ዜና ዕረፍት

መጋቢት ፬፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አበምኔት ታላቁ የጸሎት አባት የኔታ መምህር ሐረገ ወይን ምሕረቱ በእርግና ምክንያት በ፺፱ ዓመታቸው መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፈዋል።ሥርዓተ ቀብራቸውም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም መጋቢት ፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ተፈጽሟል።

የኔታ ሐረገ ወይን በርካታ ጳጳሳትንና ሊቃውንትን አስተምረው ያበቁ የአቋቋሙ ሊቅ ነበሩ። ከአርባ ዓመት በላይ ወንበር ዘርግተው ያስተማሩ፣ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጊዜ ጀምሮ ሁለት ጊዜ ያክል ለጵጵስና ቢጠየቁም “ምንኩስናዬ ይበቃኛል” በማለት በዓታቸውን ያጸኑ ጸሎተኛ አባት እንደነበሩም ተገልጿል።

ወላዴ አእላፍ መምህር የኔታ ሐረገ ወይን ምሕረቱ የሕይወት ታሪክ

ወላዴ አእላፍ መምህር የኔታ ሐረገ ወይን ምሕረቱ በወሎ ክፍለ ሀገር ሰገራት (ኩታበር ወደ ግሸን መሔጃ) ከወላጅ አባታቸው ከአለቃ ምሕረቱ ካሣ ከእናታቸወ ወ/ሮ አበቡ ወልደ ጻድቅ በየካቲት ፲፮ ቀን ፲፱፻፺፮ ዓ.ም ተወለዱ። የፊደልና ንባብ ትምህርት የጀመሩት በእናታቸው ሀገር በቦሩ ሥላሴ ነው። ግብረ ዲቁናን በ፲፱፻፭ ዓ.ም ከግብጻዊው አቡነ ቄርሎስ በአዲስ አበባ ቅድስት ማርያም ገዳም ተቀበሉ። ጸዋትወ ዜማ፣ ዳውንት፣ ምዕራፍ፣ ጾመ ድጓን የኔታ ሐረገ ወይን ቦሩ በድጋሚ ተመልሰው ተማሩ እርሳቸው እንደተናገሩት “ቦሩ እያለን አንድ ጓደኛችን ቅኔ ተቀኝቶ መጣ እኛም በቅንዓት ወደ ቅኔ ገባን” በማለት ገልጸው ነበረ፡፡

መምህራቸው ወደ ግሸን ሲሄዱ ተነስተው ደላንታ ጉርባ ጊዮርጊስ ከየኔታ ብሩ ድጋሚ ሙሉ ቅኔ ከነአገባቡ ተምረዋል ። የአቋቋም ትምህርት በጋይንት አንሳሳ ጊዮርጊስ የኔታ የማነ ብርሃን ክብረ በዓል እስከ አስተርእዮ ተማሩ። መምህሩ ወደ አማራ ሳይንት ሲሄዱ እርሳቸው በዚያው በመቅረት “አለቃ ታደሰ የሚባሉ መምህር መጡልን ሙሉ ክብረ በዓል አዘለቁን” ሲሉ ወላዴ አእላፍ መምህር የኔታ ሐረገ ወይን ገልጸዋል።ጋይንት ልዳ ጊዮርጊስ በየኔታ ዓለሙ መዝሙሩን፣ ዝማሜና ማንሻውን፤ በበጌ ምድር መድኃኔ ዓለም በየኔታ አለልኝ መዝሙር፣ የመንና መረግዱን እንዲሁም ጽፈቱን ተምረዋል።

የኔታ ስለ አብነት ትምህርታቸው ሲተርኩ “ወገራ ቅዱስ ሚካኤል ሄድን ረሀብ ነበረ ተማሪ ተበትኖ ስለአገኘነው ወደ በለሳ ላኩን፡፡ በለሳ መድኃኔ ዓለም የኔታ አፈ ወርቅ የጎንደር ማርያም አለቃ ናቸው:: ከእኚህ ሊቅ መዝሙርና ክብረ በዓል ከለስን፣ በዞዝ አምባ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከየኔታ እፁብ ክብረ በዓል፣ ወርሃ በዓል መዝሙር ከነዓመሉ የወሰንነው እዛው ነው። (አንድ ደቀ መዝሙር ወደ ምስክር ከመሔዱ በፊት የወሰነ ከሆነ አድራሽ ይባላል አድራሽ የሆንነው እዛው ነው) ” በማለት ይነገሩ ነበር።

የኔታ ትምህርታቸውን ቀጥለው ድምጫ ላይ ቤት፣ ታች ቤት፣ ሳንኳ ፊት ሚካኤል ወይም አደባባይ ኢየሱስ /በዓታ/ቂርቆስ እስከ ሦስት ዓመት አጠናክረዋል። ስለ መምህርነት ሕይወታቸው ሲናገሩ “የኔታ እፁብ መረቁኝ አስተምር ብለው ፈቀዱልኝ የመጀመሪያ የማስተማር ጊዜ በጎንደር ክፍለ ሀገር በበለሳ በታች አባሽካ ጊዮርጊስ በ፲፱፻፵ ማስተማር ጀመርኩ። ሰባት ዓመት አስተማርኩ፡፡ በመቀጠልም በጣራሽ ማርያም ስምንት ዓመት አስተምሬ ቤተሰብ ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። እዚሁ ተቀመጥ አሉኝ አክስቴ ባይሆን ተማሪዎቼን አሰናብቼ እኔም ተሰናብቼ ልምጣ ብዬ ተመልሼ ሂጄ ተማሪዎቼን ሸኝቼ ተመለስኩ” በማለት ወደ አዲስ አበባ የመጡበትን አጋጣሚ ይተርካሉ።

አዲስ አበባ እንደመጡ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ተቀጠሩ ከዚያም ኮልፌ ትምህርት ቤት በመግባት ሰባት ዓመት ሐዲስ ኪዳን ተማሩ፣ በዘመናዊ ትምህርትም እስከ ዘጠነኛ ክፍል ዘልቀዋል፡፡

ታላቁ አባት የኔታ ሐረገ ወይን ምሕረቱ በኤሊባቡር የሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ኃላፊና አቡነ ቀሲስ የሊቀ ጳጳሱ እንደ ራሴ ሆነው ለሁለት ዓመት አገልግሎት ሰጥተዋል ። ቤተ ክህነቱ ጋሞ ጎፋ ጅንካ መድቧቸው ወደ ጋሞ ጎፋ በመሄድ አቡነ ሰላማ ዘንድ የሀገረ ስብከቱ ትምህርት ክፍል ሰባኬ ወንጌል ሆነው ዐሥር ዓመት አገልግለዋል ።

አርባ ምንጭ እያሉ ብፁዕ አቡነ ሰላማ ወደ ደብረ ሊባኖስ ልከዋቸው በደብረ ሊባኖስ ገዳም መንኩስናን ተቀብለዋል። የታላቁ አባት የኔታ ሐረገ ወይን ምሕረቱ በአዲስ አበባ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጸሐፊ ሆነው አንድ ዓመት ሠርተዋል። የመንበረ ፓትርያርክ የጊቢ ኃላፊ በመሆን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጊዜ አራት ዓመት አገልግሎት ተሰጥተዋል። ወደ ኬንያ ናይሮቢ በማቅናት በመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊ ሆነው ከብፁዕ አቡነ ኤልያስ ጋር ሠርተዋል። ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ወደ ጅቡቲ ሲሄዱ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ሆነው አንድ ዓመት አገልግለዋል ።

የኔታ ሐረገ ወይን ምሕረቱ ወደ ዝዋይ ያቀኑበትን አጋጣሚ ሲገልጹ “አቡነ ጎርጎርዮስ አገኙኝ ሹመት ይፈልጋሉ ወይ አሉኝ? እኔም ኧረ አልፈልግም መምህራችን ሹመት የሚባል ነገር እንዳትፈልጉ ብለውኛል አልኳቸው፡፡ ማስተማር የሚፈልጉ ከሆነ ዝዋይ እንሂድ ብለውኝ በ፲፱፻፹ ዓ.ም ወደ ገዳሙ ገባሁ በማለት ገልጸዋል። ይህንን የሕይወት ታሪካቸውን የከተቡት አባ አትናቴዎስ ወልደ ጎርጎርዮስ እንደገለጹት የኔታ ወደ ዝዋይ ገዳም ከመጡ ጀምሮ ወዴትም አልሔዱም፣ የገዳሙ በረከት ናቸው። በዝዋይ ገዳም ብቻ በዓት አጽንተው ፴፭ ዓመት አስተምረዋል።

በረከታቸው ይደርብን!