የሊቃውንቱ ምንጭ እንዳይደርቅ ደቀ መዛሙርትን ማፍራት እንደሚገባ ተገለጸ

 

ተመራቂ ደቀ መዛሙርት

ዲ/ን ዘአማኑኤል አንተነህ

     የሊቃውንቱ ምንጭ እንዳይደርቅ ደቀ መዛሙርትን ማፍራት እንደሚገባ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ገለጹ፡፡

ብፁዕነታቸው ይህንን ቃል የተናገሩት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በጎንደር ከተማ የደብረ ኃይል ወደብረ ጥበብ በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የአቋቋም ትምህርት ሲከታተሉ የቆዩ ፶፬ ደቀ መዛሙርት ጥር ፫ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም. ሲያስመርቅ ባስተላለፉት መልእከት ነው፡፡

በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ጨምሮ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ረዳት ሊቀ ጳጳስ የተገኙ ሲሆን፣ደቀ መዛሙርቱ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ እጅ የአቋቋም የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ለደቀ መዛሙርቱ ባስተላለፉት መልእክት “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ! ተመርቃችሁ ስትወጡ ብዙ ነገር ይጠበቅባችኋል፡፡ ጨው ሁናችሁ ዓለሙን የማጣፈጥ ኃላፊነት አለባችሁ” በማለት ተመራቂ ደቀ መዛሙርቱ በተማሩት ትምህርት ወንበር ዘርግተው በማስተማርና ለምእመናን ትምህርተ ወንጌልን በመስጠት በተለይም ለገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን በመድረስ የተጣለባቸውን አደራ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

    ብፁዕነታቸው አያይዘውም “አሁን በዝታችሁ ትታያላችሁ፡፡ነገር ግን በአብያተ ክርስቲያናት ስትከፋፈሉ ቊጥራችሁ አነስተኛ ነው፡፡አሁንም ብዙ መሥራት፣መማር፣ ማስተማር እና የሊቃውንቱ ምንጭ እንዳይደርቅ ደቀ መዛሙርትን ማፍራት ይገባችኋል” ብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በበኩላቸው “ህየንተ አበዊኪ ተወልዱ ለኪ ደቂቅ፣ በአባቶችስ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ” በማለት የቅዱስ ዳዊትን ቃል መነሻ በማድረግ ለደቀ መዛሙርቱ ባስተላለፉት መልእክት “እናንተ ደቀ መዛሙርት የዓለም ብርሃን ናችሁ፣ከዚህ ወጥታችሁ  አብያተ ክርስቲያናትን ሀገራችሁን በቅንነት በተሰጣችሁ አደራ እንድታገለግሉ አደራ እንላለን” ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአቋቋም ምስክር ጉባኤ ቤቱ መምህር መጋቤ አእላፍ ክቡር ጥላሁን ያፈሯቸው ደቀ መዛሙርት የተማሩትን ትምህርት በተግባር ይተረጉሙ ዘንድ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ በመግለጽ “እነዚህ ደቀ መዛሙርት ዛሬ ተመርቀዋል፤ነገር ግን እየለመኑ ተምረው እየለመኑ መኖር የለባቸውም፡፡በርካታ ደቀ መዛሙርት ከትምህርት ገበታቸው የሚሰደዱት ሥራ አላገኝም እያሉ ነውና እንደ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሁሉ ቅዱስ ሲኖዶስ በየቤተ ክርስቲያኑ የሚመደቡበትን መንገድ ቢያመቻች ጥሩ ነው” ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ክቡር መምህር መጋቤ አእላፍ  በጉባኤ ቤቱ የሚታየውን ችግር ሲያስረዱም “ማኀበረ ቅዱሳን ለጉባኤ ቤቱ ዘመናዊ ቤት ሰርቶልናል ነገር ግን አሁንም የሠርከ ኀብስቱ እጥረት አሳሳቢ ስለሆነ ለተማሪው ፍልሰት ምክንያት እየሆነብን ነውና መፍትሄ እንሻለን፡፡ደቀ መዛሙርቱ የሚማሩት ከየሀገራቸው ትንንሽ ልጆችን እያስመጡ ልጆቹ በየመንደሩ በመንቀሳቀስ “በእንተ ስማ ለማርያም”ብለው ምግብ ያመጡላቸዋል፡፡እነሱ ደግሞ እነዚህን ልጆች ያስተምሯቸዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናት ለአብነት ትምህርት ቤቶች ከዚህ በላይ ትኩረት ሰጥታ መሥራት አለባቸው ”ሲሉ ገልጸዋል፡፡

 ማኀበረ ቅዱሳን ለጉባኤ ቤቱ ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ በ፳፻፰ ዓ.ም ሠርቶ ያስረከበ ሲሆን፣ ከሕንፃው በተጨማሪ ለ፶፭ ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው በየወሩ የ፫፻፹፭ ብር ድጋፍ ያደርጋል፤ ቤተ ክህነትም ለ፴ ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው ፹፬ ብር በየወሩ ይደጉማል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ለጉባኤ ቤቱ ያሠራው ሕንፃም ቤተ መጻሕፍት፣ ክሊኒክ፣ የመምህር ቢሮ፣ ምግብ ቤት፣ መማሪያ ክፍልና መኖሪያ ለደቀ መዛሙርቱ ማሟላቱም በደቀ መዛመርቱ የምርቃት መርሐ ግብር ላይ ተገልጿል፡፡

ጉባኤ ቤቱ በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ያፈራ ሲሆን፤ ለአብነት ያህል አለቃ ገብረ ሐና፣መሪጌታ ሐሴት፣መሪጌታ ገብረ ማርያም፣ መሪጌታ ገብረ ዮሐንስ፣ መሪጌታ አሚር እሸቱ፣ መሪጌታ ላቀው፣ መምህር ክፍሌ ወልደ ፃድቅ፣ መጋቤ አእላፍ ሄኖክ ወልደ ሚካኤል እና አሁን በማስተማር ላይ የሚገኙት መጋቤ አእላፍ ክቡር ጥላሁን እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ በጉባኤ ቤቱም ማኅተሙን ለማግኘት ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት ይፈጃል፡፡ በጉባኤ ቤቱ ከ፪፻ ያላነሡ ደቀ መዛሙርት በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በየዓመቱም የደቀመዛሙርቱ ምርቃት አይቋረጥም፡፡

አሁን በማስተማር ላይ የሚገኑኙት መጋቤ አእላፍ ክቡር ጥላሁን ከመጋቤ እእላፍ ሄኖክ ወልደ ሚካኤል በ፲፱፻፺፯ ዓ.ም ወንበሩን በመረከብ እስከ አሁን ድረስ ከ፲፻ በላይ የሚሆኑ የአቋቋም መምህራንን አፍርተዋል፡፡

በብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ እና በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ትምህርተ ወንጌል እና ቃለ ምዕዳን፣ በተጨማሪም በደቀ መዛሙርቱ ቅኔ እና ያሬዳዊ ወረብ ቀርቧል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይም የሀገረ ስብከቱ የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የአብነት መምህራን እና ምእመናንም ተገኝተዋል፡፡