‹‹የሞተ ሰውስ ዐረፈ፤ ነገር ግን መታሰቢያውን አድርግለት›› (ሲራክ ፴፰፥፳፫)

ሰዎች ሕያው ሆነን በፈጣሪ አምሳል እንደተፈጠርነው ሁሉ በኃጢአት ሳቢያ የተፈረደበትንን ሥጋዊ ሞት እንሞት ዘንድ አይቀሬ ነው፤ ‹‹አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህና›› እንደተባለውም የሰው ዘር በሙሉ ወደ አፈርነት ይመለሳል፡፡ በሕፃንነትም ይሁን በጎልማሳነት እንዲሁም በእርጅና ሰዎች ይሞታሉ፡፡ በበሽታ፣ በአደጋ ወይንም በግድያ የሰዎች ሕይወት በየጊዜው ይቀጠፋል፡፡ በተለይም በዚህ ትውልድ ዓለማችን በየጊዜው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አያጣች ነው፡፡ በእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት እንዲሁም የሰዎችን ሕይወት እንደ ቅጠል እያረገፈ ባለው ኮሮና በሽታ እጅግ ብዙ ሰዎች ሞተዋል፡፡(ዘፍ.፫፥፲፱)

ሥጋዊ ሞትን የማይቀመስ ሰው ባለመኖሩ ለእኛ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ ሞት ለጊዜው የነፍስ ከሥጋ መለየት እንጂ የሰው ለዘላለም መጥፋት አይደለም። ይህ በሥጋ የሚገጥም አካላዊ ሞት በምድር ካለ የዘወትር ድካም፣ ሐዘን፣ ሕመም፣ ፍርሐት ይህችን ዓለም ከሞላባት ድካም ሁሉ ማረፊያ መንገድ ነው፡፡ ሆኖም ግን የሞት ሞት የሆነውን የነፍስ ሞት እንዳሞት መፍራት ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች እንዲህ በቀላሉ ሲሞቱ ማየት ባያስገርምም ግን አስከፊ መሆኑን ማንም የማይክደው እውነት ነው፡፡ የሰው ሕይወት እንደ ግዑዝ ነገር እየተቆጠረና ክብር ባጣ መልኩ መገደሉን መስማት ሆነ ማየትም  እየተለመደ መጥቷል፡፡ በበሽታውም ሆነ በግድያው ዕልቂት የሚሞቱ ሰዎች ግን ለንስሓ የበቁም ሆነ ያልበቁ ስለሚሆኑ በሕይወት ያለን ሰዎች ለሞቱት መታሰቢያ ልናደረግ ይገባል፡፡

የኃጢአተኛ ነፍስ ከሥጋ ተለይታ ለፍርድ አስከምቀርብበት ዕለተ ምጽአት ድረስ ይቆያል፤ የኃጥአንም መጨረሻ ሲኦል ቢሆን እንኳን ከምድር እንደተለዩ ወደ ገሃነመ እሳት እንደማይገቡ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ይገልጻል፡፡ ጻድቃን ገነት ሆነው መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ በሐሴት ሲቀዩ ኃጢአተኞች ግን በሲኦል ይሰቃያሉ፡፡

በዚህ ዓለም የነበሩ ክርስቲያኖች በሕይወት በነበሩበት ዘመን በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በመኖራቸው በገነት ሆነው በእግዚአብሔር ፊት ስለ ኃጥአን ሊጸልዩ ይቻላቸዋል፤ ወደ ሲኦል የወረዱ ከሆኑ ደግሞ በዚያ ሆነው የእኛን ጸሎት ይሻሉ።

ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ ለነበረው ለሄኔሴፎር ‹‹በዚያችም ቀን በጌታችን ፊት ይቅርታን እንዲያገኝ እግዚአብሔር ይስጠው›› ብሎ እንደጸለየለት ቤተ ክርስቲያንም ለሞቱት ሁሉ ጸሎተ ፍትሐት ታደርጋለች። ይህም ደግሞ በጥንት በዘመነ ብሉይም የነበረ ሥርዓት ነው። (፪ኛ ጢሞ. ፩፥ ፲፰)

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በተላከው የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል ‹‹አንድ ሰው ኃጢአተኛ እንደሆነ ቢሞት የምንችለውን ያህል ልንረዳው ይገባል። የምንረዳውም በለቅሶና በሐዘን ይሆን በጸሎት፣ በምጽዋትና በቁርባን ነው። የዓለምን ኃጢአት ወደ ተሸከመው የእግዚአብሔር በግ ስለ ሙታን የምንጸልየው እነርሱ መጽናናትንና ዕረፍትን እንዲያገኙ ብለን ነው እንጂ በከንቱ አይደለም። ጻድቁ ኢዮብ ስለልጆቹ ያቀርብ የነበረው ቁርባን ጠቀሜታ ከነበረው ስለ ሙታን የምናቀርበው ቁርባን ምንኛ የበለጠ ጠቀሜታ ይኖረው? ከሞትም በኋላ ቢሆን በሰዎች መካከል የሚኖረው መንፈሳዊ ግኑኝነት በጸሎት አማካይነት ይቀጥላል።›› በእምነት የሚደረግ ጸሎት ኃይል እንዳለው ተራራንም ለማንቀሳቀስ እንደሚያስችል በወንጌል ተገልጾልና፤ መጽሐፍ ቅዱስም የአንዱ ሰው ጸሎት ሌላውን እንደሚረዳ ያስተምረናል።

በመጽሐፈ ሲራክ ላይ ‹‹ልጄ ሆይ፥ ለሞተ ሰው አልቅስለት፥ እዘንለትም፤ ራስህን አሳዝን፤ እንደ ሥርዓቱም መታሰቢያ አድርግለት›› ይላል። ቀጥሎም ‹‹የሞተ ሰውስ ዐረፈ፤ ነገር ግን ነፍሱ መታሰቢያውን አድርግለት፤ ከዚህ በኋላ ነፍሱ ታርፍ ዘንድ ልቅሶህን ተው›› በማለት ለሞቱ ወገኖች መታሰቢያ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ያመለክታል። (ሲራ. ፴፰፥፲፮-፳፫)

ኃጢአተኛ ሰው በሥጋ ከተለየ በኋላ ስለ ኃጢአቱ ሥርየት መማጸን አይችልምና በአካለ ሥጋ ያሉ ሰዎች ስለ ሙታን ይለምኑ ዘንድ ይገባል፤ እግዚአብሔር ምሕረቱ የበዛ መአቱ የራቀ ነውና ስለ እነርሱ ብሎ ሊምራቸው ይችል ዘንድ የታመነ ነው፡፡

ለሙታን የሚደረግ ጸሎት ወይም ጸሎተ ፍትሐት በእግዚአብሔር ፊት ይቅርታን ለማግኘት ይረዳል፡፡ እግዚአብሔርም ለሙሴ የነገረው ‹‹ሰው ባለማወቅ ኃአጢአት ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም፡- አትሥሩ ካላቸው ትእዛዝ አንዲቱን ቢተላለፍ፥ ቢታወቀው፥ ኃጢአት ስለሆነችበት ንስሓ ቢገባ፥ ነውር የሌለበትን በሰቅል መሥዋዕት ወደ ካህኑ ያመጣዋል፤ ካህኑም ሳያውቅ ስለ ሳተው ስሕተት ያስተሰርያል፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል›› ብሎ ነውና፡፡ (ዘሌ.፭፥፲፯-፲፰)

ጸሎት ለኃጥአን ሥርየት እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። ቤተ ክርስቲያንም በጸሎተ ፍትሐት ለሙታን ምሕረትን ትለምናለች፤ በሐዘንም ለዕለተ ሞታቸው መታሰቢያ ታደርጋለች፤ ጌታችን ኢየሱስ ደቀ መዝሙሩ አልዓዛር ሲሞት አዝኖለት እንባውን አፍስሷልና።

ለሞቱ ሰዎች መታሰቢያ ወይንም ተዝካር ማድረግም አንዱ  የቤተክርስቲያን ሥርዓት ከመሆኑ በተጨማሪ ለሙታን ምሕረትን ለመማጸን ይረዳል፡፡ በጸሎት፣ በመሥዋዕት፣ በመብራት፣ በማዕጠንት እና በምጽዋት መታሰቢያ ይደረግላቸዋል። በጸሎተ ፍትሐት ዳዊት መድገም፣ ገንዘብ በመለገስ፣ የሙት ስም በጸሎት እንዲነሣ፣ ቅዳሴ እንዲቀደስ እና ቁርባን እንዲቆርብ ማድረግ ተገቢ ነው። ነገር ግን ከንብረቱ ከፍሎ ለድሆች እና ለጦም አዳሪዎች መመጽወት ማለት እንጂ ድግስ ደግሶ ዘመድ ጠርቶ መብላት መጠጣትና ብድራትን መመላለስ ማለት አይደለም። ይህ ባሕል እንጂ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን አይደለም። ከገንዘቡም መስጠት ያለበት ለድሆች መሆኑን መጽሐፈ ሲኖዶስ ይገልፃል፡፡ ሰው በተለምዶም ይሁን እከሌ ተዝካር አወጣ ለመባል ብቻ ሁለት ወይም ሦስት ዓመት እየቆየ ይደግሳል፤ ይህን ቤተ ክርስቲያናችን አትቀበለውም። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በቀኖና የወሰነችው የደነገገችው አይደለም። ሕዝቡ ራሱ በልማድ ያመጣው ነው፤ ለደገሰው ድግስ ኃላፊው ራሱ ደጋሹ ነው። (መኾኒ ደብረ ሲና ቅድስት ማርያም ፍሬ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት)

ለሞቱ ሰዎች መታሰቢያ ማድረግ ወይንም ስለተዝካር ማውጣት በአሁኑ ጊዜ ሰዎች የተሳሳተ መረጃ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱም አስፈላጊነቱን የማይቀበሉ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን መቅረቱን በዐዋጅ እንደተነገረ በማሰባቸው ነው፡፡ ይህም በማኅበረሰቡ ውስጥ የተዛባ አመለካከት መፍጠሩ አይካድም፡፡ ስለዚህም ጉዳይ የኮኩሐ ሃይማኖት መጽሐፍ ደራሲ መልአከ ሰላም አድማሱ ጀንበሬ  በጽሑፋቸው እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ጊዜ ተዝካር ይቅር የሚሉ ሰዎች ከሥርዓት ውጭ የሚደረገው ድግስ ይቅር ማለታቸው ከሆነ ትክክል ናቸው። ፍትሐቱ ይቅር ማለት ግን ካለማወቅ የተነሣ የሚናገሩት ነው፤ ተዝካርና ከዐቅም በላይ የሆነ ድግስ የተለያዩ ነገሮች ናቸውና። እስከ አሁን ድረስ ቤተ ክርስቲያን ይህን ያህል ደግሳችሁ አብሉ ብላ አታውቅም። ጸሎተ ፍትሐቱን በቀኖና በተወሰኑት ቀናት ታካሂዳለች። ለሙታን ስለ ሙታን የሚደረጉት ሁለት ነገሮች ናቸው። አንደኛው በተገለጹት ጊዜያት ከሣልስት ጀምሮ በሟች ስም የነፍስ ይማር ጸሎተ ፍትሐት ማድረግ፥ ሁለተኛ በሟች ስም መሥዋዕተ ቁርባን ማቅረብ ናቸው። ለኃጢአት ማስተሥረያ መሥዋዕቱ በነፍስ ይማር ጸሎተ ፍትሐት ይታሰባል። እንደ ሦስተኛ አድርገን የምንቆጥረው በሟች ስም ለድሆች ምጽዋት መስጠት ማለትም በገንዘብና በዓይነት/ልብስ በማልበስ፥ ምግብ በማብላት/ የሚከናወነው ነው። ይህ ለድሆች ምጽዋት መስጠት ደግሞ በእህል ውኃም በገንዘብም ሊሆን ይችላል፤  ተዝካርም ፍትሐትም የሚባለው ይህ ነው። ዕለቱንም ስንዘክር በመሥዋዕት በቁርባን ነው እንጂ ከሥርዓት ውጭ በሆነ ድግስ አይደለም። ድግሳችን የክርስቶስ መሥዋዕት እንዲሁም ሕዝቡንም ጠርተን ተሳታፊ የምናደርገው ለጸሎቱ ወይንም ለነፍስ ይማሩ ድግስ ነው። የዚያን ቀን ለሟች በሚሠዋው መሥዋዕት ላይ ሕዝቡ ተገኝቶ ነፍስ ይማር እንዲጸልይና የመሥዋዕቱ /ሥጋ ወደሙ/ ተሳታፊ እንዲሆን ነው›› ይህንን ተረድተን ለሞቱት ወገኖቻችን በጸሎትና በተዝካር መታሰቢያ እናድርግ፡፡

እግዚአብሔር አምላክ የሙታንን ነፍስ ይማርልን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፤ መኾኒ ደብረ ሲና ድስት ማርያም ፍሬ ሃይማኖት ሰንበት ምህር ቤት፤ ኮኩሐ ሃይማኖት  ገጽ.  ፪፻፹ምዕራፍ ፲፭)