ዜና ዕረፍት

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት እና የውጪ ግንኙነት መምሪያ የበላይ ኃላፊ እንዲሁም የድሬዳዋና የጅቡቲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፈዋል። ብፁዕነታቸው ለረጅም ጊዜ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሊሻላቸው ባለመቻሉ ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል።

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ከ፲፬ ኤጲስ ቆጶሳት መካከል አንዱ ሆነው ከተሾሙበት ከሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ጀምሮ በአገልግሎት ኖረው በመጋቢት ፲፪፣፳፻፲፭ ዓ.ም እንዳረፉ መዝገበ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

የብፁዕ / አቡነ አረጋዊ የሕይወት ታሪክ

ውልደት

የቀድሞው አባ ኃይለ ማርያም መለሰ የኋላው ብፁዕ አቡነ አረጋዊ (ዶ/ር) ከአባታቸው ከሊቀ መዘምር መለስ አየነው ደስታና ከእናታቸው ከወ/ሮ ፀሐይ ገብረ አብ በሰሜን ጎንደር ደብረ ሰላም ሎዛ ማርያም አካባቢ በ1፲፱፻፷፩ ዓ.ም ተወለዱ።

ትምህርት

 • ፊደል፥ ንባብ፥ ዳዊትና ቅዳሴ ከመርጌታ ሙሴ ብፅዐ ጊዮርጊስ ተምረዋል።
 • ቅኔ፥ ከግጨው መንከር ምንዝሮ ተክለ ሃይማኖት፥ ሐዲሳት፥ ከመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ግምጃ ቤት ማርያም ተምረዋል።
 • አንደኛና ሁለተኛ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዐፄ ፋሲል፡ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በዳግማይ ደብረ ሊባኖስ አዘዞ ተክለ ሃይማኖት ትምህርት ቤቶች ተምረዋል።
 • ከሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ በቴዎሎጂ ዲፕሎማ፥
 • ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በቴዎሎጂ ዲግሪ፥
 • ከኖርዌይ ስታቫንገር ስፔሻላይዝድ ዪኒቨርስቲ የማስተርስ ዲግሪ፥
 • ከፕሪቶርያ ዩኒቨርስቲ በፍልስፍና የፒኤችዲ ዲግሪ አግኝተዋል።

ቋንቋ

 • ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ የኖርዌይ፥ የስዊድንና የዴንማርክ ቋንቋዎችን ይችላሉ፡፡

መዐርገ_ክህነት

 • ዲቁና – በ፲፱፻፷፰ ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ እንድርያስ (ቀዳማዊ) በወቅቱ የሰሜን ጎንደር ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል፥
 • ምንኵስና – በበ፲፱፻፹፬ ዓ.ም. ዓ.ም. በታዋቂውና ጥንታዊው ገዳም ጎንድ ተክለ ሃይማኖት ተቀብለዋል፥
 • ቅስና – ከብፁዕ አቡነ ያዕቆብ (ኤርትራዊ) በወቅቱ የሰሜን ጎንደር ሊቀ ጳጳስ ተቀበለዋል፥
 • ቁምስና – ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል በወቅቱ የምዕራብ ሸዋ ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል።

አገልግሎት

 • በሆለታ ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት፥ በሆለታ ገነት ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል፥ በሆለታ ገነት ደብረ ሣህል መድኃኔ ዓለም፥ በወሊሶ ጻድቁ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አብያተ ክርስቲያናት በአስተዳዳሪነት ሠርተዋል።
 • የወልመራ ወረዳ ቤተ ክህነት ምክትል ሊቀ ካህናት ሆነው በቅንንነት አገልግለዋል።
 • በኖርዌይ ስታሻንገር መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና የሕፃናትና ቤተሰብ መምሪያ የቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን መርተዋል።
 • የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የቦርድ አባል፡ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የቦርድ አባል በመሆን እያገለገሉ አገልግለዋል።
 • በቤተ ከህነት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ሲል በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ኃላፊ፥
 • በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመጀመሪያ የሪሰርችና ምርምር ኃላፊና አካዳሚክ ዲን፥ ም/ዋና ዲን በመሆን አገልግሎት ሰጥተዋል።
 • የቅድስት ልደታ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የቦርድ አባል በመሆንም ሠርተዋል።
 • በዓለም አቀፍ ተሳትፎ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ከርስቲያንን በመወከል የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማእከላዊ ኮሚቴ አባል፥ የመላው ኦርየንታል ኦርቶዶስ አብያተ ከርስቲያናትን በመወከል የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በመሆን ተሳትፈዋል፡፡
 • የመንበረ ፓትርያርከ ጠቅላይ ጽሕፍት ቤት ምክትል ሥራአስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል።

«በጎ ነገር የሆነው ሁሉ ያለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ፍጻሜ ሊያገኝ አይችልም ተብሎ በተጻፈው መሠረት ምንም እንኳን ሁሉም ተመራጮች ቆሞሳት ከዕጩ ተወዳዳሪዎቻቸው ጋር የድምፅ ብልጫ በማግኘት ሊመረጡ የቻሉት በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መሆኑ ቢታመንበትም ቅሉ ቆሞስ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ግን ከእጩ ተወዳዳሪያቸው ጋር እኩል ድምፅ አግኝተው የተመረጠት በዕጣ ስለሆነ በእሳቸው ምርጫ በይበልጥ እደ መንፈስ ቅዱስ እንዳለበት ያሳያል፡፡

የብፁዕ አባታችን በረከታቸው ይደርብን::