የቅዱስ ሲኖዶስን ጉባኤ መጀመር አስመልክቶ ከቅዱስ ፓትርያሪኩ የተሰጠ መግለጫ

ግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች፣ እንደሚታወቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል፤ ቅዱስ ፓትርያሪኩ ጠዋት ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና ለጋዜጠኞች የሰጡትን ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ወዓዲ እብለክሙ ለእመ ኀብሩ ክልኤቱ አው ሠለስቱ እምኔክሙ በውስተ ምድር በእንተ ኵሉ ግብር ዘሰአሉ ይትገበር ሎሙ በኀበ አቡየ ዘበሰማያት እስመ ኀበ ሀለዉ ክልኤቱ ወሠለስቱ ጉቡአን በስምየ ህየ እሄሉ አነ ማእከሎሙ፤ ዳግመኛም ከእናንተ ሁለቱ ወየም ሦስቱ በምድር ላይ ስለሚለምኑት ሥራ ሁሉ ቢተባበሩ፣ በሰማያዊ አባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል፤ ሁለቱ ወይም ሦስቱ በስሜ ተሰብስበው ካሉበት፣ እኔ ከዚያ በመካከላቸው እገኛለሁና /ማቴ.፲፰፥፲፱-፳/፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

ከጌታችን፣ ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠንን ዓቢይ ተልእኮ ወይም ሐዋርያዊ አገልግሎት በየተሠማራንበት ሀገረ ስብከት ስናከናውን ቆይተን፣ በዓለ ትንሣኤውን ካከበርን በኋላ፣ በቀኖና ሐዋርያት ድንጋጌ መሠት፣ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዮች ለመነጋገር በዚህ በረክበ ካህናት ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አንድ ላይ ስለሰበሰብን፣ አምላካችን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማይታበል ቃሉ እንዳስተማረን፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የገባው ቃል ኪዳን አለ፤ እርሱም ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር የተፈጸመ ጽኑ ቃል ኪዳን ነው፡፡ ቃል ኪዳኑም፡- ሁለቱ ወይም ሦስቱ በስሜ በተሰበሰቡበት፣ እኔ ከዚያ በመካከለቸው እገኛለሁ ይላል፡፡ በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው፣ ቃል ኪዳን በሁለት ወገኖች መካከል የሚፈጸምና ለቃል ኪዳኑ መከበር የሁለቱንም የቃል ኪዳን አካላት ኃላፊነት በግልጽ የሚያስቀምጥ ነው፤በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ ከቅዱሳን አበው ጋር ቃል ኪዳን መሥርቶ እንደነበረ በቅዱስ መጽሐፍ በየቦታው ተጽፎ እናገኛለን፡፡

ይሁንና በዘመነ ሐዲስ ጌታችን ቃል ከገባባቸው ዓበይት ነገሮች አንዱ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ነው፡፡ በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በስመ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሰበሰብ ሓላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ጌታችንም በስሙ በሚደረግ ጉባኤ እንደሚገኝ ቃል ገብቶአል፡፡

በመሆኑም የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በርእሰ መንበርነት፣ ቅዱስ ፓትርያርክ በመሪነት፣ ሊቃነ ጳጳሳት በአባልነት የሚገኙበት ዓቢይ ጉባኤ ነው፡፡ ቅዱስ ወይም ልዩ ጉባኤ የሚያሰኘውም ቅሉ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በርእሰ መንበርነት የሚገኝበት በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ጉባኤ ጌታችን እስከ ዓለም ፈጻሜ ድረስ እንደማይለየው ሲገልጽ፡- ወናሁ አነ እሄሉ ምስሌክሙ እስከ ኅልቀተ ዓለም፤ እነሆ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እኔ ከናንተ ጋር ነኝ ብሎ በቃሉ አረጋጦአል /ማቴ.፳፰፥፳/፡፡

እንግዲህ በየጊዜው ስመ እግዚአብሔርን ጠርተን በስሙ፣ ስለስሙ ብለን የምናካሂደው ቅዱስ ጉባኤ ወይም ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ያህል ታላቅ ክቡርና ጽኑ የሆነ አምላካዊ ቃል ኪዳን ያለው እንደመሆኑ መጠን፣ ለደረጃው በሚመጥን ክብርና ልዕልና መካሄድ ይኖርበታል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

ጌታችን፣ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን በአደራነት ያስረከበ ለዚህ ጉባኤ እንደሆነ በውል የሚታወቅ ነው፡፡

ይህ ቅዱስ ጉባኤ የእግዚአብሔር መንግሥት ወኪል እንደመሆኑ መጠን ድንበር የለውም፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት ድንበር የለውምና፡፡ ይህ ጉባኤ ገደብ የለሽ መንፈሳዊ ሥልጣን ከሕያው አምላክ ሲሰጠው፣ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ ከሚል ትእዛዝ ጋር መታዘዙ የቅዱስ ሲኖዶስ መንፈሳዊ ሥልጣን ድንበር የማይገድበው መሆኑን በግልጽ ያሳያል /ማር.፲፮፥፲፭/፡፡

በመሆኑም የዚህ ቅዱስ ጉባኤ ሥራና ሓላፊነት ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል፡፡ ይህም በመሆኑ ነው ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን በሁሉም ክፍላተ ዓለም አብያተ ክርስቲያናትን ከፍታ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በማካሄድ ላይ የምትገኘው፡፡

ይሁንና አሁን የምንገኝበት የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ወቅት፣ የሴኩላሪዝም አስተሳሰብ ያየለበት፤ የዓለም ሉላዊነት የበረታበት፣ የጽንፈኝነትና የሽብርተኝነት መንፈስ የተስፋፋበት፣ እነዚህ ሁሉ በየፊናቸው ተሰልፈው በሃይማኖት ላይ ከባድ ተጽዕኖ የፈጠሩበት ዘመን ነው፡፡ ዓለም በዚህ ሥጋዊ ፍልስፍና እና ቁሳዊ አምሮት ቤተ ክርስቲያንን ለመውጋት ስትዘጋጅ እኛ የክርስቶስ ወኪሎች እንዲሁ ዝም ብለን የምናይበት ኅሊና ሊኖረን አይችልም፡፡

ቀደምት አበው እሾህን በእሾህ ብለው እንደተናገሩት፣ የዓለምን ጥበብ በክርስቶስ ጥበብ ለመቋቋም፣ በዓለም እየሆነ ያለውን ነገር ሁሉ መከታተልና ማወቅ፣ ለወደፊትም ሊያስከትለው የሚችለውን ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሰብአዊና ባህላዊ ቀውስ አስቀድሞ በመተንበይ፣ ሕዝቡን በእግዚአብሔር ቃል ኃይል መጠበቅና መንከባከብ ከእኛ ይጠበቃል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

በሃይማኖት ዙሪያ ያንዣበቡ እነዚህ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዎች እጅግ አስጊ ቢሆኑም፣ እነርሱን ለመከላከል ብሎም ለመቀልበስ አሁንም ቢሆን ጊዜው አልመሸም፡፡ በተለይም በሀገራችን ያለው ሕዝብ፣ አሁንም ምርጫው እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንደሆነ በተጨባጭ የምናውቀው ሐቅ ነው፡፡ ይህንን ሕዝብ በሚገባ ማገልገል ከተቻለ፣ ችግሩን በሚገባ መቋቋም ይቻላል፡፡

ስለሆነም ሕዝበ ክርስቲያኑን በአግባቡ ለማገልገልና ለመጠበቅ፣ ከሁሉም በፊት የሕዝቡን ጥያቄ ማወቅ ያስፈልጋል፤ ቀጥሎም ለጥያቄው ተገቢ የሆነ መልስ በመስጠት ፍጹም መግባባት መፍጠር ይገባል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ ከሃይማኖት መሪዎችና ከአገልጋይ ካህናት የሚጠብቀውን ሁለንተናዊ አገልግሎት በሚገባ ካገኘና በሃይማኖቱ እንዲኮራ የሚያስችል ሁኔታ ከተመቻቸለት፣ ለተጠቀሱ ዓለም ዓቀፍ ተፅዕኖዎች ተንበርካኪ አይሆንም፡፡ ስለሆነም የኛው የጥበቃ ስልት መቀየስ ያለበት በዚሁ መንፈስ አቅጣጫ ነው፡፡

ሕዝበ ክርስቲያኑ በአሁኑ ጊዜ የሚጠይቃቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤

ሕዝቡ፣ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና ለሃይማኖት መጠበቂያ ብሎ በእምነት የሚለግሰው ገንዘብና ንብረት ከምዝበራ ተጠብቆ ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል ይፈልጋል፤

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መልካም አስተዳደር ሰፍኖ አድልዎ፣ ጭቅጭቅ፣ ንትርክ፣ መለያየት በአጠቃላይ ከሃይማኖቱ መርሕ ጋር የማይጣጣም ኋላ ቀር አሠራርና አስተሳሰብ ተወግዶ የተስተካከለ ሥርዓትን ማየት ይፈልጋል፤

ስለሃይማኖት ክብርና ህልውና ከልብ የሚቆረቆሩ፣ መልካም የሆነ ሥነ ምግባርና የተስተካከለ ሰብእና ያላቸው እንደዚሁም በኑሮአቸው ሁሉ ለሕዝበ ክርስቲያኑ እንደ ሞዴል የሚጠቀሱ ውሉደ ክህነትና ሠራተኞች እንዲመሩት ይፈልጋል፤

ሕዝቡ ቤተ ክርስቲያን በሁሉም መስክ ጠንካራ ዓቅምን ገንብታ እንደዚሁም ለሕዝበ ክርስቲያኑ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ችግር ደራሽና አለሁላችሁ ባይ ኾና ማየት እንደሚፈልግ ከሚያነሣው ጥያቄ ማወቅ ይቻላል፡፡

ብፁዓን ሊቃ ጳጳሳት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

የእኛ ተልእኮ እግዚአብሔርንና ሕዝብን ማገልገል ከሆነ፣ የሕዝቡ ጥያቄም ከሞላ ጎደል የሚታወቅ ከሆነ፣ በተሰጠን አደራና ሓላፊነት መሠረት የሕዝበ ክርስቲያኑን ጥያቄ በጽሞና አዳምጠንና ተቀብለን፣ በቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌና ባሉን የቤተ ክርስቲያን ሕጎች ማእከልነት፣ ጥያቄውን የማስተናገድ ክርስቶሳዊ ግዴታ አለብን፡፡

ከሕግ የወጣ የሥራ አፈጻጸም ሲኖርም፣ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በወቅቱ ማረም ያስፈልጋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቱያናችን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ አካል እንደመሆኑ መጠን፣ የቤተ ክርስቲያናችንን መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚያስችሉ ሕጎችን፣ ልዩ ልዩ ደንቦችን፣ መመሪያዎችን፣ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀትና በማጽደቅ፣ እንደዚሁም በአፈጻጸማቸው ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን እሰየው የሚያሰኝ አሠራር ማረጋገጥ አለብን፡፡ ይኸ ሲሆን ብቻ ነው ሕዝቡን ከቁሳዊው ዓለም ማዕበል መታደግ የምንችለው፡፡

በመጨረሻም

ይህ የተቀደሰ ክርስቶሳዊና ሐዋርያዊ ጉባኤ ከልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያናችን አመራር አካላትና ከጉባኤው የሚቀርቡትን ሃይማኖታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በጥልቀት በመፈተሽና በመመርመር እንደዚሁም ሕጋዊና ቀኖናዊ መፍትሔ በማስቀመጥ የተሳካ ውጤት ያስመዘግብ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እየጸለይንና ከልብ እየተመኘን የ፳፻፰ ዓ.ም የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዛሬ መከፈቱን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤

አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም

ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፡፡