በዚኹ ወረርሺኝ መከሠት ምክንያት፣ በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የሚሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት መቋረጡ፣ በምእመናን ሕይወት ላይ ችግር እየፈጠረ መኾኑና ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን ተለይተው መኖር ስለማይችሉ፤ በቀጣይም፣ የሕዝብ ጤና መጠበቅ በሚያረጋግጥ መልኩ፥ የሚመለከታቸው የሃይማኖት አባቶች እና የጤና ባለሞያዎች በሚሰጡት ሞያዊ ምክር እና መንግሥትም በሚሰጠው መመሪያ መሠረት አኹንም የአካላዊ ርቀት እና ንጽሕና አጠባበቅ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ተሰጥቶት፣ ለዚኹ ተግባር በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ በተመደቡ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አስተናጋጅነት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲከናወን፤

4. አገራችን ኢትዮጵያ አገረ እግዚአብሔር፣ ሕዝቧም ሕዝበ እግዚአብሔር እየተባለ እንደሚጠራ ይታወቃል፡፡ መጠራትም ብቻ ሳይኾን፣ ሕዝባችን በፈሪሃ እግዚአብሔር ተከባብሮ እንኳን የራሱ የኾነውን ወገኑን ቀርቶ ሌላውን እንደራሱ አድርጎ የሚወድ፣ ያለው ከሌለው ጋራ የሚካፈል እና በደግነቱ የሚታወቅ ሕዝብ መኾኑን ዓለም የሚመሰክረው ነው፡፡

በመኾኑም፣ ይህ የደግነት ምሳሌነታችን በተለይም በዚህ የኮረና ቫይረስ ወረርሺኝ በጸናበትና ኹሉም ወገን የችግሩ ተጋላጭ ኾኖ በተገኘበት በአኹኑ ጊዜ፣ ያለውን ለሌለው በማካፈል ይበልጥ ደግነታችን ጎልቶ እንዲታይ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንደምንገኝ የተገነዘበው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ ኹላችንም ባለን ነገር ኹሉ በመረዳዳት ይህን ፈታኝ ጊዜ እንድናልፈው ጥሪን ያቀርባል፡፡

5. ከዚኽም ጋራ ዜጋው እንደ ሀገር በኹለት እግሩ ቁሞ፣ ህልውናው ተጠብቆ ሊኖር የሚችለው እና አገራዊ ልማትም ኾነ ሕዝባዊ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው በኹሉም ዘንድ ሰላም እና አንድነት መግባባትም ጭምር ሲኖር እንደኾነ ይታወቃል፡፡

ኾኖም በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በፖሊቲካ ድርጅቶች መካከል እየታየ ያለው አለመግባባት እና የቃላት መወራወር በአጭሩ ካልተገታ እና ወደ መግባባት በመምጣት መፍትሔ ካልተበጀለት፣ ተጨማሪ አገራዊ ቀውስ ሊያስከትል፣ ከፍተኛም ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል በመገንዘብ፣ የሚመለከታችኹ የፖሊቲካ ድርጅቶች ኹሉ፣ ለአገራዊ ሰላም እና ለሕዝባዊ አንድነቱ በጋራ እንድትቆሙ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

6. አገራችን ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ዕድገት ያበቃል፣ ሕዝባችንን ከድህነት አረንቋ ያወጣል፤ በሚል እምነት ክጅም ጊዜ አንሥቶ ሕዝባችን ትኩረት ሰጥቶ ምንም ሳይኖረው፣ ጦሙን እያደረ አስተዋፅኦ በማድረግ እዚኽ ደረጃ ላይ ያደረሰው የሕዳሴ ግድባችን፣ አብዛኛው የግድቡ ሥራው እየተጠናቀቀና ወደ ፍጻሜውም እየደረሰ መኾኑ ስለተገለጸ፣ ጉባኤው፣ በከፍተኛ አድናቆት ተመልክቶታል፡፡ በቀጣይም፣ የግድቡን ፍጻሜ ለማየት፣ የመላውን ሕዝባችን ርብርብ እንደሚጠይቅ ግንዛቤ የተወሰደ በመኾኑ፣ እንደ አባቶቻችን ለትውልድ የሚተርፍ ታሪክ ለመሥራት፣ ሕዝባዊ አንድነቱ እና ተሳትፎው እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡

በመጨረሻም፣ ከግንቦት 4 እስከ ግንቦት 6 ቀን ለሦስት ቀናት ያኽል፣ በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ፣ እንዲሁም አገራዊ ጉዳይ ላይ ሲነጋገር የቆየው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጠናቅቆ በዛሬው ቀን በጸሎት ተዘግቷል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ግንቦት 6 ቀን 2012 ..

አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ