[smartslider3 slider="3"]

የፀረ ተሐድሶ አገልግሎት በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት

ማኅበረ ምእመናን ኦርቶዶክሳዊውን አስተምህሮ በሚገባ እንዲያውቁ የሚያበቃ ትምህርትና ሥልጠና መስጠት፤ በየዐውደ ምሕረቱ የሚቀርበው ትምህርተ ወንጌል በስፋት እንዲቀጥል መደገፍ፤ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ እንዲዳከምና ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ እንዲስፋፋ ማድረግ፤ ሐሰተኞች መምህራንን በመከታተል ከስሕተታቸው እንዲታረሙ መምከር፤ ካልተመለሱም ተወግዘው እንዲለዩ ለቅዱስ ሲኖዶስ ማቅረብ ኮሚቴው ወደፊት ለማከናወን ያቀዳቸው ተግባራት መኾናቸውን ሊቀ ጉባኤ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ጨምረው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በተለይ ራሳቸውን ‹ተሐድሶ› ብለው የሚጠሩ መናፍቃን ማን ይነካናል ብለው በድፍረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እየተሳደቡ፣ አባቶችንም እያጥላሉ እንደ ኾነ፤ የተሳሳተ ትምህርታቸውን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ፤ ቍጥራቸውም በዘመናት ሳይኾን በቀናት እየጨመረ እንደ መጣ ጠቅሰው፣ በሀገረ ስብከቱ የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ የተቋቋመው እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ይህን የመናፍቃኑን እንቅስቃሴ ለመከላከል መኾኑን አብራርተዋል፡፡

የወደቁትን እናንሣ

ጕብኝት ባደረግንበት ወቅት እንዳስተዋልነው በማኅበሩ እየተጦሩ ከሚገኙ ወገኖች መካከል አንዳንዶቹ የአብነት መምህራን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ በመንግሥትና በግል ድርጅቶች ሓላፊነት የነበራቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የቤተ ክርስቲያንና የአገር ባለውለታዎች በሕመም፣ በጤና እና በእርጅና ምክንያት የአልጋ ቁራኛ፣ የደዌ ዳኛ ኾነው ጎዳና ላይ በወደቁበት ወቅት ይህ ማኅበር ደርሶላቸው አስፈላጊውን ዅሉ ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል፡፡ በተለይ የአእምሮ ሕሙማንና ከአንድ በላይ በኾነ የጤና እክል የተጠቁ ማለትም የማየትም የመስማትም የመንቀሳቀስም ችግር ያለባቸውና ሰውነታቸውን መቈጣጠር የማይችሉ አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞችና እኅቶች ኹኔታ ልብን ይነካል፡፡ እነዚህ ወገኖች የሚንቀሳቀሱትም፣ የሚመገቡትም፣ የሚለብሱትም፣ የሚጸዳዱትም በሰው ርዳታ ነው፡፡ እነርሱን ያየ ሰው የማኅበሩን ዓላማ በግልጽ ይረዳዋል የሚል እምነት አለን፡፡

የበረዶ ናዳ በገዳመ ናዳ

የገዳሙ ደን እና ፍራፍሬ በበረዶ ናዳ ቢወድምም ዋና አስተዳዳሪው እና ማኅበረ መነኮሳቱ ብሩህ ፊታቸው አልቀዘቀዘም፡፡ ጉባኤ ቤቱም አልተፈታም፡፡ ገዳማውያኑ በተለመደው መንፈሳዊ ቋንቋ ‹‹እግዚአብሔር ይመስገን! ደኅና ነን … በአትክልት ላይ እንጂ በሰውና በእንስሳት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም … ዅሉም ነገር ለበጎ ነው … ከዚህ የባሰ አያምጣ …›› እያሉ እነርሱን ለመጠየቅና ጉዳን ለማየት የሚመጡ ምእመናንን ያረጋጋሉ፡፡ ገዳማውያን እንዲህ ናቸው፤ ተበድለው እንዳልተበደሉ፤ ተጎድተው እንዳልተጎዱ፤ ተቸግረው እንዳልተቸገሩ በማመን በኾነው ነገር ዅሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፡፡ በዚህ ዓመት በፈለገ ብርሃን ናዳ ማርያም ገዳም እና በአካባቢው በወርኃ ሰኔ የደረሰው ጉዳት እግዚአብሔርን ወደማማረር የሚገፋፋ ከባድ ፈተና ቢኾንም የገዳሙ አባቶች እና እናቶች ግን እግዚአብሔርን ማመስገናቸውን ለቅጽበት አላቋረጡም ነበር፡፡ በስበብ አስባቡ እግዚአብሔርን ና ውረድ የምንል ምእመናን ከእነርሱ ትምህርት ልንወስድ ይገባል፡፡