ten 2006 02

የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከልን ወደ ተቋምነት ለማሳደግ ምክክር ተካሄደ

 የካቲት 13 ቀን 2006 ዓ.ም.

በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

ten 2006 02ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ በማእከልነት ደረጃ ተቋቁሞ በጥናትና ምርምር፣ በቤተመጻሕፍት፣ በቤተ መዛግብትና ቋሚ ኤግዚቢሽን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል ወደ ተቋምነት እንዲያድግ የምክክር ጉባኤ በማኅበሩ የስብሰባ አዳራሽ በ11/06/06 ተካሄደ፡፡

በተካሄደው የምክክር ጉባኤ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የሴቲት ሁመራ ሊቀ ጳጳስና የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር አማካሪ ቦርድ ሰብሳቢ፣ የማኅበሩ የሥራ አመራርና ሥራ አስፈጻሚ አባላት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የምክክር ጉባኤው በጸሎት የተከፈተው በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ሲሆን፤ የምክክር ጉባኤው የመነሻ ጥናት ይዘው የቀረቡት ደግሞ የጥናትና ምርምሩ አማካሪ ቦርድ አባልና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ ናቸው፡፡

ten 2006 01ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ ባቀረቡት የመነሻ ሐሳብ የማኅበሩ ጥናትና ምርምር ማእከል እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎትና የጥናት ተቋም ባለመኖሩ እያስከተለ ያለውን ተግዳሮት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ቁጥር በየጊዜው እያሽቆለቆለ መሄዱ ያለውን አሳሳቢነት፣ የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከልን ወደ ተቋምነት ማሳደግ ያለውን ጠቀሜታና ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን አስረጅ በማቅረብ አስረድተዋል፡፡

ከጥናት አቅራቢው በመቀጠል ንግግር ያደረጉት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ጥናትና ምርምር ለቤተ ክርስቲያን በጣም አስፈላጊ መሆኑንና ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቅሰው ማእከሉን ወደ ተቋምነት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ አባታዊ አደራ ጥለውባቸዋል፡፡

ጉባኤውን በአወያይነት ሲመሩ የነበሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ሓላፊና መምህር የሆኑት ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ፤ ጥናትና ምርምር ለቤተ ክርስቲያን ሊያበረከት የሚችለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በመግለጽ ማኅበሩ የጀመረውን አገልግሎት ለመደገፍ በተሰማሩበት መስክ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ በምክክር ጉባኤው የተገኙት የማኅበሩ አመራር አባላት ለጥናት አቅራቢው የተለያዩ ጥያቄዎች አቅርበው ሰፊ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡