libraries

የመጻሕፍት ማሰባሰቢያ ሳምንት ተዘጋጀ

ግንቦት 23 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

libraries“አንድ መጽሐፍ ትውልድን ለመቅረጽ” በሚል መሪ ቃል በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል አስተባባሪነት የማኅበሩን ቤተ መጻሕት በዘመናዊ ሁኔታ ማደራጀትና ክምችቱን ለማሳደግ፤ እንዲሁም ታላቅ የመረጃ ማእከል ለማድረግ ከሰኔ 1 እስከ 22 ቀን 2005 ዓ.ም. የሚቆይ የመጻሕፍት፤ የኮምፒዩተርና የመዛግብት ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እንደተዘጋጀ የጥናትና ምርምር ማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰይፈ አበበ ገለጹ፡፡

ቤተ መጻሕፍቱ ከማኅበሩ አባላትና ምእመናን በተለገሱ ጥቂት መጻሕፍት በ1998 ዓ.ም. በአነስተኛ መጠለያ /ኮንቴነር/ ውስጥ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን፤ በወቅቱም የማኅበሩን አገልግሎትና ጥረት የተረዱት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ የነበሯቸውን 400 መጻሕፍት በመለገስ እንዲጠናከር የበኩላቸውን ድርሻ መወጣታቸውንና በአሁኑ ወቅት 5000 የሚደርሱ የታተሙ ቅጂ /Hard copy/፤ 1100 ያልታተሙ ቅጂ /Soft copy/ እና 10 የሚደርሱ የተለያዩ የብራና መዛግብት የመረጃ ክምችት ቤተ መጻሕፍቱ እንዳለው አቶ ሰይፈ አበበ ገልጸዋል፡፡

ዓላማውን አሰመልከቶ ሲገልጹም “ማኅበሩ ቤተ መጻሕፍቱን በማጠናከር ዘመናዊ በማድረግ መጻሕፍት፤ ቤተ መዛግብትና ቋሚ ዐውደ ርዕይ /ሙዚየም/ ማቋቋም፤ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ መልክ የሚገኙ የመረጃ ምንጮችን ማሰባሰብ፤ ማደራጀትና ለምእመናንና ለተመራማሪዎች አገልግሎት መስጠት ነው” ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በልዩ በልዩ ቦታዎች /በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር/ የሚገኙ ከመሰል ቤተ መጻሕፍት ቤተ መዛግብት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ጠቋሚ /ዳይሬክቶሪ/ ማዘጋጀት ከዓላማዎቹ መካከል አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ቤተ መጻሕፍቱ ወደፊት በዘመናዊ መልኩ በማደራጀት የE- Library አገልግሎት መጀመር፤ የመረጃ ክምችቱን በ40 ሺሕ ማሳደግና በሶፍትዌር ማደራጀት፤ የዲጂታል ቤተ መጻሕፍት ማቋቋምና የዲጂታላይዜሽን ሥራ ለማከናወን ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ  አክለው ገልጸዋል፡፡

ከአገር ውስጥ ማእከላት 10 ሺሕ፤ ከውጪ ማእከላት 10 ሺሕ፤ ከአባላትና ምእመናን 20 ሺህ የተለያዩ መጻሕፍት የሚጠበቅ ሲሆን መዛግብት በታተመ ቅጂ /Hard copy/፤ ባልታተመ ቅጂ /Soft copy/ በስጦታ መስጠት፤ ኮምፒዩተር፤ ስካነር፤ ፎቶ ኮፒ፤ ወዘተ . . . ቁሳቁሶችንና መጻሕፍትን ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ በመለገስ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የጥናትና ምርምር ማእከል ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ ሰይፈ አበበ አሳስበዋል፡፡