የማቴዎስ ወንጌል

ምዕራፍ ዐሥራ ሁለት

ታኅሣሥ 23 ቀን 2007 ዓ.ም.

ጌታችን እና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀዳሚት ሰንበት በእርሻ መካከል ባለፈ ጊዜ በጣም ተርበው የነበሩ ደቀመዛሙርት እሸቱን ቀጥፈው እያሹ በሉ፡፡ ፈሪሳውያንም “ሰንበትን ስለ ምን ይሽራሉ?” ብለው ደቀ መዛሙርቱን ከሰሷቸው፡፡ ጌታችን ግን ከሚያውቁት ታሪክ የዳዊትንና የተከታዮችን እንዲሁም የቤተ መቅደሱን አገልጋዮች ታሪክ ጠቅሶ ከነገራቸው በኋላ ‹”ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ፡፡ ምሕረትን እወዳለሁ፤ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኮነናችሁም ነበር፡፡ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና፡፡” ሲል መለሰላቸው፡፡

 

ይህም በበትረ ርኃብ ይመቱ፣ በረኃብ እንደ ቅጠል ይገረፉ ብላችሁ ባልፈረዳችሁባቸው ነበር፡፡ የሰንበት ጌታዋ ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ ነውና ሲላቸው ነው፡፡

 

ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ፡፡ እጁ የሰለለችውንም ሰው ፈወሰው፡፡ በሰንበት ለምን እንዲህ ታደርጋለህ? ባሉት ጊዜም በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዷል አላቸው፡፡ ብዙ በሽተኞችንም ፈወሳቸው፤ ሕዝቡ በሥራው ሲደነቅ ፈሪሳውያን ግን “ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል” ብለው በሰደቡት ጊዜ “ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም፡፡ በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም” ሲል መለሰላቸው፡፡

 

የሰው ልጅ ያለው ራሱን ነው፡፡ ስድብ ያለውም ክህደትን ነው፡፡ ይህም እርሱ ስድብ እንደሚገባው መናገሩ ሳይሆን ለመሰደቡ /ለመካዱ/ ምክንያት ሥጋ መልበሱ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስን የሚክዱ ግን ምክንያት የላቸውም፡፡ እነዚህ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን በካዱት ጊዜ ስለሚለያቸው ስለ ኃጢአቱ እንዲጸጸትና ራሱን እንዲወቅስ የሚያደርግ መንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡ ዮሐ. 16፤8፡፡ “በዚህ ዓለም ቢሆን” ሲል ስለ ኃጢአቱ ተጸጽቶ ወደ ካህኑ በመቅረብ እግዚአብሔር ይፍታህ” ስለማይባል ነው፡፡ “በሚመጣው ዓለም” ሲል ደግሞ በምድር ያልተፈታ በሰማይም ስለማይፈታ ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ደቀመዛሙርቱን በምድርም የምታሥሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፡፡” ብሎ ሥልጣን ሰጥቷቸዋልና፡፡

 

በዚያን ጊዜ ጻፎችና ፈሪሳውያን “ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን” ባሉት ጊዜም “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፤ ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም” ብሏቸዋል፡፡ ቀጥሎም በዮናስ ስብከት ንስሐ የገቡትን የነነዌ ሰዎችን እና በጆሮዋ የሰማችውን የሰሎሞንን ጥበብ በዓይኗ ለማየት በእምነት ወደ ኢየሩሳሌም የገሰገሰችው የኢትዮጵያ ንግሥት /ንግሥት ሳባን/ በዚህ ትውልድ ላይ ይፈርዱበታል ብሏቸዋል፡፡ ምክንያቱም እነዚያ በዮናስ ስብከት እና በሰሎሞን ጥበብ አምነዋል፡፡ እነዚህ ግን የዮናስ እና የሰሎሞን ፈጣሪ ቢያስተምራቸው አላመኑምና ነው፡፡

 

የባሰ ነገር እንደሚያጋጥማቸው ሲናገር መንፈስ ርኩስ ሰይጣን በጠበል በጸሎት ከሰው ከተለየ በኋላ ተመልሶ ይመጣል፣ ጸሎቱን ጠበሉን ትቶ ባገኘውም ሰው ላይ ከእሱ የከፉ ሰባት አጋንንትን ይዞ ያድርባቸዋል፡፡ “ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል” ብሏቸዋል፡፡

 

በመጨረሻም ጉባኤ እንዲፈታ የሚወድ ይሁዳ እናትህ እና ወንድሞችህ በውጭ ቆመዋል አለው፡፡ ጌታችንም ለነገረው “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማናቸው?” ሲል መለሰለት፡፡ ወንድሞች የተባሉት አብረውት ያደጉት የዮሴፍ ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህም የእመቤታችን አገልጋይና ጠባቂ አረጋዊው ዮሴፍ ከሞተችው ሚስቱ የወለዳቸው ናቸው፡፡ ይህም፡-

1ኛ/ ከእናት ከአባት ክብር የእግዚአብሔር ክብር እንደሚበልጥ፣

2ኛ/ ከጉባኤ መካከል ጉባኤ አቋርጦ መነሣት እንደማይገባቸው ሲያስተምራቸው ነው፡፡