‹‹የሚሰማኝ ግን በተስፋ ይኖራል፤ ከክፉም ሁሉ ያለድንጋጤ ያርፋል›› (ምሳ.፩፥፴፫)

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

የእስራኤል ንጉሥ ጠቢቡ ሰሎሞን በግዛቱ ዘመን ለሕዝቡ በምሳሌ ቃሌን ስሙ እያለ በተደጋጋሚ ይናገር ነበር። ነገር ግን የእርሱን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃልን መስማት ደግሞ ጥበበኛ ያደርጋል፤ ተስፋን ያለመልማል፤ ከክፉም ይታደጋል። ስለዚህ ‹‹ቃሌን የሚሰማ ግን በተስፋ ይኖራል፤ ከክፉም ሁሉ ያለድንጋጤ ያርፋል›› በማለት ያስረዳናል። በዚህ ኃይለ ቃል የእግዚአብሔርን ቃል መስማት፣ በተስፋ መኖርና ከክፉ መዳን የሚሉ መሠረታዊ ነጥቦችን እናገኛለን፤ እያንዳንዳቸውን እንመልከታቸው። (ምሳ.፩፥፴፫)

የእግዚአብሔርን ቃል መስማት

እግዚአብሔር አስቀድሞ መስማት እንድንችል ጆሮ፣ እንድናስተውል አእምሮ፣ የሰማነውን ደግሞ በተግባር ማዋል የሚያስችል አቅም ፈጥሮልናል። መቼም ቢሆን እኛ የማንችለውን አላዘዘንም፤ አያዘንምም። ነገር ግን የምንችለውን ባለማድረጋችን ሁሌም ስንጎዳ እንኖራለን። አዳም የእግዚአብሔርን ቃል ባለመስማት ተጎዳ፤ በርካታ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ባለመስማት ተጎዱ፣ ሰብአ ትካትን፣ ሰብአ ሰዶምን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በአንጻሩ የእግዚአብሔርን ቃል የሰሙት የነነዌ ሰዎች ደግሞ ከመጣባቸው መዓት ድነዋል። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ማለት አድርጉ የተባልነውን ማድረግ፣ አታድርጉ የተባልነውን ደግሞ አለማድረግ ነው፤ ቃሉ ሕይወት ነውና።ወንጌላዊው ዮሐንስ በመልእክቱ ‹‹ንዜንወክሙ በእንተ ውእቱ ዘሀሎ እምቅድም ውእቱ ዘሰማዕናሁ በእዘኒነ ወዘርኢናሁ በአዕይንቲነ ወዘጠየቅናሁ ወዘገሠሣሁ እደዊነ በእንተ ነገረ ሕይወት፤ ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና የሰማነውን በዓይናችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን  እናወራለን›› በማለት ስሙት የተባልነው ቃል የሕይወት ቃል እንደሆነ ጽፎልናል፡፡ (፩ዮሐ.፩፥፩)

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በጾመ ድጓ ድርሰቱ ‹‹ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኵሉ ዘየሐዩ በቃሉ፤ ከላይ ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፤  ሁሉን በቃሉ የሚያድነውን  ጌታ ምንም አላወቁትም›› (ጾመ ድጓ፣ ዘዘወረደ)  በማለት ስሙት የተባልነው ቃል መድኃኒት መሆኑን፤ መድኃኒት የሆነው ቃል ደግሞ በቦታ የማይወሰን አምላክ ሲሆን ልዕልናውን ለመግለጽ ከላይ የወረደውን ተብሎ የተነገረለት የሕይወት ቃል መሆኑን ያስረዳናል። ይህን ከላይ የወረደውን አምላክ አይሁድ የሰቀሉት፣ የሁሉ ጌታ፣ በቃሉ የሚያድን እነርሱ ግን ያላወቁት አምላክ እንደሆነ ሊቁ ያስረዳናል። ስለዚህ ይህን ቃል መስማት በተስፋ ያኖራል በማለት ጠቢቡ ሰሎሞን ይነግረናል።

በተስፋ መኖር

ተስፋ በክርስትና ሕይወት መሠረታዊው ጉዳይ ነው፡፡ ሰው በሚያየውና በሚጨብጠው ነገር ቢተማመን ምንም የሚያስደንቅ ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን በሥጋዊ ዐይን የማያዩትን፣ በሥጋዊ እጅ የማይዳስሱትንና የማይጨብጡትን አምላክ የፈለግሁትን ይሰጠኛል፤ የሚጠቅመኝን ያደርግልኛል ብሎ ማመን እጅግ የሚደንቅ ነገር ነው፡፡ ስለሆነም በሃይማኖት ስንኖር ዋናው እና ትልቁ መሣሪያችን ተስፋ ነው፡፡ ሃይማኖት ፈጣሬ ሰማያት ወምድር የሆነውን እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ ነው የተባለውም ለዚህም ነው፡፡

ሰው ከሞተ በኋላ በእግዚአብሔር በሕይወት እንደሚኖር ባለመጠራጠር ማመን ተስፋ መንግሥተ ሰማይ ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ እንደተነሣ ካመንን እንዲሁ እግዚአብሔር ሙታንን በኢየሱስ ያስነሣቸዋል፤ ከእርሱም ጋር ያመጣቸዋል›› በማለት እንዳስረዳን በሥጋዊ ዐይናችን ሳናይ ሰምተን ብቻ የተቀበልነው ሃይማኖት ነው፡፡ (፩ኛተሰ. ፬፥፲፬)

መንግሥተ ሰማያት እንዳለች፣ እንደምንወርሳት፣ በደስታ እንደምንኖርባት፣ ከአወቅን በኋላ እንደማናጣትም አምነን የተቀበልነው ለመንግሥተ ሰማያትን የምታበቃውን ርትዕት የሆነችውን ሃይማኖት አጽንተን በእግዚአብሔርም ቸርነት እንወርሳታለን የሚለው ሙሉ ተስፋ ስላለን ነው፡፡

ደግሞም ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹እምነትስ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የምታረጋግጥ፣ የማናየውንም ነገር የምታስረዳ ናት›› ብሎ እንደነገረን ተስፋ የምናደርገው ነገር አለ፤ እርሱም መንግሥተ ሰማያት ነው፡፡ ይህን ተስፋ የምናደርገውን ነገር ደግሞ በእምነት እንወርሳለን፡፡ በሃይማኖት ጸንተን በጎ ምግባር ሠርተን ስንኖር ያን ተስፋ ያደረግነውን ርስት ሊያወርሰን እርሱ የታመነ አምላክ ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው›› በማለት ያስረዳናል፡፡ (ዕብ.፲፩፥፩፤ ፩ቆሮ.፩፥፱)

ከጥንት ጀምሮ ቅዱሳን አበው እና ቅዱሳን ነቢያት የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት መከራ የተቀበሉት የማይቀር፣ የማያሳፍር ተስፋ ስለነበራቸው ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲገልጽ ‹‹እነርሱ በእምነት ተጋደሉ፤ ነገሥታትን ድል ነሡ፤ ጽድቅን አደረጉ፤ ተስፋቸውን አገኙ፤ የአናብስትን አፍ ዘጉ›› ሲል ያስረዳል፡፡ እነርሱም የተጋደሉት በእምነት ነው፤ ተጋድለውም ነገሥታትን ድል አደረጉ፤ ይጠባበቁት የነበረውን ተስፋም አገኙ፡፡ ተስፋቸው ደግሞ ድኅነት ነው፤ ርስተ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ነውና፤ ይህም ሆነላቸው፡፡ (ዕብ.፲፩፥፴፫)

እግዚአብሔር አምላካችን መቼም ቢሆን ተስፋችንን አያሳጣንም፡፡ ነገር ግን ተስፋ የምናደርገው ነገር ለእኛ የሚያስፈልገን መሆን አለበት፤ የሚጎዳንን አይሰጠንምና፡፡ ‹‹በእርሱም አማካኝነት ወደቆምንበት ወደ ጸጋው በእምነት ተመራን፤ በእግዚአብሔርም ክብር ተስፋ እንመካለን፡፡ የምንመካ በእርሷ ብቻ አይደለም፤ በመከራችን ደግሞ እንመካለን እንጂ፤ መከራ በእኛ ላይ ትዕግሥትን እንደሚያመጣ እናውቃለንና፡፡ ትዕግሥትም መከራ ነው፤ በመከራ ተስፋ ይገኛል፡፡ ተስፋም አያሳፍርም፤ በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን መልቷልና››  በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላከው መልእክቱ ይነግረናል፡፡ (ሮሜ.፭፥፪-፭)

ተስፋ የሚታየውን በማይታየው ይቀይራል፡፡ አብርሃም በሽምግልና ዘመኑ ያገኘውን አንድ ልጁን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው በዐይነ ሥጋ ሳይሆን በዐይነ ኅሊና የሚታይ የተሻለ ጥቅም ስለነበረው ነው፡፡ በመጽሐፍ ‹‹አብርሃምም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ ልጁን ይስሐቅን ይሠዋው ዘንድ በእምነት ወሰደው፡፡ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል ብሎ ተስፋ ያደረገለትን አንድ ልጁን አቀረበው፡፡ እግዚአብሔር ከሙታን ለይቶ ሊያስነሣው እንደሚችል አምኗልና፤ ስለዚህም ያው የተሰጠው መታሰቢያ ሆነለት›› ተብሎ የተነገረው ለዚህ ነው፡፡ አብርሃም የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ በተስፋም ከሚያውቀው ሀገር፣ ከሚያውቀው ሕዝብ ወጥቶ ወደማያውቀው ሀገር፣ ወደማያውቀው ሕዝብ ሄደ። (ዕብ.፲፩፥፲፯-፲፱፤ ዘፍ.፲፪፥፩)

በሰው ሰውኛው ሲታይ አብርሃም የፈጸመው ትክክል አይደለም ሊባል ይችላል፡፡ ምክንያቱም ‹‹በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል›› እየተባለ ያንኑ የዘሩ መጠሪያ የሆነውን ሠዋው ሲባል እሺ ብሎ መሄድ ምን ያህል እምነትና ጽኑዕ ተስፋ እንዳለ የሚያስረዳ ነው፡፡ አብርሃም አንድ ልጁን ለእግዚአብሔር አልከለከለውም፤ እንዲሁ እግዚአብሔርም አንድያ ልጁን ለአብርሃም አልከለከለውም፡፡ እንኳን ለአብርሃም በእምነት ለታዘዘው ለጠላቶቹ እንኳን አልከለከላቸውም፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት በእንደዚህ ያለ ጽኑዕ ተስፋ ያኖራል፤ በተስፋ መኖር ብቻም ሳይሆን ከክፉ ሁሉ ያለ ድንጋጤ ያሳርፋል።

ከክፉ ማረፍ

የእግዚአብሔርን ቃል ያልሰማው አዳም ልጅነትን አጣ፤ ከገነት ወጣ፤ ከገዢነት ወደተገዢነት ወረደ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ያልሰማው ቃየልም እንዲሁ ተቅበዝባዥ ሆነ። በአምላኩ በእግዚአብሔር ቃል እየተጠራ የንስሓ ጊዜ ቢሰጠው ይህን እድል አልጠቀምም፤ የሕይወትን ቃል አልሰማም ያለው ቃየል የሚቅበቀዘበዝ፣ ሰላሙን የተነጠቀ ፈሪ ሆነ። የእግዚአብሔርን ቃል ቢሰማ ግን ከእንደዚህ ያለው ክፉ ሕይወት ይድን ነበር።

የእግዚአብሔርን ቃል የሰማው ነቢዩ ዳዊት ምንም እንኳን የጎልማሳ ሚስት ቢቀማም ጎልማሳ ቢያስገድልም በንስሓ መመለሱ ዛሬም የንስሓ ሕይወቱ ለእኛ በአብነት ሲጠቀስ ይኖራል። የእግዚአብሔርን ቃል ባልሰማበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቶ ነበር። የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰማና በንስሓ ሲመለስ ግን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቀ፤ ኃጢያቱን ይቅር ተባለ፤ ሀብተ ጸጋው ሁሉ ተመለሰለት።

ነቢዩ ኢሳይያስ የእግዚአብሔርን ቃል ባልሰማበት ወቅት ሀብተ ትንቢቱ ተነሳው፤ ለምጽ ወጣበት፤ የእግዚአብሔርን ቃል በሰማ ጊዜ ግን ሀብተ ትንቢቱ ተመለሰለት፤ ኃጢያቱ ይቅር ተባለለት፤ ከለምጹም ነጻ። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት በተስፋ እንድንኖር ያደርገናል፤ ከክፉም እንድናለን። በሐዲስ ኪዳንም የእግዚአብሔርን ቃል የሰሙት ሐዋርያት እሳቱን እና ስለቱን ታግሠው ለበለጠ ክብር በቅተዋል። ከመካከላቸው የእግዚአብሔርን ቃል ያልሰማው ይሁዳ ግን ተለይቷል፤ አልሰማም ማለት በእዝነ ሥጋው አልሰማም ማለት አይደለም፤ በእዝነ ልቡናው ግን በእርግጥም አልሰማም። ስለዚህ ምንም እንኳን ከሐዋርያት ጋር ቢቆጠርም፣ ትምህርቱ፣ ተአምራቱ ባይነፈገውም ክብር ግን አላገኘም።  የእግዚአብሔርን ቃል በአግባቡ አልሰማምና። (ኢሳ.፮፥፩-፲)

በዘመናችንም ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ስለማይሰማ ሥጋዊ መፍትሔው ብቻ ይታየዋል። በእርግጥ ያም የሚገኘው በእግዚአብሔር ነው። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የሥጋም የነፍስም ድኅነት እንደሆነ አለመቀበል በብዙኃኑ ዘንድ ይስተዋላል። ይህ የሆነው ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል ካለመስማት ነው። ሥጋዊ ዕውቀትን ብቻ ተምሮ ያደገ ሰው ሁሌም የሚታየው ሥጋዊ ድሎት ነው፤ ‹‹በቃልህ እዘዝ፤ ልጄ ይድናል›› ያለው የመቶ አለቃው ቃል ትዝም አይለው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ባለመስማቱም በመጨነቅ፣ በመሸበር፣ ለውጥ የማያመጣ መፍትሔ ሲያፈላልግ ዘመኑን በከንቱ ይጨርሳል። (ማቴ. ፰፥፰)

የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ቃሉን በትክክል ሰምቶ በተግባር ላይ ማዋል በመሆኑ ሐዋርያው ያዕቆብ ‹‹ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን ሰምቶ የማያደርገው ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስታዋት እንደሚያይ ሰው ይመስላል። ራሱንም ተረድቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም እንዴት እንደሆነ ይረሳል›› በማለት እንደነገረን ቃሉን ሰምቶ በሕይወት መተርጎም ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ሕይወት ነው፤ በተስፋ ያኖራል፤ ከክፉም ያለምንም ድንጋጤ ያድናል። ከእግዚአብሔር ቃል የራቀ ሁሌም የሚታየው ሥጋዊ መፍትሔ ስለሆነ ይህ ደግሞ ዘላቂ ባለመሆኑ ሁሌም በመጨነቅ፣ በመሸበር ዘመኑን ያሳልፋል። የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ ግን በተስፋ ይኖራል፤ ከክፉም ይድናል። የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተን፣ በጽኑዕ ተስፋ ተሞልተን፣ የተረጋጋ ኑሮን ኖረን ከክፉ እንድንድን እግዚአብሔር ይርዳን፤አሜን።  (ያዕ. ፩፥፳፪-፳፬)