001sinoddd

የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጠናቀቀ

ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም.

001sinoddd

ሚያዝያ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት በጸሎት የተጀመረው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሲካሔድ ቆይቶ ዛሬ ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ተጠናቅቆ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 ላይ በተደነገገው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ ይካሄዳል፡፡

ከሁለቱ አንዱ ከጌታችን ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን በዕለተ ረቡዕ የሚውለው የርክበ ካህናት ጉባኤ ነው፡፡

በመሆኑም የርክበ ካህናቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሚያዝያ 27 ቀን ከሰዓት በኋላ በጸሎት ተከፍቶአል፡፡

በመቀጠልም ሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባን በጸሎትና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የመክፈቻ ንግግር ተጀምሮ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ ሰንብቶአል፡፡ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችንም አስተላልፎአል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለዐራት ቀናት ያህል ባካሄደው ቀኖናዊ ጉባኤ፡-

-ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚጠቅሙትን፣

-ለልማትና ለሰላም የሚበጁትን፣

-ከሀገር ውጭ ለሚገኙና በሀገር ውስጥ ላይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁለንተናዊ ሕይወት መጠበቅ የሚያስችሉትን ርእሰ ጉዳዮች በማንሣት በስፋትና በጥልቀት አይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፎአል፡፡

1.ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በጉባኤ መክፈቻ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ሕይወት የቃኘ የሀገራችን ዕድገትንና የሰላም አስፈላጊነት በስፋት የገለጸ በመሆኑ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፡፡

2.ምልአተ ጉባኤው በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበውን ዓመታዊ የሥራ መግለጫ ሪፖርት አዳምጦ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማድረግ በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፡፡

3.ምንም ጥፋትና በደል ሳይኖርባቸው ክርስቲያኖች በመሆናቸው ብቻ በሊቢያ ሀገር አይ ኤስ በተባለ የአሽባሪዎች ቡድን በግፍና በሚዘገንን ሁኔታ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችንና የግብፅ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ቋሚ ሲኖዶስ ቀደም ሲል በሟቾቹ መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ተወያይቶ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት ምልዓተ ጉባኤው ያለውን ሁኔታ በጥልቀት ከተረዳ በኋላ ሟቾቹ የዘመኑ ሰማዕት እንዲባሉ ተስማምቶ ወስኗል፡፡

4.እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም በሊቢያ የተሠውት 30 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ልጆቻችን እና እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም በሊቢያ የተሠውት 21 የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ክርስቲያኖች በሁሉቱም አብያተ ክርስቲያኖች ሲኖዶስ የሰማዕትነት ክብር የተሰጣቸው ስለሆነ፣ የሁለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰማዕታት ተብለው በአንድነት እንዲታሰቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡

5.በልዩ ልዩ ምክንያት ከኢትዮጵያ ሀገራቸው ወጥተው በባዕድ ሀገር የሚገኙትንና ወደ ሀገራቸው በመመለስ ላይ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከልና ለማቋቋም ቤተ ክርስቲያናችን መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት በመቀናጀት አስፈላጊውን ሁሉ እንድታደርግ፣ ይህን በተመለከተ ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያናችን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንም እርዳታ ሰጪዎችን በማስተባበር ኃላፊነቱን ወስዶ በንቃትና በትጋት እንዲሠራ ጉባኤው ወስኖአል፡፡

6.ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ አምስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን በሂደት ላይ መሆኗን ቅዱስ ሲኖዶስ አውስቶ ምርጫው ሰላማዊና ፍትሐዊ ሆኖ በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን በጸሎት እንድትተጋ ጉባኤው መልእክቱን አስተላልፏል፡፡

7.ኢትዮጵያ ሀገራችን ለብዙ ዘመናት ተጭኖአት ከቆየ የድህነት አረንቋ በተጨማሪ የእርስ በእርስ ግጭት ጥሎባት ባለፈ ጠባሳ ክፉኛ የተጎዳች ብትሆንም በተገኘው ሰላም ምክንያት ባሳለፍናቸው ዓመታት እየታዩ ያሉ የልማትና የዕድገት፣ የእኩልነትና የአንድነት እመርታዎች የሰላምን ጠቃሚነት ከምንም ጊዜ በላይ መገንዘብ የተቻለበት ስለሆነ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንም በላይ ሰላሙንና አንድነቱን አጽነቶ በመያዝ ሀገሩን ከአሸባሪዎችና ከጽንፈኞች ጥቃት ነቅቶ እንዲጠበቅ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ያሳስባል፤

8.ሀገራችን ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂና የካፒታል እጥረት እንደዚሁም በሀገር ውስጥ ሠርቶ የመበልፀግ ግንዛቤ ማነስ ካልሆነ በቀር በተፈጥሮ ሀብትም ሆነ በማናቸውም መመዘኛ ከሌላው የተሻለች እንደሆነች የታወቀ ስለሆነ፤ ወጣቶች ልጆቻችን ወደ ሰው ሀገር እየኮበለሉ ራሳቸውን ለአደጋ ከሚያጋልጡ በሀገራቸው ሠርተው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ኅብረተሰቡም ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ በሰፊው እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ መልእክቱን አስተላልፏል፤

9.ለሀገራችንና ለሕዝቦቻችን ችግሮች ቁልፍ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ልማትን በማጠናከርና ዕድገትን በማረጋገጥ ድህነትን ማስወገድ ስለሆነ ሕዝባችን ይህን ከልብ ተቀብሎ በየአቅጣጫው የተጀመሩትን የልማት ሥራዎች በመደገፍ ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች እኩል ለማሰለፍ የሚደረገውን ሀገራዊ ርብርቦሽ ለማሳካት በርትቶ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፤

10.በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያ ክርስቲያናት በየቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ሁሉ የአረንጓዴ ልማትና የራስ አገዝ ልማት በማካሄድ ልማትን እንዲያፋጥኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥብቅ መመሪያ አስተላልፎአል፡፡

11.በውጭ ሀገር ከሚገኙ አባቶች ጋር ተጀምሮ የነበረው የእርቀ ሰላም ድርድር ለሀገራችን ልማትና ለሕዝባችን አንድነት የሚሰጠው ጥቅም የማይናቅ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያናችን በር ለሰላምና ለእርቅ ክፍት መሆኑን ምልዓተ ጉባኤው ገልጿል፡፡

12.ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በተገለፁትና በሌሎችም መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሲወያይ ሰንብቶ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት በጸሎት አጠናቆአል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን ለሕዝባችንና ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣ ምሕረቱንና ፍቅር አንድነቱን ይስጥልን፤

እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም.

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ