የብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የሕይወት ታሪክ

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በክልል ትግራይ በማዕከላዊ ዞን በዓድዋ ወረዳ ልዩ ስሙ የሐ ደብረ ሐመልማል (መዝብር) በተባለው ቀበሌ ሚያዝያ ፳ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ከአባታቸው ከአለቃ ኃይሉ ወልደ ማርያምና ከእናታቸው እመት ዘነበች ወልደ ማርያም ተወለዱ፡፡

ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ ከአጎታቸው ከቄስ ገብረ ሕይወት ወልደ ማርያም ትምህርት ጀምረው ትምህርቱ እየገባቸው ሲሄድ ወላጆቻቸው መሪጌታ ተክለ ጊዮርጊስ ከሚባሉ መምህር አስገብተዋቸው ንባብና የቃል ትምህርት በማጠናቀቅ የግብረ ዲቁናን ትምህርት ተማሩ፡፡

ሆኖም የትምህርት ፍላጐታቸው እየተጠናከረ በመሄዱ የፈለጉትን ትምህርት ለመከታተል ከትውልድ አገራቸው ወጥተው ደብረ ዓባይ ወደሚባለው የመዝገበ ቅዳሴ ማስመስከሪያ የአብነት ቦታ ገዳም በመሄድ ምስክር ከሆኑት ሊቅ ከመምህር የኋላሸት መንገሻ ምዕራፍ ጾመ ድጓ፣ ባሕረ ሐሳብና የመዝገበ ቅዳሴን የዜማ ትምህርት ልኩን፣ አመሉንና ተቃራኒውን ለይተው ለመምህርነት በሚያበቃ ደረጃ ስለወሰነት በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡

ከዚያም በኋላ በዚሁ ገዳም ቅዳሴ እያስተማሩ ከመሪጌታ መጽሔት ቅኔ ተምረዋል፡፡ በዚህም ሳይወሰኑ የቅኔ ሞያቸውን ለማዳበር ከደብረ ዓባይ ተነሥተው ወደ ጎንደር ክፍለ ሀገር በመሄድ በሊቅነታቸው ከታወቁት ከመምህር አክሊሉ ገብረ ሥላሴ ዘንድ ቅኔ ቤት ገብተው ለአምስት ዓመት ያህል ቅኔ ከነአገባቡ ከመማራቸውም በላይ የዳዊትንና የፍትሐ ነገሥትን ትርጓሜንም ከርሳቸው አሂደዋል፡፡

ከዚያም ወደነበሩበት ገዳም ወደ ደብረ ዓባይ ተመልሰው በዚያው ቅዳሴ እያስተማሩ ለ፯ ዓመታት ያህል ከየኔታ የኋላሸት ጉባኤ መጻሕፍት ሐዲሳትን አሄደዋል፡፡ በዚህም ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው አቡነ መዝራዕተ ክርስቶስ ገዳም ወንበር ዘርግተው ጉባኤ አስፍተው ለ፲፪ ዓመታት ያህል በአፍለኛው ጉባኤያቸው ጠንክረው በማስተማር ብዙ ዲያቆናትን፣ ቀሳውስትንና መምህራንን አፍርተዋል፡፡

ቀጥሎም መምህራቸው የኔታ የኋላሸት በ፲፱፻፷፪ ዓ.ም ታኅሣሥ ፲፫ ቀን ስለ ዐረፉ በእሳቸው እግር ተተክተው ሲያስተምሩ ከቆዩ በኋላ የትግራይ ክፍለ ሀገር ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በመቀሌ ከተማ ያሠሩት ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅ የካህናት ማሠልጠኛ አዳሪ ቤት ስለሆነ ለቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ፍሬ የሚያፈሩ መሆናቸውን በመግለጽ ደጋግመው ስለጻፉላቸው፣ አስጠርተውም ስለነገሩዋቸው ቀደም ሲል ከቦታው አብረዋቸው ከየኔታ የኋላሸት የተማሩ አባት ቄሰ ገበዝ ገብረ ሊባኖስን ተክተው በ፲፱፻፷፫ ዓ.ም ወደ መቀሌ መጡ፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጉባኤ አስፍተው በከሳቴ ብርሃን ሰላማ መንፈሳዊ ኮሌጅና በደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በማስተማር ላይ እንዳሉ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በ፲፱፻፸፭ ዓ.ም አገልግሎታቸውንና ትጋታቸውን ተመልክተው መልአከ ሰላም በማለት የመዐርግ ስም ሰጥተው በመምህርነታቸው ላይ በተደራቢነት የደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል አስተዳዳሪ አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡

በዚህ ካቴድራልም ለ፳፪ ዓመታት በሰላም የኖሩ ሲሆን የማስተማሩ ሥራ እንደተጠበቀ በሳቸው አመራር በርካታ የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

ጥቂቶቹንም ለመግለጽ የደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የተሠራ ቢሆንም ብዙ ነገር ይጎድለው ስለነበር

• አጥሩ በሚገባ እንዲታጠር፣
• በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የተጀመረው ትልቁ ደወል ቤት ከፍጻሜ እንዲደርስ፣
• ትልቅ የሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ፣
• የብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሙዝየም (ቤተ መዘክር)፣
• የቅዱስ ፓትርያርክና የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ቤት፣
• የቤተ ክርስቲያኑ ቆርቆሮ እንዲቀየር፣ ምንጣፍ እንዲነጠፍ አድርገዋል፤ ሌሎችንም አስፈላጊ እድሳቶች አሳድሰዋል፤ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋይ ካህናትን መኖርያ ቤት አሠርተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ልክ እንደስማቸው ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሰላም አባት በመሆን ለ፳፪ ዓመት ሲያስተዳድሩ በካቴድራሉ አገልጋይ ካህናት ዘንድ እንዳያጥዋቸው ከመጨነቅ በቀር ምንም ዓይነት እክል ገጥሟቸው አያውቅም፤ የሰላም አባት የመሆናቸውን ያህል ሁሉም አባታዊ ፍቅር በተላበሰ መልኩ ያከብራቸዋል፤ ትእዛዛቸውን ያከብራል፤ ምክራቸውን ይቀበላል፣ በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ዘንድ እንደ አስተዳዳሪ ማዘዝ ብቻ አይታሰብም፣ ‹‹ዘይከውን ሊቀ ይኩንክሙ ላእከ›› የሚለውን አምላካዊ ቃል በመከተል

• በልማት ሥራ፣
• በማኅሌት፣ በሰዓታት፣
• በቅዳሴ፣
• በስብከተ ወንጌልና በማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ከተራው አገልጋይ ቀድሞ መገኘት የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ከላይ እንደተጠቀሰው ሞያቸው የቅዳሴ ትምህርት ብቻ አይደለም፤ የመጻሕፍተ ሐዲሳት ሞያም ስላላቸው ለ፴፫ ዓመታት ከሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ካሣ ጋር በመሆን የመዝሙረ ዳዊትን፣ የመጻሕፍተ ሐዲሳትን፣ የፍትሐ ነገሥትን እንዲሁም የውዳሴ ማርያምን፣ የቅዳሴ ማርያምን ጉባኤ በመምራት አንድ ቀን ሳይለዩ ትሕትናቸውን፣ ትዕግሥታቸውንና መልካም ምሳሌነታቸውን ያሳዩ ተወዳጅ አባት መምህር ናቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስም እጅግ አብልጠውና አልቀው ይወዱዋቸው ስለነበር ሁሉ ጊዜ ይጐበኛቸው ነበር፡፡

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በታወቀው የመዝገበ ቅዳሴ ሞያቸው በተሰጣቸው የመዓዛ ክህነት ሀብት ልዩ ተሰጥዎ ያላቸው ድምፃዊ ከመሆናቸው የተነሣ ከጥንት ከአበው ሲያያዝ የመጣውን የደብረ ዓባይ ባሕል የቅዳሴ ዜማ አብነት ግእዙና ዕዝሉ እንዲሁም አራራዩና አንቀጹ ሳይቀር በሙሉ በዘመናዊ መሣሪያ የድምፅ መቅረጫ ቴፕ ተቀርጾ በቅርስነት ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ባዘዙት መሠረት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ድምፃቸው ተቀርጾ ተሰራጭቷል ፤ በዚህም ከፍተኛ አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያን ማበርከታቸውን በመረዳት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የመታሰቢያ ስጦታ የአንገት አይከል ዕፀ መስቀል ሸልመዋቸዋል፡

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በ፲፱፻፵ ዓ.ም ማዕርገ ዲቁናን ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ጳጳስ ዘኤርትራ፤ በ፲፱፻፵፮ ዓ.ም መዐርገ ምንኵስናን ከመምህር ዘሚካኤል ዘደብረ ዓባይ ገዳም መምህር፣ (አበምኔት) በ፲፱፻፵፱ ዓ.ም መዐርገ ቅስናን ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ዘጎንደር በ፲፱፻፷፱ ዓ.ም መዐርገ ቁምስናን ከብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ዘትግራይ ተቀብለው በእነዚህ ሁሉ የክህነት መዐርጋት መንፈሳዊውን አገልግሎት እየሰጡ በንጽሕና በድንግልና የኖሩ አባት ናቸው፡፡
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ትሕትናን፣ አፍቅሮ ቢጽን፣ አክብሮ ሰብእን ዓላማ አድርገው የሚኖሩ በካህናት፣ በምእመናንና በተማሪዎቻቸው ዘንድ ተወዳጅነት ያላቸው፣ በአባትነታቸው ብዙ ፍቅርን ያተረፉ በአጠቃላይ በአርአያነታቸውና በገብረ ገብነታቸው በሁሉም ዘንድ ክብር ያገኙ ደግ አባት ናቸው፡፡

ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ይህን በመሰለው ቅድስናቸው፣ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት እውቀታቸው፣ በተለይም በመዝገበ ቅዳሴ የአብነት መምህርነታቸው አያሌ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን በማፍራታቸውና ባበረከቱት የረዥም ዘመን ቅድስናን የተመላ አገልግሎት ፍጹም አባትነታቸው ተመዝኖ ብቁ ሆነው በመገኘታቸው ሐምሌ ፱ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም በተደረገው የጳጳሳት ምርጫ ከሌሎች ዕጩ ቆሞሳት ጋር ተወዳድረው ባገኙት የድምፅ ብልጫ የመቀሌ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራልና የከሣቴ ብርሃን ሰላማ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠው ሐምሌ ፳፪ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም በብፁዕ ቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (ዶ/ር) ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እጅ ተሹመዋል።

ብፁዕነታቸው በተመደቡበት ኃላፊነት በቅንነት ሲያገለግሉ ቆይተው የካቲት ፳፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፈዋል።

የብፁዕነታቸው በረከት ይደርብን!

ምንጭ፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት