የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ደብረ መድኀኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን

 ታኅሣሥ 9 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ሪፖርታዥ፡-

hawi 01ማኅበረ ቅዱሳን ለአምስተኛ ጊዜ ያዘጋጀው የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በደብረ ዘይት ከተማ ደብረ መድኀኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ከ6000 በላይ ምእመናን በተገኙበት በድምቀት አካሔደ፡፡

ከዋዜማው ጀምሮ መርሐ ግብሩን የተሳካ ለማድረግ የማኅበሩ ሐዊረ ሕይወት አዘጋጅ ኮሚቴ በሚመድበው መሠረት የየክፍሉ አገልጋዮች በአገልግሎት ተጠምደዋል፡፡ መርሐ ግብሩን የተሳካ ለማድረግ ሁሉም ይጣደፋል፤ የጎደለውን ይሞላል. . . ፡፡

ከሌሊቱ 12፡00 ጀምሮ አምስት ኪሎ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ከሚገኘው ከማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ ጀምሮ በተለምዶ ሰባ ደረጃ እስከሚባለው ሠፈር ድረስ ሰባ 1ኛ ደረጃ የሚሆኑ የከፍተኛ አገር አቋራጭ አውቶቡሶች መስመራቸውን ይዘው ተሰልፈው የምእመናንን መምጣት ይጠባበቃሉ፡፡

ከሌሊቱ12፡30 ጀምሮ ምእመናን በማኅበሩ በተወከሉ አስተባባሪዎች አማካይነት መለያ ባጅ እየተረከቡ በተዘጋጀላቸው መኪና ውስጥ በመግባት ጉዞው ተጀመረ፡፡

የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል አባላት ሌሊቱን ለኢንተርኔት የቀጥታ ሥርጭት ቅድመ ዝግጅት ስናደርግ አድረን በተዘጋጀልን መኪና ወደ ደብረ ዘይት አመራን፡፡

hawi 02 2በደብረ ዘይት ደብረ መድኀኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርሰቲያን ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ስንደርስ የሰንበት ትምህርት ቤቱ መዘምራን አውራ ጎዳናው ላይ ወጥተው በዝማሬ ተቀበሉን፡፡ ነጫጭ የሀገር ባሕል አልባሳት የለበሱ የማኅበረ ቅዱሳን ደብረ ዘይት ማእከል አባላት፤ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባላትና ትራፊክ ፖሊሶች በሰልፍ ምእመናንን ይዘው እየመጡ ያሉትን ከፍተኛ አገር አቋራጭ አውቶቡሶችን ቦታ ለማስያዝ ይረባረባሉ፡፡ የደብረ ዘይት የጸሐይ ግለት ለደመናና ነፋሻማ አየር እጇን ሰጥታለች፡፡ የአካባቢው ምእመና ነጫጭ የሀገር ባሕል ልብስና ነጠላ ለብሰው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ይጓዛሉ፡፡ ደብረ ዘይት በጠዋቱ ደምቃለች፡፡

ደብረ መድኀኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ የእለተ ሰንበት ቅዳሴው በመገባደድ ላይ ነበር፡፡ አስቀዳሽ ምእመናንን ላለመረበሽ አንድ ጥግ ይዘን ከተሳለምን በኋላ እቃዎቻችንን ይዘን ወደ ድንኳኑ በመገባት ለቀጥታ ሥርጭት አመቺ ቦታ ነው ባልነው ሥፍ ላይ ሆነን የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎቻችንን አስተካክለን የመርሐ ግብሩን መጀመር መጠባበቅ ጀመርን፡፡

ምእመናን ከመኪናቸው እየወረዱ በአስተባባሪዎች እየታገዙ በተዘጋጀው ድንኳን ውስጥ ቦታቸውን በመያዝ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የደብረ ዘይት ከተማ ምእመናን ጨምሮ ከስድስት ሺሕ ምእመናን በላይ ግቢውን ሞሉት፡፡ ሁሉም ፊት ላይ የደስታ ስሜት ይነበባል፡፡ ስለ ቤተ ክርስቲያን ለመወያየት፤ ቃለ እግዚአብሔር ለመስማት የመጓጓት ስሜት፡፡

ከጠዋቱ 2፡50 ሲሆን ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ማትያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ በጎንደር መንበረ መንግስት መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባዔያት መምህርና የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ፤ መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን የሊቃውንት ጉባኤ አባል፤ የኔታ ሐረገ ወይን የዝዋይ ሐመረ ኖህ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አበምኔት፤ መጋቤ ሐዲስ ደጉ ዓለም ካሳ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት መምህር፤ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ የቅዱስ ጳውሎስ መንሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት መምህርና፤ ሌሎችም አባቶች ወደ ሥፍራው ደረሱ፡፡

ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና በደብሩ ካህናት መርሐ ግብሩ በፀሎተ ወንጌል ተጀመረ፡፡

የእለቱ ምስባክ “ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር ምክር ሰናይት ለኵሉ ዘይገብራ ወስብሐቲሁኒ ይነብር ለዓለም፤ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ለሚያደርጓትም ሁሉ ምክር በጎ ናት፤ ምስጋናውም ለዘለዓለም ይኖራል” መዝ.110፡10

ጸሎተ ወንጌሉ እንደተጠናቀቀ የደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ያሬዳዊ መዝሙር በማቅረብ መርሐ ግብሩ ቀጥሎ በቀሲስ ፋሲል ታደሰ የመጀመሪያውን ክፍል የወንጌል ትምህርት “የእግዚአብሔር መልስ” በሚል ርዕስ ተሰጠ፡፡hawi 02

በትምህርታቸውም “እግዚአብሔር ለጠየቅነው ነገር ሁሉ ጊዜውን ጠብቆ ያከናውንልናል፡፡ እግዚአብሔር ዝም የሚልበት ጊዜ አለው፤ መልስ የሚሰጥበትም ጊዜ አለው፡፡ . . . ከእኛ ሁለት ነገሮች ይጠበቃሉ፡፡ በእምነት ሆነን መጸለይና በትዕግስት እግዚአብሔርን መጠበቅ፡፡” በማለት ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

ከትምህርቱ በኋላ ከተመሠረተ ሃያ ዓመታትን ያስቆጠረውና ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን አንቀጸ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት የጎልማሶች ክፍል፤ እንዲሁም ዘማሪ ዲያቆን ቴዎድሮስ ዮሴፍ መዝሙር አቅርበዋል፡፡

ክፍል ሁለት የወንጌል ትምህርትን በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ በጎንደር መንበረ መንግስት መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባዔያት መምህር “አነ ውእቱ ሕብስተ ሕይወት፤ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” ዮሐ. 6፡32 በሚል ርዕስ አስተምረዋል፡፡

“ጌታችንን ይከተለው ከነበረው አምስት የገበያ ሕዝብ መሐል አንዳንዶቹ ሥጋዊ ምግብን ፍለጋ፣ አንዳንዶቹ ከደዌቸው ለመፈወስ፣ አንዳንዶቹ ትምህርቱን ለመስማት፣አንዳንዶቹ መልኩን ለማየት ሌሎቹ ደግሞ የኦሪትን ሕፀፅ፤ የወንጌልን መብለጥ ሰምተው ይነቅፉት ዘንድ ይከተሉት ነበር፡፡ ለእነዚህ ሁሉ እንደተነገረላቸው ትንቢት ለሁሉም የሚሹትን ይሰጣቸው ነበር፡፡ . . . ልጆቼ ምን ያህል እንጀራ አላችሁ? አላቸው ደቀመዛሙርቱን፡፡ እነሱም አምስት እንጀራ እና ሁለት አሳዎች ብቻ ነው ያለን፡፡ ነገር ግን ይህ ለአምስት ሺሀ ሕዝብ ምን ይበቃልን? አሉት እሱም አንስቶ አመሰገነ አበርክቶም ለሕዝቡ ሰጣቸው፡፡ በሉ ጠገቡም፡፡

… አስራ ሁለት መሶብ ትራፊም አነሱ፡፡ ይህም ሴቶች እና ሕፃናት ሳይቆጠሩ ነው፡፡ ለምን ቢሉ ሲቶች በወንዶች ፊት ስለሚያፍሩ ብዙ በደንብ አንስተው አይበሉም፤ ሕፃናትም ከሚበሉት የሚፈረፍሩት ስለሚበዛ ነው፡፡ … ምስጢሩን ስንመለከት ምግቡን በምሽት ያበረከተበት ምክንያት ጠዋት ቢሆን ሁሉም ቁርሱን በልቶ ስለጠገበ ብዙ ተርፎ ተነሳ እንዳይሉ፣ ሁለተኛው በለምለም ስፍራ ላይ ያስቀመጣቸው ምክንያቱ ልብሳችን እንዳይቆሽሽ ተደላድለን ስላልተቀመጥን ብዙ ስላልበላን ተርፎ ተነሳ እንዳይሉ፣ ሦስተኛው በከተማ ሳይሆን በምድረባዳ ምንም በሌለበት ማድረጉ ምግቡ ሲያንስ ደቀመዛሙርቱ ከከተማ እየገዙ እንጂ አበርክቶት አይደለም እንዳይሉ፣ አራተኛው በጥብርያዶስ ወንዝ አጠገብ ያስቀመጠበት ምክንያት እጃችንን ሳንታጠብ ስለበላን እንጂ ብዙ ተርፎ አይነሳም እንዳይሉ፤ በመጨረሻም እስከ ዛሬ ይከተሉት የነበረው ለመብል መሆኑን ስለተረዳ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” አላቸው፡፡ ከጧት እሰከ ማታ ሳይበሉ መቆየታቸው ጾመው ጸልየው መንግሥቱን ያገኙ ዘንድ ነው፡፡ ሥጋዬ አውነተኛ የሕይወት መብል፤ ደሜም እውነተኛ የሕይወት መጠጥ ነው፡፡ ሥጋዬን ያልበላ፤ ደሜንም ያልጠጣ የዘላለም ሕይወት የለውም ሲላቸው በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ አሠረው” በማለት አስተምረዋል፡፡

ከትምህርት ወንጌሉ በመቀጠል ዘማሪ ዲ/ን እንግዳ ወርቅ በቀለ፤ እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራን መዝሙር በማቅረብ ቀጥሎ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሰባሳቢ አቶ አምሳሉ ደጀኔ የደብረ መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክና እየተከናወኑ ስለሚገኙ የልማት ሥራዎች ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

hawi 05አቶ አምሳሉ ባቀረቡት ሪፖርትም አካባቢው የኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ “በአጥቢያው ከአሥር ሺሕ በላይ ምእመናን የሚገኙበት ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ አምልኮተ እግዚአብሔር ለመፈጸም ባለመቻላችን ምእመናኑን ፊርማ በማሰባሰብ ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመሆን ለማስፈጸም ችለናል፡፡ በዚህም መሠረት የካቲት 3 ቀን 2005 ዓ.ም. በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የመሠርት ድንጋይ ተቀምጦ በሦስት ወራት ውስጥ ተሠርቶ ተጠናቋል፡፡ አሁንም ቤተ ክርስቲያኑ ጠባብ በመሆኑ ወደፊት በተሻለ ሁኔታ ለመሥራት የታሰበ ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመክፈት ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን” በማለት ሪፖርታቸውን አጠናቀዋል፡፡

የከስዓት በፊቱ መርሐ ግብር በማጠናቀቅ የምሳ መርሐ ግብሩ ቀጥሏል፡፡

ከምሳ መልስ የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ክፍል አባላት ያሬዳዊ ወረብ ” ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናቲነ አስተጋብአነ ሀበ ትረፍቅ መካነ፤ እስመ ዝርዋን አግብርቲከ ንህነ፤ በኃጢዓት የተበተን እኛን ሊቀ ካህናችን ክርስቶስ በፍቅር ሰብስበን” በማለት አቅርበዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ ማኅበሩ በዩኒቨርስቲዎችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ እንዲሁም በአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት እያከናወናቸው ስለሚገኙት ተግባራት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

ቀጥሎ የተካሔደው የጥያቄና መልስ መርሐ ግብር ሲሆን ጥያቄዎቹ ከማኅበሩ አባላትና ምእመናን በተለያዩ ጊዜያት ሲጠየቁ የነበሩ ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹንም ለመመለስ ከሊቃውንቱ መካከል መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን የሊቃውንት ጉባኤ አባል፤ መጋቤ ሐዲስ ደጉ ዓለም ካሣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት ትርጓሜ መምህር፤ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ በቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የብሉይና የሐዲስ ትርጓሜ መምህር ሲሆኑ ጥያቄዎቹ በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ አቅራቢነት ተስተናግደዋል፡፡

hawi 03ከጥያቄዎቹ መካከል፡- የኑሮ ውድነት እና ሀብት የማካበት ትኩረታችን ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ጊዜ ከመስጠት እያገደን ስለሆነ ምን እናድርግ? ቅዱስ ጳውሎስ ሀገራችን በሰማይ ነው ስላለ እኛ ክርስቲያኖች በምድራዊት ሀገራችን ላይ እንዴት እንሥራ? ባለትዳሮች ከትዳር አጋራቸው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እና ከሌሎች ቤተሰብ አባላት ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት? ፖለቲካ ኃጢአት ነው? ለሱሰኛ እና ለጠጪ ባንመጸውት ኃጢአት ይሆንብናል ወይ? ንስሐ አባት ለምን ያስፈልጋል? ነፍስን ለፈጠረ እግዚአብሔር በቀጥታ ኃጢአትን መናዘዝ አይቻልም ወይ? ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ከጥያቄና መልሱ በኋላ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳሰ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ባስተላለፉት መልእክት “ሁሉም ነገር የሚሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ለእምነቱ፤ ለሀገሩና ለአንድነቱ የቆመ በመሆኑ ረጅሙን ጉዞ በመጓዝ ወደ ሀገረ ስብከታችን መጥቶ ይህንን መንፈሳዊ ጉባኤ መካፈል በመቻሉ ተደስተናል፡፡ በሊቃውንቱ ቀኑን ሙሉ ሲነገር የዋለው ቃለ እግዚአብሔር በሚገባ ከያዝነውና ወደ ሕይወታችን መለወጥ ከቻልን ቤተ ክርስቲያንና ሀገራችንን የሚጠቅም ሥራ ልንሠራ እንችላለን፡፡ ሁላችንም ሓላፊነታችንን መወጣት አለብን፡፡ ማኅበሩ በሚቀጥለው ጊዜ ሊያዘጋጅ ያሰበው ጉባኤም ከሀገረ ስብከታችን አይወጣም” ብለዋል፡፡

hawi 04ብፁዕ አቡነ ማትያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለ ምእዳንም “እናንተ እድለኞች ናችሁ፡፡ እኔ በእድሜዬ እንዲህ ያለ ጉባኤ አይቼ አላውቅም፡፡ በውጭ ያሉ ወገኖቻችሁ ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ ተከራይተው ነው አገልግሎት የሚያገኙት፡፡ ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብላችሁ በተረጋጋ መንፍስ ሆናችሁ ትማራላችሁ፡፡ ጆሮ ያለው ሁሉ ይስማ፡፡ ቀኑን ሙሉ ቃለ እግዚአብሔር ሲነገር ነው የዋለው፡፡ የተነገረውን ሁሉ የሰማ በሥራ መተርጎም ይጠበቅበታል፡፡ ሁላችንም የሰማነውን ለሌሎች ብናስተላልፈው ብዙ ሥራ ሊሠራ ይችላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን! ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ፡፡ በውጭ ያሉትም በአገልግሎታችሁ ይደሰታሉ፡፡ አንዳንዶች ያልገባቸው ሌላ አድርገው ይተረጉሙት ይሆናል፡፡ ዛሬ የተማርነው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶን አስተምህሮ የተከተለ ትምህርት ነው፡፡ ይህንን የሚቃወሙ ከቤተ ክርስቲያን ተለይተው የወጡ ብቻ ናቸው” በማለት የተናገሩ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳንን፤ የደብሩ ሰበካ ጉባኤንና ምእመናንን አመስግነዋል፡፡

በዚሁ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡