Timketal8n.jpg

የመርካቶ ሌላኛዉ መልክ

በአልታየ ገበየሁ
Timketal8n.jpg

Timketal6n.jpgመርካቶ የሚለውን ቃል እዚህ ጋር ስናነብ መቼም በየሕሊናችን የሚመጡ ብዙ የመርካቶ ሥዕሎች ይኖራሉ ፡፡ በተለይ ግርግሩ፣ ማጭበርበሩ፣ ሌብነቱ፣ በቀላሉ የማይገታዉ አመጹ፣ ምንም ነገር ፈልጎ የማይታጣበት መሆኑ፣ ቆሻሻው….በነዚህ ሁሉ ነገሮች እንደ መርካቶ ቅድሚያዉን የሚይዝ አካባቢ የሚኖር አይመስለኝም፡፡

Timketn.jpgዛሬ የመርካቶን ሌላኛውን መልክ እንይ፡፡ በመርካቶ ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ ነጋዴዎች እና ወጣቶች በደንብ ከሚታወቁባቸዉ  ነገሮች መካከል አንዱ መንፈሳዊ አገልግሎታቸው ነዉ፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ሙሉ ቤተ ክርስቲያን የሚያሠሩ፣ ነዳያንን የሚያበሉ፣ የሚያለብሱ፣ በየዓመት በዓሉ የተቸገሩ ወገኖቻችን ከሌላው ወገናቸው ባልተናነሰ መንገድ በዓሉን እንዲያከብሩ በገንዘብ እና ለበዓላት በሚያስፈልጉ ነገሮች የሚረዱ በትክክል ገንዘባቸው ከየት እንደተገኘ የተረዱ ወገኖችን የያዘ አከባቢ መርካቶ ነው፡፡

Timketal7n.jpgመርካቶ ለሀገሪቷ ኢኮኖሚ ዋልታ አንዱ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ለቤተ ክርስቲያንም ትልቅ የገንዘብ እና የሰው ኀይል ምንጭ እንደሆነ ቤተ ክርስቲያኒቷ ምን ያህል እንደተገነዘበች እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በአራቱም ማዕዘን የሚገኙ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ሕልውና እንዳይጠፋና በነዚሁ አከባቢ ለሚኖሩ ምዕመናን ተስፋ በመሆን እያገለገሉ ያሉ የቤተ ክርስቲያን አለኝታ የሆኑ የክርስቲያን ወገኖችን የያዘ ቦታ መርካቶ ነው፡፡

የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል ደግሞ እንዴት አድምቀው እንደሚያከብሩት ገንዘባቸውን እና ጉልበታቸውን እንዴት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንደሚያውሉት ያሳዩበትን ታላቅ ሥርዓት እንይ፡፡

Timketal5n.jpgየመርካቶ መሬት ወትሮ ከሚታወቅበት ቆሻሻነት ጸድቶ  እሱም  እንደ አዲስ ክርስቲያን ተጠምቆ በቄጠማ፣ በምንጣፍ አምሮበት ለሚያይ የወትሮው መርካቶ ነው ብሎ ለማመን በጣም ያስቸግራል፡፡ አየሩ በዕጣን መዓዛ ተሞልቶ፣ በመዝሙርና ዕልልታ ደምቆ ልዩ ልዩ ቀለማት ባሏቸው ፊኛዎችና ጥቅሶች ተውቦ ለሚያየው እውነት ይህ መርካቶ ነው ብሎ እንዲጠይቅ ያደርገዋል፡፡

በየአደባባዩና በየቦታዉ ድንኳን ተጥሎ ‹‹ካልባረክ¤ኝ አልለቅህም›› የሚለው የአባታችን የያዕቆብ የእምነት ቃል ተሰቅሎበት ምዕመናን የእግዚአብሔርን በረከት የሚጠብቁበት ብዙ ማረፊያ ቦታ ያለበት የጥምቀት በዓል በመርካቶ ነው የሚገኘዉ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ምዕመናን ጠበል ጸዲቅ አዘጋጅተው ለበዓሉ ታዳሚ ያደሉበት መስተንግዶ፣ በዓሉን የንግድ በዓል ለማድረግ የሚጥሩትን አንዳንድ ነጋዴዎችንም የተከላከሉበት ሥርዓት ማስከበር በመርካቶው የበዓል አከባበር ላይ የታየ አንዱ ውበት ነበር፡፡

Timketal4n.jpgወጣቶች በልዩ ልዩ ቲሸርቶችና ጥቅሶች ደምቀው ቄጠማ በመጎዝጎዝ፣ ርዝመቱ በውል የማይታወቀውን ምንጣፍ በመጠቅለል እና በመዘርጋት ታቦታቱን ያከበሩ ካህናት በባዶ አስፓልት ላይ እንዳይራመዱ የሚፋጠኑትን ወጣቶች ስናይ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ሳናደንቅ አናልፍም፡፡

መቼም ከኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት የወጡ እና በሌላ እምነት ስር ያሉ ወጣቶች ክርስቲያን ባለመሆናቸዉ ወይም በመውጣታቸዉ የሚቆጩበት ቀን ብትኖር የዛሬዋ የጥምቀት በዓል ናት የሚል እምነት አለኝ፡፡

ለወትሮ መርካቶ ውስጥ ሌባ ሲያባርሩ፣ የተጣሉ ሲያስታርቁ፣ ተራ ሲያስከብሩ የምናያቸው ፖሊሶች እንኳን ሥራ አጥተው ለበዓሉ ሞገስ ሆነው እንደማንኛዉም ምዕመን ታዳሚ ሆነው ነበር የዋሉት፡፡ ፓሊስ መሆናቸው እንኳን የሚታወቀው በለበሱት ዩኒፎርም ነው ማለት ይቻላል፡፡

Timketal2n.jpgታዲያ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች የሚመለከታቸዉ የመንፈሳውያን ማኅበራት ይህንን ጊዜ ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው ልብ ሊሉት ይገባል፡፡ ጌታችን ወደኔ የመጣውን ወደውጭ አላወጣውም ብሏልና እነዚህን ወጣቶች አሳልፈን እንዳንሰጥ የተቀበልነውን አደራ እናስታዉስ፡፡ ስለዚህ ቢታሰብላቸው፡፡